ማክሰኞ 26 ሜይ 2015

ሰበር-ዜና የታላቁ ደብረ ሊባኖስ ገዳም የድጓው ሊቅ አለቃ መርዓዊ /የኔታ መኮንን አረፉ

                                                                                                         ዜና ዕረፍቱ ለአለቃ መርዓዊ ሣህለ ሚካኤል ማኅቶታ ለደብረ ሊባኖስ ፈረየ ዓምአተ ወአመከአበ ቦ ዘ፷ ወቦ ዘ፴ ዘራዒሁሰ እንድርያስ ውእቱ ወፍሬሁኒ ጳጳሳት ወሊቃውንት እሙንቱ ::
   ታላቁ ሊቅ አለቃ መርዓዊ ሣህለ ሚካኤል የቤተ መንግሥት ቁም ጸሐፊና የደብረ ሊባኖስ ገዳም የሃይማኖተ አበው ትክለኛ ከሆኑት አባታቸው አለቃ ሣህለ ሚካኤልና ከእናታቸው ወ/ሮ እቱነሽ ጌታሁን በደብረ ሊባኖስ አካባቢ ልዩ ስሙ ፍኖተ ጽድቅ /ዋሻ ገደል/ ታሕሳስ 13ቀን 1915 ዓ.ም ተወለዱ
  እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ የአባታቸው ርስት ከሚገኝበት ልዩ ስ ጠሬ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከአባ ወልደ ማርያም ንባብና የቅዳሴ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጲያን በወረረበት ወቅት ከተክለ ሃይማኖት ልጆች ጋር በመሆን ገና በልጅነት ዕድሜያቸው በግዳጅ ታስረው ወደ ሞቃዲሾ ተግዘዋል ከዚያም ፋሺሽት ጣሊያን ድል ተነሥቶ ኢትዮጲያን ለቆ ከወጣ በኋላ በ1933 ዓ.ም  ከሞቃዲሾ ወደ ትውልድ ቦታቸው ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ተመልሰው በጠላት ምክንያት ለተቋረጠው ትምህርታቸው መንፈሳዊ ቅንዓትና ልዩ ፍላጎት ስለነበራቸው
 አንደኛ ከሁለቱ መምህራኖች ከአለቃ ተገኝና ከየኔታ ንጉሤ የዜማ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል::
   ሁለተኛ በ1936 ዓ.ም በሥሬ መድሐኔዓለም ዝነኛና ታዋቂ ከሆኑት ከታላቁ ሊቅ አለቃ ጥበቡ ገሜ ዘንድ ቅኔን ከነ አገባቡ ቀጽለዋል
   ሶስተኛ በ1937 ዓ.ም ወደ ጎንደር በመሄድ በእስቴ ወረዳ ልዩ ስሙ መካነ ኢየሱስ ከሚባለው ደብር ከመምህር ጥበቡ ድጓና ጾመ ድጓን ለሁለተኛ ጊዜ ተምረዋል እንዲሁም በዚሁ ደብር ከላይ በተጠቀሱት መምህር ዝማሬና መዋስዕትን በሚገባ ተምረዋል ::
አራተኛ በ1940 ዓ.ም በዚያው በጎንደር ቆላማ አካባቢ ወደ ሆነው ወደ መልዛ በመውረድ የተማሩትን እያስተማሩ ለድጓና ጾመ ድጓ ጽሑፍ የሚሆናቸውን ብርሃና በማውጣት ቆይተዋል::
  አምስተኛ በ1945 ዓ.ም የድጓ ማስመስከሪያ ወደ ሆነው ወደ ቤተልሔም ገብተው ለሶስት ዓመታት ድጓና ጾመ ድጓውን ጽፈውና አስመስክረው በመምህርነት ተመርቀዋል
 ስድስተኛ ወደ ጎንደር ከተማ በመሄድ ደብረ ኃይል ወደብረ ጥበብ በዓታ ለማርያም የአቋቋም ምስክር ከሆኑት ከአለቃ ክፍሌ ዘንድ አቋቋም በሚገባ ተምረዋል የአቋቋም ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የትምህርት ቤት ጓደኛቸውና የመንፈስ ቅዱስ ወንድማቸው ከሆኑት ከርዕሰ ደብር መዝገቡ ኃብተ ገብርኤል ጋር በመሆን ለትምህርት ከሄዱበት ከጎንደር ክፍለ ሀገር ለቀው በአውሮፕላን የኢትዮጲያ መናገሻ ከተማ ወደ ሆነችው ወደ አዲስ አበባ ከተማ መጥተው በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን በድጓ መምህርነት እያስተማሩ ሳለ በወቅቱ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፖትርያርክ በሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ መልካም ፈቃድ ለድጓ መምህርነት ተመርጠው የትውልድ ቦታቸው ወደ ሆነው ወደ ታላቁ ገዳም ወደ ደብረ ሊባኖስ በ1949 ዓ.ም ተመድበው የማስተማር ሥራቸውን ጀምረዋል::
