ዓርብ 10 ኦክቶበር 2014

ማኅሌተ ጽጌ (Part One

 
 
ማኅሌተ ጽጌ፤ ምንጩ ትርጉሙ መልእክቱ 
           ይህ ድርሰት በማንኛውም ጊዜ የሚጸለይ ቢሆንም በተለየ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውለው ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ቀን ድረስ ባለው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የስደት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ወቅት በየሳምንቱ እሑድ ሌሊት በሙሉ የእመቤታችንን ከልጇ ጋር ወደ ግብፅ መሰደድና መንከራተት እያሰቡ የሚደረስ ምሥጋናና ጸሎት ነው፡፡
             በሀገራችን የመስከረምና የጥቅምት ወራት የአበባ ወራት /ዘመነ ጽጌ/ ናቸው፡፡ ይህም ወቅት ተራሮች በአበባ የሚያጌጡበትና ለዓይን ማራኪ የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህም ዘመን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ስለ ልብስስ ስለምን ትጨነቃላችሁ) የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፡፡ አይደክሙም፣ አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞንስ ስንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም፡፡ እግዚአብሔርን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጐደላችሁ እናንተንማ ይልቁን እንዴት እንግዲህ ምን እንበላለን ምንስ እንጠጣለን) ምንስ እንለብሳለን) ብላችሁ አትጨነቁ ...» /ማቴ.5÷28-33/ በማለት የተናገረውን ቃል በማሰብ መጨነቅ የሚገባን መንግሥተ ሰማያት ለመግባት እንጂ በዚህ ዓለም ስላለው ነገር እንዳልሆነ ተራሮችን በአበባ ያለበሰ አምላክ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረንን እኛን ለኑሮ የሚያስፈልገንን ምግብና ልብስ እንደማይነሳን እያሰብን የምንዘክርበት ወቅት ነው፡፡
                እንዲሁም ክቡር ዳዊት «ተዘከር እግዚኦ ከመ መሬት ንሕነ ወሰብእሰ ከመ ሳዕር መዋዕሊሁ ወከመ ጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ፤ አቤቱ እኛ አፈር እንደሆን አስብ ሰውስ ዘመኑ እንደሣር ነው እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋልና» /መዝ.12÷14-16/ በማለት እንደ ተናገረው የሰው ሕይወት በሣር ይመሰላል፡፡ ሣር አድጐ አብቦ ከዚያ በኋላ ይደርቅና በነፋስ አማካኝነት የረገፈው ሣር እየተነሣ የነበረበት ቦታ ስንኳ እስከማይታወቅ ድረስ ይሆናል፡፡ ሰውም ከአደገ በኋላ በሕማም ፀሐይነት ይደርቅና በሞት ነፋስነት ይወሰዳል፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ መቃብር ሲወርድ የነበረበት ቦታ ይዘነጋል፡፡ ስለዚህ ዘመነ ጽጌ ሰው ዘመኑ እንደ አበባ በቶሎ የሚረግፍ መሆኑን በማሰብ ይህ ዘመን ሳያልፍ መልካም ሥራ ለመሥራት ትንሣኤ ኅሊና የሚነሣበት ጊዜ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለዘመነ ጽጌ የሠራው ድጓም ይህንኑ የሰውን ዘመን አጭርነት የሕይወቱን ኢምንትነት በዚህ ሕላዌ የተፈጠረ ሰው በዚህ ዓለም ክፉ ሥራ መሥራት እንደሌለበት ሁልጊዜ በተዘክሮተ ሞት እንዲኖር የሚያስረዳ ነው፡፡
                     በዘመነ ጽጌ ቅዱስ ያሬድ ከደረሰው ድጓ በተጨማሪ ከላይ እንደተጠቀሰው 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣ አባ ጽጌ ድንግል ከዚሁ ዘመን ጋር የተያያዘ ድርሰት ደርሷል፡፡ ይህ ድርሰት በግጥም መልክ የተደረሰ በአብዛኛው አምስት ስንኞች ያሉት ሲሆን ብዛቱም 15 ያክል ነው፡፡ ይህም ድርሰት «ማኅሌተ ጽጌ» በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ፍሬ ከአበባ አበባም ከፍሬ እንደሚገኘው ሁሉ ማኅሌተ ጽጌም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጇን መድኃኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአበባና በፍሬ እየመሰለ የሚያስረዳ ድርሰት ነው፡፡ እርሷን በአበባ ሲመስል ልጇን በፍሬ እርሷን በፍሬ ሲመስል ደግሞ ልጇን በአበባ እየመሰለ ይናገራል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ «ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ ወየዓርግ ጽጌ እምጉንዱ፤ ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፤ ከሥሩም ቁጥቋጦ ያፈራል»  /ኢሳ.11÷1/ ብሎ ከእሴይ ዘር የምትገኘውን እመቤታችንን በበትር ከርሷ የሚገኘውን ክርስቶስን ደግሞ በጽጌ መስሎ ትንቢቱን ተናግሯል፡፡ አባ ጽጌ ድንግልም ድርሰቱን በዚሁ አንጻር በመቀመር እያንዳንዱን መልክዕ እመቤታችንንና ልጇን አስተባብሮ በጽጌና በፍሬ በመመሰል የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ በምሥጢር በታሪክ፣ በጸሎትና በመሳሰለው መልክ ድንቅ በሆነና በተዋበ ሁኔታ አዋሕዶ ደርሶታል፡፡
                                                                                                                  
