ማክሰኞ 4 ፌብሩዋሪ 2014

በቅዱስ ላልይበላ ደብር የተፈጠረው አለመግባባት በሰላም ተፈታ






በሀገራችን ታሪክ መቀዳሚነት ዓለምን በማስደነቅ የሚታወቀውና በዩኔስኮ ተመዝግቦ ሀገሪቱን በከፍተና ደረጃ የሚያስተዋውቀው የቅዱስ ላልይበላ ደብር በቀድሞው አሰተዳዳሪ አበ ገብረ ኢየሱስ አስተዳደር ፤ የከተማው ባለሃብት እና በከተማው የቱሪስት አስጎብኚ ማህበራት መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ረጅም ጊዜ የፈጀ መሆኑን የተለያዩ የዜና ምንጮች  ሲዘግቡት መቆታቸው ይታወቃል  ይሁን እንጂ በሶስት ተከፍለው ማለትም በደብሩ አስተዳደር፤ በከተማው ባለሀብት እና በከተማው ያሉ አስጎብኚ ማህበራት መካከል የአሰራር ክፍተቶች  እንደ ነበረና በተለይ በደብሩ የቀድሞ አስተዳደር አማካይነት የተፈጠሩ የአሰሠራር ችግሮች ስለነበሩ የደብሩ አስተዳዳሪ አባ ገብረ ኢየሱስ  ከስተዳዳሪነት ንዲነሱ ተደርጓል፡፡ ነገር ግን በወቅቱ የተከሰተውን አለመግባባትን ለመፍታት የከተማው አስተዳደር እና የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የሰላም ኮሚቴ አዋቅሮ ስለነበር ኮሚቴው የሶስቱንም አካላት ችግሮች ካጠና በኋላ ለሶስቱም የሚስማማ የእርቀ ሰላም ሰነድ አዘጋጅቶ ጥር 25/2006ዓ.ም በዚያው በላልይበላ ጽርሐ ቤተ አብርሃም አዳራሽ የደብሩ ሊቃውንት፤ ሰበካ ጉባዔ፤ የከተማው ባለሃብት፤ አስጎብኚ ማህበራት በተገኙበት ለደብሩ አዲስ በተመደቡት አስተዳዳሪ መ/ር አባ ወልደ ትንሣኤ አስተባባሪነት በከተማው ከንቲባና እና በሰላም ኮሚቴው ከፍተኛ ጥረት ሁሉም አካላት እንዲታረቁ ሆኖአል፡፡ በእርቀ ሰነዱ ላይም የሚከተሉት ስምምነቶች ተካተዋል፡፡

                                                                 
                                                                   

                                                                   እርቀ  ሰላሙ ሲፈጸም

በደብሩ አስተዳደር
1 . በቀድሞው አስተዳዳሪ የተባረሩት ሊቃውንት ካህናትና ልዩልዩ ሠራተኞች እንዲመለሱ
2. በደብሩ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሠራር እንዲኖር
3. የአብነት መምህራን  ሊቃውንቱ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጣቸው
4.ደብሩ ልዩ ልዩ እቅዶችን እያቀደ ከህዝቡ ጋር እተመካከረ እንዲሠራ
5. የደብሩ ትኩረት ከቱሪስቱ ባለፈ ለአካባቢው ሕዝብ የሚሆን የልማት አውታር ቢቀርጽ እና ተግባራዊ  ቢያደርግ የሚሉት እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
                          በከተማው ባለሀብት
1.    በደብሩ የሚፈጠረውን ማንኛውንም ችግሮችን ዝም ማለቱ ቀርቶ ችግሩን በጋራ መፍታት
2.   በልማት ሆነ በመሳሰሉት አገልግሎት ተሳታፊ እንዲሆኑ
3.   በከተማው የሚስተናገዱትን ቱሪስቶች በትብብር ማስተናገድና የመሳሰሉትን አካቶአል
                 የከተማው አስጎብኚ ማኅበራት

1.    የደብሩን ታሪክ በሚገባ አጥንተው ሳይጨመርና ሳይቀነስ ቱሪስቱን እንዲያስረዱ
2.   ሃይማኖታዊ ሥነ ምግባርን በተላበሰ መልኩ የማስጎብኘት ተግባራትን እንዲያከናውኑ
3.   የከተማውን ሰላም በማስፈን ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ስላላቸው የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ
4.   በገንዘባቸውም ሆነ በመሳሰሉት ደብሩን የመደገፍ ሥራ እንዲሰሩ እና የመሳሰሉትን እንዲተገብሩ በእርቀ ሰላሙ  ሰነድ ላይ ከተካተተው ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ወደፊት ችግሮች ቢኖሩም በውይይት እንዲፈታ እና ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንደ መሆናችን መጠን ለቤተ ክርስቲያናችን የሚገባንን ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ ነን በማለት እርቀ ሰላሙ ተፈጽሟል፡፡

                                        
                                                    