    አለቃ መርዓዊ ሣህለ ሚካኤል ከመምህርነት ሥራቸው በተጨማሪ ባላቸው ጊዜ የሐዲስ መምህር ከሆኑት ከመምህር ፍስሐ ኪዳንና ትምህርተ ኅቡዓት አንድምታ ትርጓሜን ቀጽለዋል በመቀጠልም ከየኔታ አንድርጌ ውዳሴ ምርያምና ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜን አሂደዋል::
         አለቃ መርዓ ሣህለ ሚካኤል ዘነሣዕክሙ በፀጋ  በፀጋ ሀቡ የሚለውን አምላካዊ ቃል አብነት በማድረግ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያለዋጋ ከመላው ኢትዮጲያ የሚመጡ ደቀ መዛሙርትን በዕውቀት በመቅረጽ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን አያሌ ሊቃውንትን ለቤተ ክርስቲያኒቱ አፍርተዋል::
   አለቃ መርዓዊ ሣህለ ሚካኤልን ከመምህራን ልዩ የሚያደርጋቸው ለተማሪዎቻቸው ከዜማ ትምህርት በተጨማሪ ፍትሐ ነገሥት መጽሐ መነኮሳት የዓለም ታሪክን በማገናዘብ የዓለም ታሪክን በማስነበብ አዕምሮአቸው እንዲበለጽግ በማድረግ እጅግ የላቀ ተሰጥኦ ነበራቸው
  እንዲሁም በአካባቢው ያሉ ወንዶችና ሴቶች ህፃናትን ወደ ገዳሙ የሚመጡ መናንያንን ሴት መነኮሳትን የግዕዝ ንባብና ሥነ ጽሑፍ እንዲያውቁ በማድረግ ትውልድ የሚያኮራ ታላቅ ሥራ ሠርተዋል::
ታላቁ ሊቅ አለቃ መርዓዊ ሣህለ ሚካኤል በልዩነት ከተሰጣቸው የመንፈስ ቅዱስ ሐብት የሚያስደንቀወ የዜማ ትምህርት ለመማር ከሳቸው ዘንድ የሚመጡ ደቀ መዛሙርት ሁሉ በአዕምሮ የበለፀጉ ማስተዋልና በዕውቀት እጅግ የተካኑ መሆናቸው የእሳቸውን የመንፈስ ቅዱስ ልዩ ስጦታ መሆኑን ይገልጻል
     ሥልጣነ ክህነትን በተመለከተ አለቃ መርዓዊ ሣህለ ሚካኤል የዲቁና ማዕረግን ከብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ግብጻዊ የቅድስና ማዕረግን ከብፁዕ አቡነ ሣዊሮስ ኢትዮጲያዊ ተቀብለዋል::ሥርዓተ ምንኩስናም በዚሁ ታላቅ ገዳም ፈጽመዋል::
      አለቃ መርዓዊ ሣህለ ሚካኤል በታላቁ ገዳም በደብረ ሊባኖስ በዕልቅና ከ1977 ዓ.ም እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ሊቃውንቱን በቅንነትና በመንፈሳዊነት ሲመሩ ቆይተዋል::
   አለቃ መርዓዊ ሣህለ ሚካኤል በክብር ላይ ክብር በትሩፋት ላይ ትሩፋት ለመጨመር ወደ ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም በመሄድ ታሪካዊ ቦታዎችን ጎብኝተዋል::
አለቃ መርዓዊ ሣህለ ሚካኤል እንደ ኢዮብ በትዕግሥት እንደ አብርሃም በልግስና እንደ አባታቸው አቡነ ተክለ ሃይማኖት በተጋድሎና በትሩፋት በንጽሕና በቅድስና ምትክ የሌላቸውና አባታቸው ቅዱስ ያሬድ ዘኮኖ ልቡ ሠረገላ ለጸሎት ብፁዕ ውእቱ ያለው ቃል የተፈጸመላቸው የምንመካባቸው አባታችን ነበሩ ምንም እንኳን ለደቀ መዛሙርቶቻቸው ብርሃን ለዚህ ታላቅ ገዳም ዓምድ ቢሆኑም ለሰው ልጆች ሁሉ የማይቀር የሞት ፅዋ ለሳቸውም የማይቀር በመሆኑ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ አንሰ በድርየኒ ፈጸምኩ ወሃይማኖትየኒ ሰለጥኩ እንከሰ ጽኑሕ ሊተ አክሊል ዘየአስየኒ መኮንነ ጽድቅ ብለው ለ60 ዘመናት እስትንፋሳቸው እስከ ተቋረጠችበት ዕለት ድረስ ከደቀ መዛርቶቻቸውና ከወንበራቸው ሳይለዩ ግንቦት7 ቀን 2007 ዓ.ም በተወለዱ በ92 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተው የቀብራቸው ሥነ ሥርዓትም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አበው መነኮሳት ሊቃውንት ደቀ መዛሙርቶቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ግንቦት 8 ቀን 2007 ዓ.ም በታላቁ ደብረ ሊባኖስ በክብር ተፈጽሟል::
    ለደቀ መዛሙርቶቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን እየተመኘን ለሁላችንም በረከታቸውና ረድኤታቸው አይለየን በማለት እንሰናበታቸዋለን::




ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...