                     እመቤታችን ጣዕሟንና ፍቅሯን እንዲሁም ምስጋናዋን ሲናፍቁ የነበሩትን ቅዱስ ኤፍሬምንና አባ ሕርያቆስን ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን እንደገለጸችላቸው ለፍቅሯ ሲሳሳ ለነበረው ለአባ ጽጌ ድንግል ደግሞ ይህንን ማኅሌተ ጽጌን እንዲደርስ አድርጋዋለች፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ማኅሌተ ጽጌ በመልክዕ አደራረስ ሥርዓት የተደረሰ ሲሆን ይህንንም ለመመልከት እንዲያመች በሚከተሉት ክፍሎች ከፋፍሎ ማቅረብ ይቻላል፡፡
1. ጸሎት
            በዚህ አገባብ ጸሎት ስንል በተለየ ሁኔታ ጸሎትነቱ የጐላውን ለማየት እንጂ ድርሰቱ በሙሉ ጸሎት ነው፡፡ ሌሎቹንም እንዲሁ ታሪክ፣ ተግሳጽ፣ ምሥጢር ተብለው መከፈላቸው በበዛውና በጐላው ለመግለጽ ነው እንጂ ሁሉም በሁሉ አለ፡፡ በጸሎትነታቸው ጐልተው ከሚታዩት ውስጥ የተወሰኑትን እንመለከታለን፡፡
1.1.  አንብርኒ ማርያም ውስተ ልብኪ ከመ ሕልቀት፣
ወከመ ማዕተብ ፁርኒ በመዝራዕትኪ ልዕልት፣
በእንተ ርስሐትየሰ ኢትመንንኒ ንግሥት፣
እስመ ወሀብኩ ንብረትየ ለፍቅርኪ ሞት፣
ዘአሰገርዎሙ ለሰማዕት በጽጌሁ ሕይወት፡፡
              ጠቢቡ ሰሎሞን «የምእመናንንና የክርስቶስን ነገር በምሥጢር በተናገረበት በመኃልይ መጽሐፉ «እንደ ማኅተም በልብህ እንደ ማኅተም በክንድህ አኑረኝ» /መኃ.9÷6/ ይላል፡፡ ይኸውም የምእመናንንና የክርስቶስን አንድነት የሚገልጽ ነው፡፡ «አንብርኒ ማርያም ውስተ ልብኪ ከመ ሕልቀት፤ ወከመ ማዕተብ ፁርኒ በመዝራዕትኪ ልዕልት» ማለቱ እመቤታችንን እንደ