                                                    የጉባኤው ተሳታፊዎች በከፊል

ሰኞ 27 ጃንዋሪ 2014

በዐረብ ፔኒዙኤላ የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ልትታነጽ ነው


 click here for pdf

በመካከለኛው ምሥራቅ ከእሥራኤልና ቤይሩት ቀጥሎ ሦስተኛዋ፣ በዐረቢያ ፔኑዙኤላ ደግሞ የመጀመሪያዋ የምትሆነው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በኳታር ምድር ልትታነጽ ነው፡፡ 
በኳታር ምድር የዛሬ አሥር ዓመት ለጸሎትና ለትምህርት መሰባሰብ በጀመሩ ወንድሞችና እኅቶች የተጀመረችው የኳታር ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ወደ አካባቢው ለሥራ የሚጓዙ ምእመናንን በማሰባሰብና በማገናኘት፣ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋትና ክርስቲያናዊ ማኅበራዊ ኑሮን በማጠናከር የምትታወቅ ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያንዋ አገልግሎቷን የምትፈጽመው በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲሆን በዓረቡ ዓለም እንደተለመደውም ዘወትር ዓርብ ከሰዓት በኋላ የቅዳሴና የትምህርት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የኳታር ቅድስት ሥላሴ ምእመናን የሥራ ጫናውን ሁሉ ተቋቁመው ተግተው በማገልገል ብቻ ሳይሆን ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀው በማስጠበቅም የሚታወቁ ናቸው፡፡
በአብዛኞቹ የዓረበ ሀገሮች እንዳሉት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ በኳታር ለነበረችው ቤተ ክርስቲያንም ዋና ፈተና የነበረው የራስዋ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን አለመኖር ነው፡፡ ይህም አገልግሎቷን በሳምንት ወደ ተወሰኑ ቀናትና ሰዓታት ከማሳነሡም በላይ፣ ምእመናን የሚፈልጓቸውን ሁሉን አገልግሎቶች ለመስጠት እንዳትችል አድርጓት ነበር፡፡ ለቤተ ክርስቲያንዋ የራስዋ ሕንጻ መሥሪያ ቦታ በመፈለግ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ የነበረው የሰበካ ጉባኤ ባሳለፍነው ሳምንት በዐረቡ ዓለም የመጀመሪያ የምትሆነውን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት የሚያስችል መሬት ተረክቧል፡፡ 
እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በየመን፣ በዓረብ ኤምሬትስ፣ በባሕሬን፣ በኩዌት፣ በሊባኖስና በግብጽ የራስዋ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ቢኖሯትም በራስዋ ገንዘብ የተሠራና ንብረትነቷ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሆነ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ግን ከእሥራኤልና ቤይሩት በቀር አልነበራትም፡፡ የኳታር ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ከተሠራ በመካከለኛው ምሥራቅ ሦስተኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ‹ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን› ይሆናል፡፡
በኳታር ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ መሠራት ዘርፈ ብዙ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ በአንድ በኩል የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑን አገልግሎት ከሳምንት እስከ ሳምንት የማያቋርጥ እንዲሆን ሲያደርገው በሌላ በኩል ደግሞ በአካባቢው ላሉት ሌሎች አጥቢያዎችም አርአያነት ይኖረዋል፡፡ ከኳታር በፊት እንቅስቃሴ የጀመሩት እንደ አቡዳቢ መድኃኔዓለም ያሉትን አጥቢያዎች የጀመሩትን በርትተው እንዲፈጽሙ ያነሣሣቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያነት ታሪክ በዐረቢያ ፔኒዙኤላ የነበረው ቤተ ክርስቲያን ከ1400 ዓመታት በፊት በየመን ናግራን ታንጾ የነበረው የቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡ እርሱ ከጠፋ ከ1600 ዓመታት በኋላ በዓረቢያ ፔኑዚኤላ ሁለተኛው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በቅድስት ሥላሴ ስም እንደገና በኳታር መታነጹ የታሪኩ ተገጣጣሚነት የሚያስደንቅ ነው፡፡
ይህ ቤተ ክርስቲያን በአንድ በኩል ታሪካዊ፣ በሌላ በኩል የቤተ ክርስቲያኒቱን ሐዋርያዊ ተልዕኮ ወደ አንድ ምዕራፍ የሚያሸጋግር፣ ሲሠልስም ለሌሎች አርአያነት ያለው በመሆኑ ሥራ በኳታር ለሚገኙ ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ ግብጻውያን እንደዚህ ባሉ አካባቢዎች የሚታነጹ የተለየ ታሪክና ጠቀሜታ ያላቸውን አብያተ ክርስቲያናት በመተጋገዝ እንደሚገነቧቸው ሁሉ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም እያንዳንዷን የሕንጻዋን ብሎኬት ተካፍለው በመገንባት በታሪክ ምዕራፍ ላይ አሻራቸውን ማስቀመጥና በረከት ማግኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡
 በሀገር ቤት፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በአውስትራልያ የሚገኙ ምእመናን በአካባቢያቸው ቤተ ክርስቲያን ባይኖር ነድተውም ሆነ ተሳፍረው ወደ ሌላ አካባቢ በመሄድ ቤተ ክርስቲያን መገልገል ይችላሉ፡፤ በዐረቡ ዓለም ግን በአንድ አካባቢ አንድ አጥቢያ ብቻ ስለሚገኝ ወጣ ብሎ በሌላ አጥቢያ መገልገል አይቻልም፡፡ በተለይ ደግሞ እንደ ኳታር ባሉ ሀገሮች ያለው ቤተ ክርስቲያን አንድ ነው፡፡ ይህን ቤተ ክርስቲያን ማነጽና አገልግሎቱን ማጠናከር፣ በዐረቡ ዓለም የሚገኙ ወገኖቻችን በመንፈሳ ሕይወታቸው በርትተው፣ ከመንፈስ ጭንቀት ተላቅቀው፣ የሚደርስባቸውን ፈተናም አሸንፈው ለሀገራቸውና ለወገኖቻቸው የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው፡፡ በመሆኑም በመላው ዓለም የተሠማሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚታነጸው የራሳቸው አጥቢያ መሆኑን አስታውሰው ልባቸው ኳታር ሊሆን ይገባል፡፡ 
 
የገባው ክርስቲያን እግዚአብሔር ሲሠራ አብሮ ይሠራል፡፡ 
         ዶሃ፣ ኳታር

ዓርብ 24 ጃንዋሪ 2014

ፓትርያርኩ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በሙስና ላይ እንዲዘምቱ አዘዙ


  • በቤተ ክርስቲያናችን ሸፍጥና ጉቦ ተንሰራፍቷል›› /ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ/
  • ሰንበት ት/ቤቶቹ የአማሳኝ አስተዳዳሪዎችን ዶሴ ለፓትርያርኩ ለማቅረብ ተዘጋጅተዋል
(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፫ ቁጥር ፯፻፴፩፤ ቅዳሜ ጥር ፲ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም.)
His Holiness Patriartch Abune Mathias
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በተንሰራፋውና ለዕድገቷ መሰናክል ኾኖ በተደነቀረው ሙስናና ሸፍጥ ላይ በተጠናከረ ኃይል በመዝመት የተጀመረውን የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ከዳር እንዲያደርሱ አዘዙ፡፡
Dn Yonas Isayas of A.A.D SSD Unity reading the position paper
የአ/አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሥራ አመራር ተወካይ ዲያቆን ዮናስ ኢሳይያስ ለፓትርያርኩ የፁረ ሙስና እንቅስቃሴ፣ ለአ/አ ሀ/ስብከት የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ተግባራዊነት የሰንበት ት/ቤቶቹን የድጋፍ መግለጫ ሲያሰማ
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፣ ቅዱስነትዎ በይፋ የገለጹትንና እንዲስተካከል አበክረው ማሳሰቢያ የሰጡበትን የቤተ ክርስቲያን ዘርፈ ብዙ ችግር ለማረም በሚደረገው ጥረት ኹሉ በግንባር ቀደምነት መሰለፍ የእኛም የወላጆቻችንም ጽኑ አቋም እንደኾነና በታዘዝንበት መሥመር ኹሉ ለመሰለፍ ዝግጁዎች መኾናችንን ለቅዱስነትዎ በላቀ አክብሮትና ትሕትና ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

