ጥምቀት
በጽርዕ ቋንቋ ኤጲፋኒያ በግእዝ አስተርዮ በአማርኛ መገለጥ ይባላል፡፡ ቃሉ በቀጥታ ሲተረጎም በውኃ ውስጥ ገብቶ
መውጣት፣ መነከር፣ መዘፈቅ፣ መጥለቅ ማለት ነው፡፡ ጥምቀት ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን (ምሥጢረ ጥምቀት፣
ምሥጢረ ሜሮን፣ ምሥጢረ ቁርባን፣ ምሥጢረ ንስሐ፣ ምሥጢረ ክህነት፣ ምሥጢረ ተክሊል፣ ምሥጢረ ቀንዲል) አንዱና
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ በዮሐ. 3፥5 ላይ ‹‹እውነት እውነት እልሀለሁ፤
ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡›› ብሎ እንደተናገረው
ከውኃና ከመንፈስ ተወልደን የሥላሴን ልጅነት የምናገኝበት መንግሥተ ሰማያት የምንገባበት ኃጢአታችን የሚደመሰስበት
ድኅነትን የምናገኝበት ዐቢይ ምሥጢር ነው፡፡ ጥምቀት በምሥጢረ ሥላሴና በምሥጢረ ሥጋዌ አምኖ ለሚፈጽመው ሰው ሁሉ
ለኃጢአት መደምሰሻ ከሥላሴ የጸጋ ልጅነት ለመቀበልና የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የተሰጠ ልዩ የሕይወት
መንገድ ነው፡፡
የጥምቀት አመጣጥ
የምሥጢረ
ጥምቀት መስራች ራሱ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ነገር ግን ከጌታችን ጥምቀት በፊት አይሁድ
ለመንጻትና ለኃጢአት ሥርየት (ይቅርታ) የሚጠመቁት ጥምቀት ነበራቸው፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር በረድኤት የሚገለጥባቸው
የተቀደሱ ዕለታትና ቦታዎች ሁሉ ሰውነትንና ልብስን ማጠብ የእግዚአብሔር ቤት ማገልገያ የሆኑ ዕቃዎችን ሁሉ ማጠብ
ማንጻት ሥርዓትና ልማድ ነበር፡፡ የእግዚአብሔርም ፈቃድ ያለበት አሠራር ነበር፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቤት
ከመቅረባቸውና ለተቀደሰው አገልግሎት ከመግባታቸው አስቀድመው እግሮቻቸውንና እጆቻቸውን የመታጠብ ግዴታም ነበራቸው፡፡
ሰውነታቸውን ከአፍአዊ (ከውጫዊ) እድፍ በማጠብና ንጹሕ በማድረግ በባሕርይ ንጹሕና ቅዱስ በሆነው አምላክ ፊት
ውስጣዊ ሕይወትን ንጹሕ አድርጎ የመቅረብን ሥርዓትና ምሥጢር የሚያመለክት ልማድ ነበር፡፡
‹‹አሮንንና ልጆቹን ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ታቀርባቸዋለህ፤ በውኃም ታጥባቸዋለህ›› /ዘፀ. 29፥4/
‹‹ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አቀረበ፣ በውኃም አጠባቸው፡፡›› /ዘሌ. 8፥6/
በብሉይ ኪዳን ዘመን የጥምቀት ምሳሌዎች
- አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ መልከጼዴቅ መሄዱ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም የምእመናን መልከጼዴቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ናቸው፡፡ /ዘፍ. 14፥17/
- ኢዮብ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ተፈውሷል፡፡ ይህም ምእመናን ተጠምቀው ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ የመፈወሳቸው ምሳሌ ነው፡፡
- ንዕማን ሶርያዊ ተጠምቆ ከለምጽ ድኗል፡፡ 2ነገ. 5፥14 ይኸውም ምእመናን ተጠምቀው ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ የመዳናቸው ምሳሌ ነው፡፡
- የኖኅ
መርከብ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ዘፍ. 6፥13 ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍሳት
በውኃ የዳኑባትን መርከብ ሲሠራ በኖኅ ዘመን የእግዚአብሔር ትዕግሥት በዘገየ ጊዜ ቀድሞ ክደውት ለነበሩት
ሰበከላቸው፡፡ አሁንም እኛን በዚያው አምሳል በጥምቀት ያድነናል ሥጋን ከዕድፍ በመታጠብ አይደለም ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ በመነሣቱ በእግዚአብሔር እንድናምን መልካም ግብርን ያስተምረን ዘንድ ነው እንጂ፡፡›› /1ጴጥ. 3፥20/
- እስራኤል
በደመና ተጋርደው ቀይ ባሕርን መሻገራቸው የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ /ዘፀ. 14፥15/ ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ
ጳውሎስ ‹‹አባቶቻችን ሁሉ ደመና እንደ ጋረዳቸው ሁሉም በባሕር መካከል አልፈው እንደ ሄዱ ልታውቁ እወዳለሁ፡፡
ሁሉንም ሙሴ በደመናና በባሕር አጠመቃቸው›› /1ቆሮ. 10፥1/
- ለአብርሃም
ሕግ ሆኖ የተሰጠው ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም ከአረጀ በኋላ ቢገረዝም ልጆቹ ግን በተወለዱ
በስምንተኛው ቀን እንዲገረዙ እግዚአብሔር አዞ ነበር /ዘፍ. 17፥9/ ‹‹በሰው እጅ የአልተደረገ መገረዝን በእርሱ
ሆናችሁ ተገረዛችሁ፡፡ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር
ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር ተነሥታችኋል፡፡›› /ቈላ. 2፥11/
ጌታችን ለምን ተጠመቀ?