ማኅተም በልብሽ አኑሪኝ በማለት በእናትነትሽ፣ በአማላጅነትሽ አትርሽኝ ካለ በኋላ «በእንተ ርስሐትየሰ ኢትመንኒ ንግሥት» ይላል፡፡ ይኸም ማለት አትርሽኝ በልብሽ አኑሪኝ ብዬ የምለምንሽ አንቺ እንዳትረሽኝ የሚያደርግ መልካም ሥራ ኖሮኝ አይደለም፡፡ ስለዚህ በሰውነቴ ክፋት ምክንያት በኃጢ አቴና በወራዳነቴ ምክንያት እኔን ከማሰብ ከልቡናሽ አታውጪኝ በማለት እመቤታችን በርኅሩኅ ልቧ «መሐር ወልድየ ወተዘከር ኪዳንየ» እያለች እንድታዘክረን የሚያሳስብ ጸሎት ነው፡፡
ሶበ አተቦ ለማይ በቅዳሴኪ እንዘ ይጼሊ፣
ረሰዮ ኅብስተ ጽጌ ሃይማኖት ሳሙኤል ዘሐቅለ ዋሊ፣
ምሕረተ ወፍትሐ ለተአምርኪ አኀሊ፣
ሥረዪ ኃጢአትየ ወእጸብየ አቅልሊ፣
እስመ ኩሎ ገቢረ ማርያም ትክሊ፡፡
            አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ቅዳሴ ማርያምን እየደገሙ ውኃው በተአምራት ኅብስት ይሆንላቸው ነበር፡፡ ይህን ተአምር ከአደነቀ በኋላ «ማርያም ሆይ ሁሉን ማድረግ ትችያለሽና ኃጢአቴን አስተስርይልኝ» ይላል፡፡ ጌታችን «እውነት እላችኋለሁ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም» /ማቴ.17÷1/ በማለት ላመነ የሚሣነው ነገር እንደሌለ ተናግሯል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መልአኩ «ትጸንሻለሽ፣ ትወልጃለሽ ...» ብሎ ባበሠራት ጊዜ ይህ እንደምን ይሆንልኛልብላ ስትጠይቅ «ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም» ሲላት በፍጹም እምነት ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ እንደቃልህ ይሁልኝ» በማለት የተቀበለች ናት፡፡ ይህንንም ቅድስት ኤልሳቤጥ መንፈስ ቅዱስን ተመልታ «ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና የታመነች ብፅዕት ናት» /ሉቃ.1÷453 ብላ መስክራለች፡፡ ላመኑ ሁሉ የሚቻል ከሆነ እመቤታችን ግን ቅዱሳን ሁሉ የሚማጸኑትን አምላክ በሥጋ ወልዳ ያስገኘች ስለሆነች ለእርሷ የሚሳናት ነገር የለም፡፡ ስለዚህም ነው ላንቺ የሚሳንሽ ነገር የለምና ኃጢአቴን አስተስርዪልኝ፣ የከበደኝን ሁሉ አቅልይልኝ በማለት የለመነው፡፡

ረቡዕ 8 ኦክቶበር 2014

የጅማ ሀገረ ስብከት ሁለገብ ዘመናዊ ሕንፃ ተመረቀ


አትም ኢሜይል
መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም.
እንዳለ ደምስስ
jima 2007 3የጅማ ሀገረ ስብከት ያስገነባው ባለ 5 ፎቅ ሁለገብ ዘመናዊ ሕንፃ መስከረም 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በቅዱስ ፓትርያርኩና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንት ተመረቀ፡፡

jima 2007ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የልዩ ልዩ መምሪያ ሓላፊዎችና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ክፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በመሆን የጅማ ሀገረ ስብከት ከሃያ ስምንት ሚሊዮን አምስት መቶ አራት ሺሕ ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባውን ባለ አምስት ፎቅ ዘመናዊ ሁለገብ ሕንፃ ባርከው ሲመርቁ በሰጡት ቃለ ምእዳን “ይህ ሁለገብ ዘመናዊ ሕንፃ በጣም የሚያስደንቅና ለቤተ ክርስቲያናችን ተጨማሪ ሀብት መሆን የቻለ ነው፡፡ ለሌሎች ሀገረ ስብከቶችም ታላቅ ምሳሌና በአርአያነቱም ተጠቃሽ የሚሆን ነው” ብለዋል፡፡

የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ባቀረቡት ሪፖርትም በጅማ ሀገረ ስብከት 308 አብያተ ክርስቲያናት እንደሚገኙና፤ የዚህ ሕንፃ መገንባት ዋነኛ ዓላማ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አብያተ ክርስቲያናት በካህናትና በበጀት እጥረት jima 2007 2ምክንያት የተቸገሩ በመሆናቸው ሕንፃው ተከራይቶ በሚያስገኘው ገቢ እነዚህን አብያተ ክርስቲያናት በመደገፍ አገልግሎት እንዳይቋረጥ ለማስቻል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ዝርዝሩንእንደደረሰልን እናቀርባለን፡፡


አርሴማ

ዐጽሟ ያረፈበት አርመን የሚገኘው ቤተ ክርስቲያን
ቅድስት አርሴማ በ290 ዓም በአርመን በሰማዕትነት ያረፈች ወጣት ክርስቲያን ሰማዕት ናት፡፡ ትውልዷ ሮም ሲሆን ሰማዕትነት የተቀበለችው አርመን ነው፡፡ እኛ አርሴማ ስንላት እነርሱ Saint Hripsime ይሏታል፡፡ ታሪኳን የፈለገ ሰው በዚህ ስሟ ጎጉል ላይ ቢፈልግ በቀላሉ ያገኘዋል፡፡ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ መስከረም 29 ቀን ወይም ኦክቶበር 9 ሰማዕትነት የተቀበለችበትን ቀን ያከብራሉ፡፡ የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን በስሟ የተሠራውም አርመን ኤችሚዚን ውስጥ በ395 ዓም ነው፡፡ ይህ የአርሴማ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ላይ ሳይፈርሱ ከኖሩት እጅግ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዱ ነው፡፡