አቡነ ማትያስ ትእዛዙን የሰጡት ሙስናና ብልሹ አስተዳደርን በሥር ነቀል እርማት ለማስተካከል ያስተላለፉትን መግለጫ ለመደገፍና የፓትርያርኩ ልዩ ሀ/ስብከት የኾነው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ያዘጋጀው የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናት ተግባራዊ እንዲኾን ለመጠየቅ ከትላንት በስቲያ ኀሙስ፣ ጥር 8 ቀን 2006 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ለተሰበሰቡት በሺሕ ለሚቆጠሩ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በሰጡት መመሪያ፣ ቃለ ምዕዳንና የበዓለ ጥምቀት ቡራኬ ነው፡፡
ከአዲስ አበባ ሀ/ስብከት 160 ገዳማትና አድባራት የተሰበሰቡት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በሀ/ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሥራ አመራር አማካይነት ባወጡት መግለጫ፣ ፓትርያርኩ ሙስናና ብልሹ አስተዳደርን በማውገዝ ለማስተካከል አበክረው ሥራ በመጀመራቸው ምስጋናቸው አቅርበዋል፡፡ ብዙኃን የሰንበት ት/ቤት አባላት አይነኬ ኾኖ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲያስተቻት የቆየውን ሙስናና ብልሹ አስተዳደር እስከ እስር ደርሰው ሲታገሉት እንደቆዩም ተናግረዋል፡፡
የሙስናና ብልሹ አስተዳደር ተጠቂ እየኾኑ በማደጋቸው አስከፊነቱን በሚገባ እንደሚያውቁ በመግለጫቸው ያተቱት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶቹ፣ ፓትርያርኩ በየጊዜው ያስተላለፏቸውን መመሪያዎች በመከታተልና የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ ስለሚያደርገው እንቅስቃሴ በሀ/ስብከቱ ጽ/ቤትና በየክፍለ ከተማቸው በመወያየት ችግሩ ከመሠረቱ እንደሚወገድና በዘመናቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ትንሣኤ እንደቀረበ መገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡
ሙስናንና ብልሹ አስተዳደርን ለማረም የሚካሔደው እንቅስቃሴ በእነርሱም በወላጆቻቸውም ጽኑ እምነት እንደተያዘበት የጠቀሱት ወጣቶቹ፣ ጥረቱን ከግቡ ለማድረስ ከፓትርያርኩ ጎን ቆመው በታዘዙበት መሥመር ለመሰለፍ ዝግጁዎች መኾናቸውን አስታውቀዋል፡፡
Sunday School Students of Holy Trinity Cathedral headind to Jan Meda,2004E.CTimket
የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሰንበት ት/ቤት መዘምራን ወደ ጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት ሲያመሩ
‹‹የፀረ ሙስና እንቅስቃሴውን እንደግፋለን ብላችኁኛል፤ እኔም እንደምትደግፉኝ አምናለኹ፤›› በማለት ተስፋቸውን የገለጹት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በበኩላቸው÷ ‹‹ዘመኑ የእምነት ጉድለትና የኑፋቄ ነው፤ ሐቅ፣ መልካም አስተዳደር፣ እውነተኝነትና ሓላፊነት ጠፍቷል፤ በቤተ ክርስቲያናችን ሸፍጥና ጉቦ ተንሰራፍቷል፤›› ሲሉ አምርረው ተናግረዋል፡፡ ስለ ሙስናና ብክነት ከሚሰጧቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎች ጋራ ተያይዞ ‹‹ኹላችንም ሌቦች ተብለናል›› የሚል ቅሬታ ያቀረቡላቸው ወገኖች መኖራቸውን ያልሸሸጉት አቡነ ማትያስ፣ ‹‹የሚያመው ያመው ይኾናል፤ ኹላችኁም አማሳኞች ናችኹ የሚል አልወጣኝም፤ የሚያማስኑ እንዳሉ ግን ሐቅ ነው፤›› ሲሉ የችግሩ አስከፊነት ሊካድ እንደማይገባው አረጋግጠዋል፡፡
ሙስና ማለት ጥፋት ነው ሲሉ የቃሉን ትክክለኛ ንባብና ገላጭነት ያብራሩት ፓትርያርኩ፣ ‹‹በቤተ ክርስቲያን ያለው የሙስና ሙስና›› መኾኑን በመግለጽ በፀረ ሙስና ቅስቀሳው የሰንበት ት/ቤት ወጣቶቹ በይበልጥ እንዲዘምቱበት አሳስበዋቸዋል፡- ‹‹ተይዞ ባለው የፀረ ሙስና ቅስቀሳ እናንት የሰንበት ት/ቤት አባላት በይበልጥ ብትዘምቱበት፤ በተጠናከረ ኃይል ይህን ብትረዱኝና ከዳር ብናደርሰው አመሰግናችኋለኹ፡፡››
በተያያዘ ዜና÷ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን የአደረጃጀትና አሠራር ለውጥ እንቅስቃሴ የሚበዙት የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የጽ/ቤት ሠራተኞች፣ ማኅበረ ካህናት፣ ማኅበረ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እንደሚደግፉት እየተገለጸ ቢሰነብትም ‹‹ምእመናን በእኛ ሕግ ምን ያገባቸዋል፤›› የሚሉ አንዳንድ አስተዳዳሪዎች ቅሬታቸውን ለፓትርያርኩ ማቅረባቸውን የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ምንጮች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
እንደምንጮቹ መረጃ፣ ቅሬታ አቅራቢ አስተዳዳሪዎቹ የመዋቅር ለውጡን የሚቃወሙ ሲኾኑ ከእነርሱም መካከል ለአደረጃጀትና አሠራር ለውጡ በተከታታይ የተካሔዱት የድጋፍ መግለጫ ስብሰባዎች ምእመናኑን በእነርሱ ላይ ኾነ ተብሎ ለማነሣሣት የታለሙ ናቸው ብለው ያምናሉ፡፡ ሰንበት ት/ቤቶቹ ከፓትርያርኩ ጋራ ባካሔዱት ውይይት ሙስናና ብልሹ አስተዳደርን በግልጽ በመቃወማቸውና በማጋለጣቸው ያሳሰሯቸውና ያስደበደቧቸው አስተዳዳሪዎች እንዳሉ ተገልጧል፡፡
የሰንበት ት/ቤት ወጣቶቹ የቤተ ክርስቲያንን ሀብትና ንብረት ለግል ጥቅም በማዋልና ለባዕድ አሳልፎ በመስጠት አላግባብ በልጽገዋል የሚሏቸውን አማሳኝ አስተዳዳሪዎች ዶሴ ለፓትርያርኩ ለማቅረብ፣ እንደ ሕጉ አግባብም ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ለማመልከትም ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ከአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሥራ አመራር አባላት ተጠቁሟል፡፡
YeTimket Lijoch
ዉሉደ ጥምቀት
የቤተ ክርስቲያኒቱ የጥቅምት ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ÷ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሃይማኖት ዕንከን ሳይኖርባት፣ ሞያ ሳያንሳትና ተቆርቋሪ ምእመናን እያሏት በመልካም አስተዳደርና በፋይናንስ አያያዝ ምክንያት የምትወቀስበትና ልጆቿን የምታጣበት ታሪክ መገታት እንዳለበት የገለጸ ሲኾን የቤተ ክርስቲያኒቱን የአገልግሎት አፈጻጸም እሴቶችና መርሖዎች የሚገልጸው መሪ ዕቅድ ከገመገመ በኋላ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦትን ከሥሩ ለመቅረፍ በሚያስችል አኳኋን ተዘጋጅቶ እንዲቀርብለት መመሪያ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