ሀ. ለትሕትና ለትምህርት ለአርአያ /ዮሐ. 13፥1-17/
ለ. በዮርዳኖስ ተጥሎ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤ ሊደመስስ /ቈላ. 2፥14/
ሐ. የሦስትነትን ምሥጢር ይገልጥልን ዘንድ /ማቴ. 3፥16/
መ. በእርሱ ጥምቀት የእኛን ጥምቀት ለመባረክ
ጌታችን መች ተጠመቀ?
ጌታችን
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በ5531 ዓመተ ዓለም ዘመነ ሉቃስ ማክሰኞ ጥር 11 ቀን ከሌሊቱ
በ10ኛው ሰዓት ነበር፡፡ ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 19 በተጠመቀም ጊዜ ዕድሜው 30 ዓመት ከ13 ቀን ነበር፡፡ /ሉቃ.
3፥23/
ጌታችን ስለምን በ30 ዓመት ተጠመቀ?
በብሉይ
ኪዳን ሥርዓትና ልማድ ካህናት ለቤተ እግዚአብሔር ተልእኮ እና መንፈሳውያን አገልግሎቶች ከ30 ዓመት ዕድሜ በፊት
አደባባይ አይወጡም ነበር፡፡ እጅግ አስፈላጊ እንኳ ቢሆን ከ20 እና 25 ዓመት አስቀድሞ ለአገልግሎት መሰየም ልማድ
አልነበረም፡፡ የቤተ እግዚአብሔር አገልጋዮች በዕድሜና በዕውቀት የበሰሉ፣ በጠባይና በሥራ ልምድ የተፈተኑ
ተልዕኳቸውን በብቃት ለመወጣት በተገልጋዩ ሕዝብ ዘንድ የተመሰከረላቸው መሆን ነበረባቸው፡፡ /ዘፀ. 4፥3፤1ዜና
መዋ. 23፥24፤ 1ጢሞ. 3፥6-10/ ያንን ሥርዓት ለመፈጸም ጌታችን የተጠመቀውና ለትምህርተ ወንጌል የተገለጠው
በ30 ዓመቱ ነበር፡፡ ዮሐንስ መጥምቅም የጌታን መምጣት ለማወጅ በዮርዳኖስ ይሁዳ ምድረ በዳዎች ወጥቶ የታየው ከ30
ዓመት ዕድሜው በኋላ ነው፡፡ ሌላው ዐቢይ ምክንያት የሰው ሁሉ መጀመሪያ አዳም የ30 ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ተፈጥሮ
በ40ኛ ቀን ተሰጥቶት ኋላም በኃጢአት ምክንያት ያስወሰደውን ልጅነት ለማስመለስ ነው፡፡ ክርስቶስ የተጠመቀው ክብር
ሽቶ ሳይሆን የአብ የባሕርይ ልጅነቱን (የባሕርይ አምላክነቱን) ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ለማስመስከር፣ ውኃውን
ለመቀደስ፣ የአዳምን ልጆች የእዳ ደብዳቤ ለመደምሰስና በስህተት የጠፋውን የልጅነት ክብር ለመመለስ ነው፡፡ ጌታ
ተጠምቆ ከውኃው ከወጣ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ በማረፍ አብ በደመና ‹‹ይህ ልጄ
ነው›› ብሎ ሲመሰክርለት ምሥጢረ ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት በጉልህ ተረጋግጧል፡፡ /ማቴ. 3፥16/
ጌታችን በዮሐንስ እጅ ለምን ተጠመቀ?
ጌታችን
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ሲሆን በአገልጋዩ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ በፍጹም ትሕትና
ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ ይህንንም ያደረገልን አብነት ሊሆነን ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ቅዱስ ዮሐንስን
‹‹መጥተህ አጥምቀኝ ›› ብሎት ቢሆን ኖሮ ነገ ነገሥታቱና መኳንንቱ ካህናቱን መጥታችሁ አጥምቁን ባሉ ነበር ስለዚህ
እንዲህ እንዳይሆን ነው፡፡ ጌታችን ‹‹ጌታ ስሆን በባርያዬ እጅ እንደተጠመቅሁ እናንተም ወደ ቤተክርስቲያን ሄዳችሁ
በካህናት እጅ ተጠመቁ›› ሲል ነው፡፡
ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀው ልጅነትን የምታሰጥ ጥምቀትን ባርኮ ቀድሶ ሊሰጠን እንጂ ክብር እንዲሆነው አይደለም፡፡ ምክንያቱም፡- እርሱ እከብር አይል ክቡር እጸድቅ አይል ጻድቅ ነውና፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን በማን ስም አጠመቀው?