የዚህች ወጣት ሰማዕት ታሪክ በስንክሳር በመስከረም 29 ቀን ተጽፏል፡፡ በሀገራችን ገድላቸው ከተተረጎመላቸው የውጭ ቅዱሳን አንዷ አርሴማ ናት፡፡ የዚህ ምክንያቱ የታወቀ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ አርመን ከአርመንም ወደ ኢትዮጵያ የሚሄዱና የሚመጡ ቅዱሳን ነበሩ፡፡ በ10ኛው መክዘ አካባቢ በአርመን የደረሰውን የፋርሶችን ወረራ በመሸሽ አያሌ አርመናውያን ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውንና ዛሬ ሐይቅ እስጢፋኖስ በተባለው ቦታ መሥፈራቸውን የአርመን ታሪክ ይነግረናል፡፡ በአርመንኛ ‹ሐይቅ› ማለትም ገዳም ማለት ነው ይላሉ፡፡
                        በአርመን ቤተ ክርስቲያንዋ የሚታወቀው ሥዕል ይህ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በ13ኛው መክዘ ኢትዮጵያዊው አቡነ ኤዎስጣቴዎስ መጀመሪያ ወደ ግብጽ (1330-32 ዓም)፣ ከዚያም ወደ እሥራኤል በመጨረሻም ወደ አርመን ተጉዘው በዚያ ለአሥራ አራት ዓመታት ከቆዩ በኋላ በ1352 ዓም ዐርፈዋል፡፡ ከእርሳቸው ዕረፍት በኋላም ደቀ መዝሙሮቻቸው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡፡ እነዚህ የተመለሱ የአቡነ ኤዎስጣቴዎስ ደቀ መዛሙርት ብዙ የውጭ ሀገር ቅዱሳት መጻሕፍትን ይዘው በመምጣትና ወደ ግእዝ በመበተርጎም ታላቅ አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡ (ዝርዝር ታሪኩን የፈለገ ‹አራቱ ኃያላንን› መመልከት ነው)፡፡ በጎንደር መንግሥት ጊዜም አቡነ ዮሐንስ የተባሉ ቆሞስ የአቡነ ኤዎስጣቴዎስን ተረፈ ዐጽም ይዘው በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን መጥተው ነበር፡፡ እነዚህ ከወዲህና ከወዲያ የነበሩ ግንኙነቶች ቅድስት አርሴማን በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንድትታወቅ አድርጓታል፡፡ ገድሏም ወደ ግእዝ ሊተረጎም ችሏል፡፡
በአሁኑ ዘመን አርሴማ በኢትዮጵያውያን ወጣቶች ዘንድ ይበልጥ እየታወቀችና እየተከበረች መጥታለች፡፡ ወጣቱ የወጣቷን ሰማዕት አርአያ ማንሣቱ የሚያስመሰግን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ስለ ክርስቶስ ስትል የከፈለችውን ሰማዕትነት፣ ድንግልናን በብጽዐት ለመጠበቅ ስትል የተቀበለችውን መከራ፣ ወጣትነቷ ሳያጓጓት ለእምነት የከፈለችውን ዋጋ፣ በሕይወቷ ሳለች ከሠራችውም በላይ በሰማዕትነቷ ያፈራችውን ፍሬ በማሰብና ከእርሱም በመማር ዘመኑን ከመዋጀት ይልቅ የሰማዕቷን ዝክር ከትዳርና ከፍቅረኞች፣ ከጥራጥሬና ከታሪኳ ጋር ከማይሄዱ ነገሮች ጋር ማገናኘቱ መልካም አይደለም፡፡
                                                    ቅድስት ባርባር
ሌላው ቀርቶ በአሁኑ ጊዜ የቅድስት አርሴማ ሥዕል ነው ተብሎ በስፋት የሚታወቀው ሥዕል በኦርቶዶክስ ሥነ ሥዕል (አይኮኖግራፊ) የቅድስት ባርባራ ሥዕል ነው፡፡ አርመን ኤችሚዚን በሚገኘው መቃብሯ ላይ የሚገኘው ሥዕሏ ከታች የተገለጠው ነው፡፡ ጣና ደሴት ውስጥ በሚገኘው ቤተ ክርስቲያንዋም ኢትዮጵያዊውን ሥዕል ማግኘት ይቻላል፡፡
                በመቃብሯ ላይ የሚገኘው ሥዕል
በአጠቃላይ ቅድስት አርሴማ ታሪኳ በመላው ዓለም ክርስቲያኖች ዘንድ የታወቀ፣ ከንጽሕናና ቅድስና ጋር በእጅጉ የተገናኘ፣ ለወጣት ሰማዕታት ታላቅ አርአያ የሚሆን፣ ንጽሕናን ለመጠበቅ ፈታኝ በሆነበት በዚህ ዘመን ምሳሌ የሚሆን፣ ቀደምት እናቶቻችንና እኅቶቻችን ስለ ክርስቶስ ሲሉ የከፈሉትን ዋጋ የሚያሳይ በመሆኑ በዓሏም በዚህ መንፈስ መከበር ይኖርበታል፡፡