ዓርብ 17 ጃንዋሪ 2014

ምሥጢረ ጥምቀት

ጥምቀት በጽርዕ ቋንቋ ኤጲፋኒያ በግእዝ አስተርዮ በአማርኛ መገለጥ ይባላል፡፡ ቃሉ በቀጥታ ሲተረጎም በውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት፣ መነከር፣ መዘፈቅ፣ መጥለቅ ማለት ነው፡፡ ጥምቀት ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን (ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ሜሮን፣ ምሥጢረ ቁርባን፣ ምሥጢረ ንስሐ፣ ምሥጢረ ክህነት፣ ምሥጢረ ተክሊል፣ ምሥጢረ ቀንዲል) አንዱና ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ በዮሐ. 3፥5 ላይ ‹‹እውነት እውነት እልሀለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡›› ብሎ እንደተናገረው ከውኃና ከመንፈስ ተወልደን የሥላሴን ልጅነት የምናገኝበት መንግሥተ ሰማያት የምንገባበት ኃጢአታችን የሚደመሰስበት ድኅነትን የምናገኝበት ዐቢይ ምሥጢር ነው፡፡ ጥምቀት በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ አምኖ ለሚፈጽመው ሰው ሁሉ ለኃጢአት መደምሰሻ ከሥላሴ የጸጋ ልጅነት ለመቀበልና የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የተሰጠ ልዩ የሕይወት መንገድ ነው፡፡


 የጥምቀት አመጣጥ
የምሥጢረ ጥምቀት መስራች ራሱ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ነገር ግን ከጌታችን ጥምቀት በፊት አይሁድ ለመንጻትና ለኃጢአት ሥርየት (ይቅርታ) የሚጠመቁት ጥምቀት ነበራቸው፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር በረድኤት የሚገለጥባቸው የተቀደሱ ዕለታትና ቦታዎች ሁሉ ሰውነትንና ልብስን ማጠብ የእግዚአብሔር ቤት ማገልገያ የሆኑ ዕቃዎችን ሁሉ ማጠብ ማንጻት ሥርዓትና ልማድ ነበር፡፡ የእግዚአብሔርም ፈቃድ ያለበት አሠራር ነበር፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቤት ከመቅረባቸውና ለተቀደሰው አገልግሎት ከመግባታቸው አስቀድመው እግሮቻቸውንና እጆቻቸውን የመታጠብ ግዴታም ነበራቸው፡፡ ሰውነታቸውን ከአፍአዊ (ከውጫዊ) እድፍ በማጠብና ንጹሕ በማድረግ በባሕርይ ንጹሕና ቅዱስ በሆነው አምላክ ፊት ውስጣዊ ሕይወትን ንጹሕ አድርጎ የመቅረብን ሥርዓትና ምሥጢር የሚያመለክት ልማድ ነበር፡፡
‹‹አሮንንና ልጆቹን ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ታቀርባቸዋለህ፤ በውኃም ታጥባቸዋለህ›› /ዘፀ. 29፥4/
‹‹ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አቀረበ፣ በውኃም አጠባቸው፡፡›› /ዘሌ. 8፥6/

በብሉይ ኪዳን ዘመን የጥምቀት ምሳሌዎች
  1. አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ መልከጼዴቅ መሄዱ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም የምእመናን መልከጼዴቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ናቸው፡፡ /ዘፍ. 14፥17/
  2. ኢዮብ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ተፈውሷል፡፡ ይህም ምእመናን ተጠምቀው ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ የመፈወሳቸው ምሳሌ ነው፡፡
  3. ንዕማን ሶርያዊ ተጠምቆ ከለምጽ ድኗል፡፡ 2ነገ. 5፥14 ይኸውም ምእመናን ተጠምቀው ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ የመዳናቸው ምሳሌ ነው፡፡
  4. የኖኅ መርከብ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ. 6፥13 ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍሳት በውኃ የዳኑባትን መርከብ ሲሠራ በኖኅ ዘመን የእግዚአብሔር ትዕግሥት በዘገየ ጊዜ ቀድሞ ክደውት ለነበሩት ሰበከላቸው፡፡ አሁንም እኛን በዚያው አምሳል በጥምቀት ያድነናል ሥጋን ከዕድፍ በመታጠብ አይደለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመነሣቱ በእግዚአብሔር እንድናምን መልካም ግብርን ያስተምረን ዘንድ ነው እንጂ፡፡›› /1ጴጥ. 3፥20/
  5. እስራኤል በደመና ተጋርደው ቀይ ባሕርን መሻገራቸው የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ /ዘፀ. 14፥15/ ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አባቶቻችን ሁሉ ደመና እንደ ጋረዳቸው ሁሉም በባሕር መካከል አልፈው እንደ ሄዱ ልታውቁ እወዳለሁ፡፡ ሁሉንም ሙሴ በደመናና በባሕር አጠመቃቸው›› /1ቆሮ. 10፥1/
  6. ለአብርሃም ሕግ ሆኖ የተሰጠው ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም ከአረጀ በኋላ ቢገረዝም ልጆቹ ግን በተወለዱ በስምንተኛው ቀን እንዲገረዙ እግዚአብሔር አዞ ነበር /ዘፍ. 17፥9/ ‹‹በሰው እጅ የአልተደረገ መገረዝን በእርሱ ሆናችሁ ተገረዛችሁ፡፡ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር ተነሥታችኋል፡፡›› /ቈላ. 2፥11/

ጌታችን ለምን ተጠመቀ?
ሀ. ለትሕትና ለትምህርት ለአርአያ /ዮሐ. 13፥1-17/
ለ. በዮርዳኖስ ተጥሎ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤ ሊደመስስ /ቈላ. 2፥14/
ሐ. የሦስትነትን ምሥጢር ይገልጥልን ዘንድ /ማቴ. 3፥16/
መ. በእርሱ ጥምቀት የእኛን ጥምቀት ለመባረክ

ጌታችን መች ተጠመቀ?
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በ5531 ዓመተ ዓለም ዘመነ ሉቃስ ማክሰኞ ጥር 11 ቀን ከሌሊቱ በ10ኛው ሰዓት ነበር፡፡ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 19 በተጠመቀም ጊዜ ዕድሜው 30 ዓመት ከ13 ቀን ነበር፡፡ /ሉቃ. 3፥23/