ጌታችን
ዮሐንስን አጥምቀኝ ባለው ጊዜ ‹‹ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለሁ አንተን በማን ስም ላጥምቅህ? በአብ ስም
እንዳላጠምቅህ አብ አባትህ ባንተ ሕልው ነው በወልድ ስም እንዳላጠምቅህ ወልድ አንተ ነህ በመንፈስ ቅዱስ ስም
እንዳላጠምቅህ መንፈስ ቅዱስ ሕይወትህ ባንተ ሕልው ነው ታዲያ በማን ስም ላጥምቅህ?›› ብሎ ቢጠይቀው ጌታም
‹‹እንደ መልከጼዴቅ ሥርዓት አንተ የዓለም ካህን ብርሃንን የምትገልጥ የአብ የባሕርይ ልጅ ሆይ ይቅር በለኝ››
ብለህ አጥምቀኝ አለው፡፡
ዮሐንስ ጌታን ሲያጠምቀው እጁን ለምን አልጫነበትም?
- ዮሐንስ በጥምቀት አከበረው /ልዕልና ሰጠው/ እንዳይባል፡፡
- መለኮትን በእጅ መንካት ስለማይቻል
ጌታችን ጥምቀቱን ለምን በዮርዳኖስ አደረገው?
በኢየሩሳሌም
አካባቢ ብዙ ወንዞች ኩሬዎችና ሐይቆች መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ ጌታ ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ያደረገው ስለዚሁ
አስቀድሞ የተነገረውን ትንቢት መፈጸሙን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ‹‹ባሕር አይታ ሸሸች ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ››
/መዝ. 113፥3/ ከዚህም ጋር ከላይ ምንጩ አንድ የሆነው ዮርዳኖስ ዝቅ ብሎ በደሴት ተከፍሎ እንደገና እንደሚገናኝ
በግዝረት በቁልፈት (በመገዘርና ባለመገዘር) ተለያይተው የነበሩ ሕዝብና አሕዛብ መላው የአዳም ልጆች በጌታችን
ጥምቀት አንድ መሆናቸውን የሚገልጽ ትርጉም አለው፡፡ እስራኤል ዮርዳኖስን ተሻግረው ምደረ ርስት ገብተዋል፡፡ ያመኑ
የተጠመቁ ምዕመናንም በጥምቀት ገነት መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ፡፡ ሌላው በዮርዳኖስ ተጥሎ የነበረውን የዕዳ
ደብዳቤ ይደመስስልን ዘንድ /ቈላ. 2፥14/
ጌታችን ለምን በሌሊት ተጠመቀ?
በኃጢአት ጨለማ ስለነበረ ሕዝብ የጽድቅ ብርሃን እንዲወጣለትና በጨለማ የሚመስል ኦሪት ይኖር ስለነበረ ለሕዝብ ብርሃን የሆነ ወንጌል መገለጡን ለማሳየት ነው፡፡ ኢሳ. 9፥2
- አንድም ጌታ ልደቱ፣ ጥምቀቱ፣ ትንሣኤው እንዲሁም ምጽአቱ በሌሊት ነው፡፡ ይኽም የሆነበት ምክንያት፡- ሌሊቱን ተከትሎ የሚመጣው ብርሃን በመሆኑ ከሞት ወደ ሕይወት ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሲኦል ወደ ገነት የመሸጋገራችን ምሳሌ ነው፡፡
- አንድም መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል የሚወርድ ነውና በጌታ ላይ የወረደው ርግብ እንጂ መንፈስ ቅዱስ አይደለም ባሉ ነበር፡፡ በሌሊት ርግብ የለም ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ይታወቅ ዘንድ፡፡
መንፈስ ቅዱስ ለምን ጌታ ከውኃ ከወጣ በኋላ ወረደ?
ሀ. ዮሐንስን ያከብሩት ነበርና መንፈስ ቅዱስ የወረደው ለዮሐንስ እንጂ ለጌታ አይደለም ይሉ ነበርና ምክንያቱን ጌታ ውኃ ውስጥ እያለ ከዮሐንስ አልተለየም ነበርና፡፡
ለ. ውኃን የሚባርክ መልአክ እንዳለ ያውቁ ነበርና ውኃውን ለመባረክ አንጂ ለጌታ አይደለም እንዳይባል፡፡
ሐ. ማረፊያ ያጣች ርግብ በባሕር ስትበር አረፈችበት ባሉ ነበርና ሐሳባቸውን በሙሉ ያጠፋ ዘንድ ከውኃ ውስጥ ከወጣ በኋላ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወረደ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመንቀሉ ክቡር
ምንጭ ኆኅተ ብርሀን ሰ/ት/ቤት