ረቡዕ 1 ኦክቶበር 2014

ማዕተብ: የክርስትናችን ዓርማ የነፍሳችን ሰንደቅ ዓላማ



  • ሦስት ቀለማት ያላቸው ክሮች የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሲኾኑ አንድ ላይ መፈተላቸው ወይም አንድ መኾናቸው ቅድስት ሥላሴ ማለት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በመለኰት በህልውና አንድ አምላክ መኾናቸውን ያመለክታል፡፡ ጥቁሩ፡- ክርስቲያን ስለ ሃይማኖት የሚቀበለው መከራ የሚሸከመው መስቀል፣ ቀዩ፡- በሰማዕትነት ደም የማፍሰስ ሲኾን ቢጫው ደግሞ የክርስቲያን ተስፋ የሃይማኖት ምልክት ነው፡፡
  • ክርስቲያን ለክርስቶስ ታማኝ በመኾኑ በነፍሱ ሞግዚት በቄሱ እጅ ከሕፃንነቱ ጀምሮ የድኅነቱ ምልክት በሚኾን አንገቱ በማዕተበ ክርስትና ይታሰራል፡፡ ማዕተብ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ስለ እኛ ቤዛ ለመኾን የብረት ሀብል /የብረት ገመድ/ በአንገቱ ታስሮ በአይሁድ መጎተቱን ስለሚያስታውሰን ለታማኝነታችንና ለክርስቲያንነታችን ምልክትነቱ ማረጋገጫ ስለኾነ አናፍርበትም፡፡
  • አንዲት ሀገር ነፃና ሉዓላዊ መኾኗ የሚታወቀው ወይም ራሷን የቻለች መንግሥት ያላት ከባዕድ ቀንበር ቅኝ ግዛት ነፃ የወጣች መኾኗ በቀዳሚነት የሚለየው በባንዴራዋ ምልክትነት እንደኾነ እንደዚኹም አንድ ክርስቲያን በክርስቶስ አምኖ በጥምቀት ከዲያብሎስ ቁራኝነት ነፃ መውጣቱ፣ ነፃነት ያለው አማኝ መኾኑ የሚታወቀው በማተቡ ምልክት ነው፡፡
  • አንዳንድ ሰዎች የማዕተብ ሥርዐትን ለመቃወምና ዘመናውያን መስለው ለመታየት ‹‹እምነት በልብ ነው›› ይላሉ፤ ተሳስተዋል! ሃይማኖት የልብ ብቻ አይደለም፤ የጠቅላላው ሕዋሳት ኹሉ ናት፡፡
  • አጋንንት የለከፏቸው ሰዎች ማተብና መስቀል አይወዱም፡፡ የሰፈረባቸው ርኩስ መንፈስ ማተብ እንዲበጥሱ መስቀል እንዲጥሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ማተብ በሰይጣን ዘንድ ከተጠላ በአጋንንት ላለመለከፍ የማዕተቡ መኖር ይጠቅማል ማለት ነው፡፡
* * *
Ethiopian girl wearing a cross shaped tattoo on her foreheadየኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያኖች በአንገታቸው ላይ ክር ያስራሉ፤ ለሕፃኖቻቸውም ክርስትና ሲነሡ ክር ያስሩላቸዋል፡፡ በሕፃናቱም ኾነ በዐዋቂዎቹ ክርስቲያኖች አንገት ላይ የሚታሰረው ክር በግዕዝ ማዕተብ በአማርኛ ማተብ ይባላል፡፡ ቃሉ ወጣው ዐተበ ካለው ግዕዛዊ ግስ ነው፡፡ ዐተበ ፍቺው አመለከተ፣ ባረከ ማለት ነው፤ ማዕተብ ፍቺው ከዚኽ ይወጣል፡፡ ምልክት ማለት ነው፡፡
ለተጠመቁ ክርስቲያኖች የክር ማተብ ለሃይማኖት ምልክትነት ወይም መታወቂያ ከመኾኑ በፊት፣ በብሉይ ኪዳን ዘመን የሃይማኖት አባቶች ከጣዖት አምላኪዎች ተለይተው የሚታወቁበት ምልክት ነበራቸው፡፡ ስለ ታላቁ የሃይማኖት አባት ስለ ጻድቁ አብርሃም የሃይማኖት ማኅተም(ምልክት) ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡- ‹‹ሳይገረዝም በነበረው እምነት ያገኘው የጽድቅ ማኅተም የኾነ የመገረዝን ምልክት ተቀበለ፡፡›› (ሮሜ ፪÷፲፩፤ ዘፍጥ.፲፯÷፱ – ፲፬)