ጌታችን ስለምን በ30 ዓመት ተጠመቀ?
በብሉይ ኪዳን ሥርዓትና ልማድ ካህናት ለቤተ እግዚአብሔር ተልእኮ እና መንፈሳውያን አገልግሎቶች ከ30 ዓመት ዕድሜ በፊት አደባባይ አይወጡም ነበር፡፡ እጅግ አስፈላጊ እንኳ ቢሆን ከ20 እና 25 ዓመት አስቀድሞ ለአገልግሎት መሰየም ልማድ አልነበረም፡፡ የቤተ እግዚአብሔር አገልጋዮች በዕድሜና በዕውቀት የበሰሉ፣ በጠባይና በሥራ ልምድ የተፈተኑ ተልዕኳቸውን በብቃት ለመወጣት በተገልጋዩ ሕዝብ ዘንድ የተመሰከረላቸው መሆን ነበረባቸው፡፡ /ዘፀ. 4፥3፤1ዜና መዋ. 23፥24፤ 1ጢሞ. 3፥6-10/ ያንን ሥርዓት ለመፈጸም ጌታችን የተጠመቀውና ለትምህርተ ወንጌል የተገለጠው በ30 ዓመቱ ነበር፡፡ ዮሐንስ መጥምቅም የጌታን መምጣት ለማወጅ በዮርዳኖስ ይሁዳ ምድረ በዳዎች ወጥቶ የታየው ከ30 ዓመት ዕድሜው በኋላ ነው፡፡ ሌላው ዐቢይ ምክንያት የሰው ሁሉ መጀመሪያ አዳም የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ተፈጥሮ በ40ኛ ቀን ተሰጥቶት ኋላም በኃጢአት ምክንያት ያስወሰደውን ልጅነት ለማስመለስ ነው፡፡ ክርስቶስ የተጠመቀው ክብር ሽቶ ሳይሆን የአብ የባሕርይ ልጅነቱን (የባሕርይ አምላክነቱን) ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ለማስመስከር፣ ውኃውን ለመቀደስ፣ የአዳምን ልጆች የእዳ ደብዳቤ ለመደምሰስና በስህተት የጠፋውን የልጅነት ክብር ለመመለስ ነው፡፡ ጌታ ተጠምቆ ከውኃው ከወጣ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ በማረፍ አብ በደመና ‹‹ይህ ልጄ ነው›› ብሎ ሲመሰክርለት ምሥጢረ ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በጉልህ ተረጋግጧል፡፡ /ማቴ. 3፥16/

ጌታችን በዮሐንስ እጅ ለምን ተጠመቀ?
ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ሲሆን በአገልጋዩ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ በፍጹም ትሕትና ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ ይህንንም ያደረገልን አብነት ሊሆነን ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ቅዱስ ዮሐንስን ‹‹መጥተህ አጥምቀኝ ›› ብሎት ቢሆን ኖሮ ነገ ነገሥታቱና መኳንንቱ ካህናቱን መጥታችሁ አጥምቁን ባሉ ነበር ስለዚህ እንዲህ እንዳይሆን ነው፡፡ ጌታችን ‹‹ጌታ ስሆን በባርያዬ እጅ እንደተጠመቅሁ እናንተም ወደ ቤተክርስቲያን ሄዳችሁ በካህናት እጅ ተጠመቁ›› ሲል ነው፡፡
ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀው ልጅነትን የምታሰጥ ጥምቀትን ባርኮ ቀድሶ ሊሰጠን እንጂ ክብር እንዲሆነው አይደለም፡፡ ምክንያቱም፡- እርሱ እከብር አይል ክቡር እጸድቅ አይል ጻድቅ ነውና፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን በማን ስም አጠመቀው?
ጌታችን ዮሐንስን አጥምቀኝ ባለው ጊዜ ‹‹ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለሁ አንተን በማን ስም ላጥምቅህ? በአብ ስም እንዳላጠምቅህ አብ አባትህ ባንተ ሕልው ነው በወልድ ስም እንዳላጠምቅህ ወልድ አንተ ነህ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዳላጠምቅህ መንፈስ ቅዱስ ሕይወትህ ባንተ ሕልው ነው ታዲያ በማን ስም ላጥምቅህ?›› ብሎ ቢጠይቀው ጌታም ‹‹እንደ መልከጼዴቅ ሥርዓት አንተ የዓለም ካህን ብርሃንን የምትገልጥ የአብ የባሕርይ ልጅ ሆይ ይቅር በለኝ›› ብለህ አጥምቀኝ አለው፡፡

ዮሐንስ ጌታን ሲያጠምቀው እጁን ለምን አልጫነበትም?
-    ዮሐንስ በጥምቀት አከበረው /ልዕልና ሰጠው/ እንዳይባል፡፡
-    መለኮትን በእጅ መንካት ስለማይቻል

ጌታችን ጥምቀቱን ለምን በዮርዳኖስ አደረገው?
በኢየሩሳሌም አካባቢ ብዙ ወንዞች ኩሬዎችና ሐይቆች መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ ጌታ ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ያደረገው ስለዚሁ አስቀድሞ የተነገረውን ትንቢት መፈጸሙን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ‹‹ባሕር አይታ ሸሸች ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ›› /መዝ. 113፥3/ ከዚህም ጋር ከላይ ምንጩ አንድ የሆነው ዮርዳኖስ ዝቅ ብሎ በደሴት ተከፍሎ እንደገና እንደሚገናኝ በግዝረት በቁልፈት (በመገዘርና ባለመገዘር) ተለያይተው የነበሩ ሕዝብና አሕዛብ መላው የአዳም ልጆች በጌታችን ጥምቀት አንድ መሆናቸውን የሚገልጽ ትርጉም አለው፡፡ እስራኤል ዮርዳኖስን ተሻግረው ምደረ ርስት ገብተዋል፡፡ ያመኑ የተጠመቁ ምዕመናንም በጥምቀት ገነት መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ፡፡ ሌላው በዮርዳኖስ ተጥሎ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤ ይደመስስልን ዘንድ /ቈላ. 2፥14/

ጌታችን ለምን በሌሊት ተጠመቀ?
በኃጢአት ጨለማ ስለነበረ ሕዝብ የጽድቅ ብርሃን እንዲወጣለትና በጨለማ የሚመስል ኦሪት ይኖር ስለነበረ ለሕዝብ ብርሃን የሆነ ወንጌል መገለጡን ለማሳየት ነው፡፡ ኢሳ. 9፥2
-    አንድም ጌታ ልደቱ፣ ጥምቀቱ፣ ትንሣኤው እንዲሁም ምጽአቱ በሌሊት ነው፡፡ ይኽም የሆነበት ምክንያት፡- ሌሊቱን ተከትሎ የሚመጣው ብርሃን በመሆኑ ከሞት ወደ ሕይወት ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሲኦል ወደ ገነት የመሸጋገራችን ምሳሌ ነው፡፡
-    አንድም መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል የሚወርድ ነውና በጌታ ላይ የወረደው ርግብ እንጂ መንፈስ ቅዱስ አይደለም ባሉ ነበር፡፡ በሌሊት ርግብ የለም ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ይታወቅ ዘንድ፡፡


