በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን
‹‹ርትዕት ሃይማኖቶሙ ለቅዱሳን አበዊነ = የአባቶቻችን ሃይማኖት የቀናች ናት››
ራሱን እስላማዊ መንግሥት (አይ ኤስ አይ ኤስ) እያለ የሚጠራው የጨካኝ አረመኔዎች ስብስብ፣ በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ላይ ያካሔደው ዘግናኝ ግድያ ሳይበቃው ይህን እኩይ ድርጊቱን በልዩ ልዩ ምክንያት ከአገር ተሰድደው በሊቢያ በነበሩ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ላይ ፈጽሟል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ‹‹ሃይማኖቱን ገልጦ የማይናገር በክብር የተገለጠ አይኾንም››/ሃይ.አበ. 63÷41/ እንዳለው ‹‹ሃይማኖታችንን አንክድም፤ ማዕተባችንን አንበጥስም›› ባሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ላይ ኢሰብአዊነት በተሞላበት ግፍ አንገታቸውን በሰይፍ በመቅላት እና ጭንቅላታቸውን በጥይት በመበታተክ በጭካኔ አገዳደል ገድሏቸዋል፡፡
ይህ ቡድን ከጨካኝ እና አረመኔ የግድያ ድርጊቱ አንጻር የአባላቱን ሰብአዊ ፍጥረት አጠራጣሪ የሚያደርገው ነው፡፡ እጆቻቸው በደም የተሞሉ ናቸው፡፡ ቅዱስ ዳዊት፣ ‹‹የሰውን ደም ለማፍሰስ እግራቸው ፈጣን ነው፤ በመንገዳቸው ኃሣር መከራ አለ፤ የፍቅርን መንገድ አያውቋትም፤ በልቡናቸው እግዚአብሔርን መፍራት የለም፤›› እንዳለው ነው፡፡ መዝ. 13(14)÷1-4፡፡
ስለኾነም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሥር የምንገኝ ሰንበት ት/ቤቶች፡-
- በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ ክርስትናን በማስገደድ እና በመቀሰጥ ለመለወጥ የሚደረገውን ዘመቻ እና እንቅስቃሴ በጥብቅ እንቃወማለን፡፡
- ራሱን አይ ኤስ አይ ኤስ ብሎ የሚጠራውን ቡድን ድርጊት በጥብቅ እናወግዛለን፡፡
- በዚኹ ቡድን እና በቡድኑ የአሸባሪነት ድርጊት ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ያወጣቸውን የአቋም መግለጫዎች በሙሉ እንቀበላለን፤ በአፈጻጸሙም እንታዘዛለን፡፡
- በደቡብ አፍሪቃ በዜጎች እና ሌሎችም ወገኖች ላይ የሚፈጸመውን ጥላቻ እና ዘረኝነት የወለደው ግድያ እና ዘረፋ በጥብቅ እናወግዛለን፡፡
- በአዲስ አበባ ያሉ ሰንበት ት/ቤቶች ኹሉ መርሐ ግብር በማውጣት በየቤተሰቦቻቸው ቤት በመገኘት ሐዘንተኞችን የሚያጽናኑ ይኾናሉ፡፡
ወደፊትም ኹኔታውን እየተከታተልን የሚጠበቅብንን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መኾናችንን እየገለጽን ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን፣ በተጋድሎ ላለፉት ወንድሞቻችን ደግሞ ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን ልዑል እግዚአብሔር እንዲሰጥልን እንለምናለን፡፡
ልዑል እግዚአብሔር በሃይማኖታችን ያጽናን፤ ለዓለሙም ሰላም ይስጥልን፤ አሜን፡፡
የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት
የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