በሥርዐተ ኦሪት ብኵርና ከጥንት ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ገንዘብ ኾኖ ስለሚቆጠር ብኵርና ላለው ኹሉ የአባት በረከት ከሌሎች ይልቅ በይበልጥ ምርቃት ዕጥፍ ድርብ ኾኖ ስለሚሰጠው ብኵርና ይወደዳል፤ ይፈቀራል፡፡ ብኵርና ማቃለል ዋጋ የሌለው ጸጸትን ያስከትል ነበር፡፡ ብኵርና ለዘመነ ሐዲስ ክርስትና ምሳሌ እንደኾነ ይታመናል፡፡ ክርስትናውን ንቆ አቃሎ ዓለምን መስሎ የሚኖር ሰው፣ ለጊዜያዊ መብል ፍለጋ ብኵርናውን በሸጠው በያዕቆብ ወንድም ዔሳው ተመስሏል፤ ‹‹. . .ስለ አንድ መብል በኵርነቱን እንደ ሸጠ እንደ ዔሳው ለዚኽ ዓለም የሚመች ሰው እንዳይኾን ተጠንቀቁ፡፡ ከዚያ በኋላ እንኳ በረከቱን ሊወርስ በወደደ ጊዜ እንደተጣለ ታውቃላችኹና በእንባ ተግቶ ምንም ቢፈልገው ለንስሐ ስፍራ አላገኘምና፡፡›› (ዕብ.፲፪÷፲፮፤ ዘፍጥ. ፳፭÷፳፱ – ፴፬፤ ፳፯÷፴ – ፵)
ብኵርና ለክርስትና ምሳሌ መኾኑ ከላይ ተገልጧል፡፡ ትዕማር ከይሁዳ መንትያ ልጆችን ፀንሳ በምትወልድበት ጊዜ በኵሩ እጆቹን ሲያወጣ አዋላጅቱ ቀይ ፈትል ለምልክት አስራበታለች፡፡ ይህ ምሳሌያዊ ድርጊት በሐዲስ ኪዳን ሲተረጎም ከትዕማር የተወለደው በኵሩ ዛራ ለክርስቲያን ምሳሌ ሲኾን ቀዩ ፈትል ለክርስትናው ምልክት፤ ለማዕተብ ምሳሌ ኾኗል፡፡
አዋላጅቱ ለአጥማቂው ቄስ ምሳሌ ናት፡፡ ትዕማር የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ስትኾን በኋላ የመጣው ፋሬስ በኵሩን ጥሶ ቀድሞ መወለዱና ከቀይ ፈትል አልባ መኾኑ በምሳሌያዊ ትንቢትነት፣ ከቤተ ክርስቲያን በጥምቀት ከተወለዱ በኋላ ክርስትናቸውንና ጥምቀታቸውን ክደው የእውነተኞቹ ክርስቲያኖች ተቃዋሚዎች በመኾን ፊት ከተፈጠረ ጆሮ እንደ ቀንድ ብቅ ያሉ የመናፍቃንና የኢጥሙቃን (ኢአማንያን) ምሳሌ እንደኾኑ ያስረዳል፡፡ (ማቴ.፩÷፫፤ ዘፍጥ.፴፰÷ ፳፮ – ፴)
በዛራ ልማድ ጌታችን ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ እመቤታችን አውራ ጣቱን በክር አስራዋለች፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ለኖሎት ተገልጦ ምልክቱን እንዲህ ሲል ነግሯቸዋል፡- ‹‹ወከመዝ ትእምርቱ ለክሙ ትረክቡ ሕፃነ እሱረ መንኮብያቲኹ፤ ምልክቱ ይህ ነው፡፡ ሕፃኑ አውራ ጣቱን ታስሮ ታገኙታላችኹ፡፡›› (ሉቃ.፪÷፲፪) እመቤታችን አውራ ጣቱን በክር እንዳሰረችው ‹‹ወወለደት ወልደ ዘበኵራ ወአሰርቶ መንኮብያቲኹ፤ የበኵር ልጅዋን ወለደች፤ አውራ ጣቱን አሰረችው፡፡›› ( ሉቃ.፪÷፯፤ የግእዝና አማርኛ ነጠላ ትርጉም አማርኛ ሒዲስ ኪዳን ይመልከቱ)
ድንግል እመቤታችን አውራ ጣት ማሰሯ ለክርስቲያኖች ማዕተብ ማሰር አብነት ኾኗል፡፡ ጣቱን ማሰሯ ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ይኸውም፡- ፩ኛ/ሕፃን ስለኾነ እንዲያጸናው፤ ፪ኛ/ጣቱን ባይታሰር ምትሀት ነው፤ ሰው አልኾነም ለሚሉ መናፍቃን ለክሕደታቸው ምክንያት ባገኙ ነበርና ምክንያት ለማሳጣት፤ ፫ኛ/ቀደም ብለን እንደገለጽነው ልማዳችንን አስቀረብን እንዳይሉ በዛራ ልማድ፤ ፬ኛ/ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በዕለተ ዓርብ ከመስቀል አውርደው እንዲኽ አድርገው ይገንዙሃል ለሰው ቤዛ ለመኾን ልትታሰር መጣኽን፣ ስትል ነው በማለት መምህራነ ቤተ ክርስቲያን በአንድምታ ትርጓሜያቸው ያትታሉ፡፡