መንፈስ ቅዱስ ለምን ጌታ ከውኃ ከወጣ በኋላ ወረደ?
ሀ. ዮሐንስን ያከብሩት ነበርና መንፈስ ቅዱስ የወረደው ለዮሐንስ እንጂ ለጌታ አይደለም ይሉ ነበርና ምክንያቱን ጌታ ውኃ ውስጥ እያለ ከዮሐንስ አልተለየም ነበርና፡፡
ለ. ውኃን የሚባርክ መልአክ እንዳለ ያውቁ ነበርና ውኃውን ለመባረክ አንጂ ለጌታ አይደለም እንዳይባል፡፡
ሐ. ማረፊያ ያጣች ርግብ በባሕር ስትበር አረፈችበት ባሉ ነበርና ሐሳባቸውን በሙሉ ያጠፋ ዘንድ ከውኃ ውስጥ ከወጣ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወረደ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመንቀሉ ክቡር

 ምንጭ ኆኅተ ብርሀን ሰ/ት/ቤት

ሰኞ 13 ጃንዋሪ 2014

ከቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አቅጣጫ ውጭ የአ/አ ሀ/ስብከትን የአደረጃጀትና አሠራር ጥናት ለመገምገም በተቋቋመው ኮሚቴ ውስጥ በጠቅ/ቤተ ክህነቱና በሀ/ስብከቱ ችግሮች ተጠቃሽ የኾኑ ግለሰቦች መካተታቸው እንደሚያሳስባቸው የገለጹ ምእመናን አካሔዱ በጥንቃቄ እንዲጤን ጠየቁ


  • ጥናቱን የማስቆም አልያም የማዘግየት ፍላጎት ያላቸው ሙሰኛ እና ጎጠኛ ‹ተቃዋሚዎች› የመናፍቃንን ዓላማ በውስጥ አርበኝነት የማስፈጸም ዓላማ ሊኖራቸው እንደሚችል በማስጠንቀቅ ሕጋዊና የሥነ ሥርዐት ርምጃዎች እንዲወሰዱባቸው አመልክተዋል

*                *                *

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን 
ጥር 5 ቀን 2006 ዓ.ም 
ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
አዲስ አበባ 
ጉዳዩ፡- የቤተ ክርስቲያኒቱን አደረጃጀትና አሠራር ለማሻሻል የተጠናው ጥናት ተግባራዊ እንዲደረግ ስለ መጠየቅ

ቅዱስ አባታችን፡-
ከሁሉ አስቀድሞ እኛ ምእመናን የመንፈስ ቅዱስ ልጆችዎ በመጀመሪያው በዓለ ሢመትዎ ዋዜማ ላይ ኾነን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ው ፓትርያርክ ኾነው በመመረጥዎ የተሰማንን ደስታ እየገለጽን መልካም የሥራ ጊዜ እንዲኾንልዎት እንመኛለን፡፡ እንዲሁም ለ2006 ዓ.ም. የጌታችን የመድኃኔታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ የልደት በዓል እንኳን በሰላም አደረሰዎ ስንል የቅዱስነትዎ ቡራኬ እንዲደርሰን ከእግረ መስቀልዎ ሥር ኾነን በመማፀን ነው፡፡ 
ቅዱስ አባታችን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነቷ ሥርዓቷና ትውፊቷ እንከን የማይወጣለት በዓለም ዐደባባይ ገናናነቷ ጥንታዊነቷና ድንቃድንቅ ቅርሶቿ ገዳማትና አደባራቷ ከሰው ልጆች ዓይነ ኅሊና የማይጠፋ ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም መንፈሳዊና ማኅበራዊ አስተዋፅኦ ያበረከተች እንደኾነች በእምነት ከማይመስሉን ወገኖች ጭምር ምስክርነት የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ብቻ ሳትወሰን የመንግሥት መዋቅርና አደረጃጀት እንደዛሬው ባልተስፋፋበትና ባልተጠናከረበት ወቅት የሕዝቡ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ኑሮ እንዲሻሻል፣ የአገሪቱ ሉዓላዊነት እንዲከበር፤ ፍቅርና ሰላም እንዲሰፍን በሕዝቡ የዕለት ተዕለት አኗኗር ሁሉ የመቻቻል መንፈስ እንዲሰፍን በማድረግ በአጠቃላይ ለሀገሪቱ ሥልጣኔና ዕድገት የተጫወተችውን የላቀ ሚና ታሪክ የማይረሳውና በገሓዱ ዓለምም በግልጽ የሚታይ ነው፡፡ 
ቅዱስ አባታችን፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፡- ይህ በእንዲህ እንዳለ ኾኖ በአሁኑ ወቅት በሰፊው የሚስተዋለው የሥነ ምግባር ግድፈቶች፣ ጎጣዊ/ዘረኛ አሠራሮችና የሙስና መንሰራፋት ለምእመናን ወደ መናፍቃን ጎራ መጉረፍ ምክንያት ከመኾናቸውም ባሻገር ፤በቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች  የተጠናና የተደራጀ በሚመስል ኹኔታ የሚፈጽሙትን የሥነ ምግባር ጉድለቶች በማየት አንዳንድ ምእመናን ከቤተ ክርስቲያን ይርቃሉ፤ በቤታቸው ኾነው መጸለይን ይመርጣሉ፤ እነሱን አርኣያ በማድረግም ኃጢአት ለመሥራት ይደፋፈራሉ፤ ሃይማኖቱ በራሱ ሕጸጽ እንዳለበት አድርገው የሚቆጥሩም አሉ፡፡ 
የሙሰኞችና የጎጠኞች ዋነኛ ዓላማ ላይ ላዩን እንደሚታየውና እንደሚገመተው የራሳቸውን ጎጥ/ጎሳ አባላት መጥቀም ብቻ ሳይሆን በጥልቀት ሲመረመር ራሳቸውን ለመጥቀም በሚያደርጉት እንቅስቃሴ አውቀውም ኾነ ሳያውቁ በተዘዋዋሪ መንገድ በውስጥ አርበኝነት የመናፍቃንን ዓላማ ማስፈጸም መኾኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
የውስጥ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ከውጭ ጠላቶች የበለጠ አደገኛ ናቸው፤ ከመለያቸውም መካከል፡-  
·   ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዐት ሥራ ላይ እንዳይውል በጥብቅ ይከላከላሉ፡፡
·    ከአጥቢያ ጀምሮ እስከ ሀገረ ስብከትና እስከ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ድረስ በተዘረጋ የሙስና መረብ ከሕጋዊ መዋቅሩ በበለጠ እርስ በርስ በመደጋገፍ የተፈጸሙ ጥፋቶችን ይሸፋፈናሉ፤
·   የሥራ ዕድገት በሞያና በትምህርት ብቃት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በዘመድና በጉቦ እንዲፈጸም ያደርጋሉ፣
·       ጥፋተኛነቱ በተረጋገጠ የደብር አለቃ ወይም ሓላፊ ላይ ተገቢውን የሥነ ሥርዐት ርምጃ በመውሰድ ፋንታ ወደ ሌላ የተሻለ ቦታ እንዲዘዋወሩ ይደረጋል፡፡ 
በወዳጅም በጠላትም በአኩሪ ታሪክና ምግባር የምትታወቀው ቤተ ክርስቲያናችን የዘመናት ስሟንና ክብሯን የማይመጥን እኩይ ተግባራት የሚፈጸምባት ቦታ፤ ከሃይማኖት ይልቅ ግላዊ ጥቅም በሚያስቀድሙ የውስጥ አርበኞች ብልሹ አሠራር ዘረኝነት፣ ሙስናና የሥነ ምግባር ጉድለት ጎልቶ የሚታይባትና ተከታዮቿን የሚያሸማቅቅ ነውር ተግባር የሚፈጽሙባት እየኾነች መጥታለች፡፡
ቅዱስ አባታችን፡- ይህን ኹኔታ በሚገባ የተገነዘቡት ቅዱስነትዎ በግንቦት 12/2006 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር “ምእመናን በተለያየ መልኩ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡትን ስጦታ ዘመኑ በሚፈቅደው የፋይናንስ አያያዝና ቁጥጥር ባለመያዛችን ለቤተ ክርስቲያን ሥራ ከሚውል ይልቅ በየመንገዱ እየተንጠባጠበ ወፎች የሚለቃቅሙት እንደሚበዛ ፍጹም የማይካድ ሐቅ ነው፡፡
በሌላ በኩል ከአድልዎና ከወገንተኝነት ሙሉ በሙሉ ያልተላቀቀው አስተዳደራችን የቤተ ክርስቲያናችን ታላቅነትና ተሰሚነትን ክፉኛ እየጎዳው መኾኑ አሌ ልንለው አይገባም” የሚለውን አባታዊ ቃልዎን በብዙኃን መገናኛ ስንሰማ እግዚአብሔር የእውነተኛ አገልጋዮቹን እንባ ተቀብሎ የቤተ ክርስቲያናችንን ችግር መፍትሔ የሚሰጥበት ጊዜ ደረሰ ብለን ደስ ብሎናል፤ በከፍተኛ አድናቆትም ተቀብለናል፡፡
የቅዱስ አባታችንን መንደርደሪያ ሓሳብ መሠረት አድርጎ በሰፊው  የተወያየው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤም በወርቅ ቀለም የተጻፈውን የቤተ ክርስቲያናችንን መልካም ስምና ዝና ወደ ቀደመ የክብር ቦታው ለመመለስ የሚያስችል ጥናት የሚያጠና ኮሚቴ ማቋቋሙዎን በተለይም የቅዱስነትዎ ልዩ ሀገረ ስብከት በኾነው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አሠራርና አደረጃጀት የሚያጠና ኮሚቴ መዋቀሩን ስንሰማ፣ ‹‹እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰባት፤ የቤተ ክርስቲያናችንን ትንሣኤ ሊያሳየን ነው፤›› ያላለ ምእመን አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግር ይፈታል ተብሎ የታመነበት ይህ ጥናት ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ቀርቦ ተቀባይነት ማግኘቱን ሰምተን ደስታችን ወደር አልነበረውም፡፡ ስለአደረጃጀትና የአሠራር ማሻሻያው ጥናት ግንዛቤ ለማስጨበጥ በተከታታይ በተካሔዱ ውይይቶች የተሳተፉ ማኅበረ ካህናትና ምእመናንም በጥናቱ ይዘት በእጅጉ ተደስተናል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የአደረጃጀትና የአሠራር ማሻሻያ ጥናቱ ተግባራዊ ኾኖ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሰንገው አላንቀሳቅስ ያሏት ሙስናና ጎጠኝነት ተወግደው ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡት ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ለማዋል ያስችላል ተብሎ በጉጉት ሲጠበቅ በጥናቱ ያልተደሰቱ የተወሰኑ ግለሰቦች ባቀረቡት ቅሬታ ጥናቱ ተግባራዊ ከመኾን ታግዶ እንደገና በዐዲስ መልክ እንዲታይ መወሰኑን በከፍተኛ ድንጋጤ ነው የሰማነው፡፡
ይህ ለቤተ ክርስቲያን ዓበይት የአስተዳደር ችግሮች ኹነኛ መድኅን ይኾናል ተብሎ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የታመነበት መመሪያ በተግባር ተፈትኖ በአፈጻጸም ያስከተለው ችግር ሳይመረመር ከወዲሁ በድጋሚ እንዲታይ ብሎ ማዘግየት እስካሁን የጠፋው ጥፋት አልበቃ ብሎ በሙስናው ሥራ ለተሠማሩት ወገኖች ተጨማሪ ዕድልና ጊዜ መስጠት ወይም እነሱ በሚፈልጉት ዓይነትና ሁኔታ ተቃኝቶ እንዲስተካከል ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም፡፡ 
በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ተንሠራፍቶ የቆየው ሙስናና ብልሹ አሠራር ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ለነገ ሊባል የማይችል ባስቸኳይ ርምጃ መወሰድ ያለበት ስለኾነ የቤተ ክርስቲያቱን ሥር የሰደደና የተከማቸ ችግር ያስወግዳል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትና የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል በኾነው በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቀው ጥናት ባስቸኳይ ተግባራዊ እንዲደረግ በአጽንኦት እንጠይቃለን፡፡
ቅዱስ አባታችን፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፡-የተቋማዊ ለውጡ ጥናት በቅዱስ ሲኖዶስ ተቀባይነት ማግኘቱ በራሱ ከፍተኛ ውጤት ቢኾንም አስፈላጊው የአፈጻጸም ስልትና በቁርጠኝነት ሥራ ላይ ሊያውል የሚችል ቅን ታታሪ ታማኝ ተግዳሮቶችን በከፍተኛ ጽናት መቋቋም የሚችል የሰው ኃይል ካልተመደበለት ብልጣብልጦቹ እጅ ወድቆ የታሰበውን ውጤት ሳያስገኝ ሊከሽፍ የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው፡፡ 
ስለዚህ ተቋማዊ ለውጡን በተሟላና በተሳካ ሁኔታ ሥራ ላይ ለማዋልና ዘለቄታማነቱን ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ፡ 
  1. በጥናቱ ላይ ጥያቄ ያለው ግለሰብ ወይም ቡድን ቢኖር ጥያቄውን በዝርዝር አቅርቦ በጥናት ቡድኑ ታይቶ በቅዱስ ሲኖዶስ የሚታመንበት ነገር ካለ አስፈላጊው ማሻሻያ ከሚደረግበት በስተቀር በጉጉት የምንጠብቀው የጥናት ውጤት ቢቻል ለማስቆም ካልተቻለም ለማዘግየት እንደገና በአዲስ መልክ እንዲታይ እየተደረገ ያለው አካሔድ ቆሞ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ልዕልና ተጠብቆ በውሳኔው መሠረት እንዲፈጸም እንዲደረግ፤
  2. የተጠናውን የአሠራርና የአደረጃጀት ጥናት የሚገመግም አዲስ ኮሚቴ በተመለከተም ጥናቱን ሊያዳብር በሚችል መልኩ በፍጥነት ሠርተው ያቀርባሉ ብሎ ለማሰብ ከኮሚቴው አባላት መካከል ከአሁን ቀደም በሀገረ ስብከቱም ኾነ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ውስጥ በተመሳሳይ ችግር ተጠቃሽ የሚኾኑ ሰዎች መካተታቸው ያሳሰበን በመኾኑ እንደገና እንዲታይልን እንዲደረግ
  3. ተቋማዊ ለውጡን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ያስተላለፈው ውሳኔ እንዳይፈጸም በሚያውኩና በሚቃወሙ ላይ ሌሎችን ሊያስተምር የሚችል ጥብቅ የሥነ ሥርዓት ርምጃ እንዲወሰድ እንደረግ፤
  4. ከቅን የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናትና ሠራተኞች፣ ከሰንበት ት/ቤት እንዲሁም ከምእመናን የተውጣጣ ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ የሆነ የተቋማዊ ለውጥ አስፈጸሚ አካል እንዲቋቋም
  5. ከዚህ ቀደም በቤተክርስቲያን ሀብትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ምዝበራ የፈጸሙ ሁሉ ጉዳያቸው ተጣርቶ ተገቢው ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድልን፣
  6. ስለጎጠኝነትና ሙስና አስከፊነት የሥልጠናና ትምህርት መርሐ ግብር ቀርጾ ተግባራዊ እንዲደረግ፣
  7. ከሙስና የጸዱትንና የላቀ መልካም ተግባር የሚፈጸሙትን አገልጋዮች በመሸለም እንዲበረታቱ እንዲደረግ፣
  8. ቤተ ክርስቲያኒቱ ከወቅታዊ ሁኔታዎች አንጻር ራሷን እየፈተሸች፣ ችግሮቿን እየለየች መፍትሔ በማስቀመጥ ተግባራዊ ርምጃ ለመውሰድ የሚያስችላት የጥናትና ምርምር ማዕከል እንዲቋቋም እንዲደረግ፣
  9. ከመንግሥት አሠራር ልምድ በመቅሰም በስፋት የተንሰራፋውን የሙስና ተግባር መቋቋም ይቻል ዘንድ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና አካል ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እንዲቋቋም እንዲደረግ፤
በቅድስት ቤተክርስቲያናቸን ስም አበከረን እንጠይቃለን፡፡ 
ቅዱስ አባታችን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፡-ቤተ ክርስቲያናችን የደረሰባትን የበጎች/የተከታዮች ስርቆትና ብልሹ አሠራር ለማስወገድ ብቻ ሳሆን ለህልውናዋ ስትል ከችግሩ ለመላቀቅ ጨክና (በቁርጠኝነት) ይህን መሰል ድርጊት በሚፈጽሙ ስውር የቤተ ክርስቲያን ጠላቶችና የመናፍቃን ጉዳይ አስፈጻሚ ተላላኪዎች ላይ ዛሬ ነገ ሳትል በጥንቃቄ በተጠና መንገድ ጠንካራና ጠበቅ ያለ ርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀት ይኖርባታል፡፡ 
ሕገ ቤተ ክርስቲያን ሲጣስ ቃለ ዓዋዲው በዘፈቀደ ሲሻር የደጋግ አባቶች አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ እንደዘበት በቸልታ ማለፍ ከክፉ ሰዎች ክፉ ተግባር ባልተናነስ ደረጃ ቤተ ክርስቲያናችንን ጉዳት ላይ እየጣላት እንደኾነ ልናስተውል ይገባል፡፡ ትላንት ርምጃ መውሰድ ሲቻል ባለመወሰዱ ዛሬ መመሪያውን ተግባራዊ ማድረግ እየተቻለ በጥቃቅን ምክንያቶች ተግባራዊ ባለመደረጉ በዚች በዛሬዋ ዕለት እንኳ በቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት ይልቁንም በቅንና እውነተኛ አባቶቻችን ላይ የሚደርሰውን ኢፍትሐዊ ውሳኔ ለማዳን እየቻልን ያለማዳናቸን በታሪክና በትውልድ ይልቁንም በእግዚአብሔር ዘንድ ተወቃሽ ከመሆን ለመዳን አዲሱን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ እንረባረብ፡፡ 
ቅዱስ አባታችን፡- በመጨረሻም ያቀረብነው ጥያቄ በጥሞና ታይቶ ምላሽ የሚሰጥበት ቀነ ቀጠሮ እንዲያዝልን በታላቅ መንፈሳዊ ትሕትና እናሳስባለን፡፡
የቅዱስ አባታችንንና የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ረድኤትና በረከት ይደርብን!  
ወስብሐት ለእግዚአብሔ

ቅዳሜ 4 ጃንዋሪ 2014

ሰበር - ዜና የመስቀል ደመራ በዓል በዓለም ቅርስነት በዩኔስኮ መመዝገቡን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የእንኩዋን አደረሳችሁ በማለት ገለጸች



ቅዳሜ ታኅሳስ 26 2006 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በተዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ እንደተናገሩት የመስቀል ደመራ በዓል በአለም ቅርስነት በመመዝገቡ እንኩዋን ደስ አለችሁ ካሉ በኋላ በቀጣይም የጥምቀት በዓል ፤ የቅዱስ ያሬድ ዜማ ፤ ቅኔ፤ እና የ መጻሕፍት ትርጓሜ  በአለም ቅርስነት እነዲመዘገቡ ማስተዋወቅ ና በትጋትና በጥራት መስራት አለብን ብለዋል ቅዱስ ፓትርያርኩ  ለዚህ ታላቅ ውጤት ለመብቃት በባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቅርስና ጥበቃ ባለስልጣናት ቢሮን ተወካይ፤ የአዲስ አበባን አድባራትና ገዳማትን አመስግነዋል በተዘጋጀው የእንኩን ደስ አላችሁ በዓል ላይ ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ፤ካህናት ምእመናን ተገኙ ሲሆን የገነተ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ደብር ሊቃውንት ወረብ  አቅርበዋል፡፡ በተቸማሪም ደብሩ ለተገኙት ተሳታፊዎች  የቁርስ መስተንግዶ አቅርቦአል፡፡

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...