* * *
በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ዘንድ ክርስቲያን የኾነ ኹሉ ማተብ የማሰር ልምድ የጀመረው በሃይማኖተ አበው በድርሳነ ያዕቆብ እንደተገለጸው፣ ከልደተ ክርስቶስ በኋላ በእስክንድርያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአምስተኛው ምእት ዓመት ያስተምር በነበረው በሊቀ ጳጳሱ በያዕቆብ ዘእልበረዳኢ ዘመነ ስብከት ነበር፡፡
ያዕቆብ ዘእልበረዳኢ የሶርያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባት ነው፡፡ መምህሩ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳሳት ስለ ተዋሕዶ ሃይማኖት ሲመሰክር በመለካውያን (ልዮናውያንና ንስጥሮሳውያን) ግፊትና ተቃውሞ መከራ ሲቀበል ጽሕሙ ተነጭቶ ጥርሶቹ ረግፈው ስለነበር የተነጨ ጽሕሙን የረገፉ ጥርሶቹን በመሐረም ቋጥሮ ‹‹ዝንቱ ፍሬ ሃይማኖቱ ለእግዚአብሔር፤ ለእግዚአብሔር የምናቀርብለት የሃይማኖት ፍሬ ይህ ነው›› በማለት ለእስክንድርያ በያዕቆብ ዘእልበረዳኢ እጅ ልኮላታል፡፡ እርሱም ስለ ሃይማኖት በደሴተ ጋግራ ታስሮ ሰማዕት ኾኗል፡፡
ደቀ መዝሙሩ ቅዱስ ያዕቆብ አልባሌ መስሎ በሶርያ ብቻ ሳይኾን በእስክንድርያ የሴት ቀሚስ ሳይቀር ለብሶ ሲያስተምር ንስጥሮሳውያን ከጉባኤው እየገቡ ስላስቸገሩት ኦርቶዶክሳውያንን ከመናፍቃን ለመለየት ከእግዚአብሔር ባገኘው ምልክት ጥቁር ቀይ ቢጫ ክሮች አንድ ላይ ፈትሎ በአንገታቸው ላይ ያስርላቸው ጀመር፡፡ ሌሊት ሌሊት ሲያስተምርና ሲጸልይ የቅዱስ ዲዮስቆሮስ ጥርሶቹ እንደ ፋና ያበሩለት ነበር፡፡ ይህም በተኣምራት የተፈጸመ ነው፡፡
tattoos on neck , forehead and gums , wearing a silver cross and a white garment decorated with crosses , Lalibelaሦስት ቀለማት ያላቸው ክሮች የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሲኾኑ አንድ ላይ መፈተላቸው ወይም አንድ መኾናቸው ቅድስት ሥላሴ ማለት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በመለኰት በህልውና አንድ አምላክ መኾናቸውን ያመለክታል፡፡ ጥቁሩ፡- ክርስቲያን ስለ ሃይማኖት የሚቀበለው መከራ የሚሸከመው መስቀል፣ ቀዩ፡- በሰማዕትነት ደም የማፍሰስ ሲኾን ቢጫው ደግሞ የክርስቲያን ተስፋ የሃይማኖት ምልክት ነው፡፡
ቆይቶ ግን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሕፃናት ክርስትና ሲነሡ፣ ኢአማንያን አምነው ሲጠመቁ ቀይ፣ ነጭና ሰማያዊ ፈትሎች በአንድ ላይ ተገምደው መታሰር ጀመረ፤ ትርጓሜውም የሦስቱ አንድ ላይ መገመድ የሥላሴን አንድነት ሦስትነት የሚያመለክት ምሳሌ ነው፡፡ ይኽንንም ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲያስረዱ፡- ሥላሴ ማዕተበ ብርሃን ኃይለ ሃይማኖቶሙ ለክርስቲያን፤ ሥላሴ ለክርስቲያን ኹሉ የሃይማኖታቸው ጉልበት መታወቂያ የብርሃን ማዕተብ (ምልክት) ናቸው፤ ብለዋል፡፡
ቀለሞቹ ደግሞ ቀይ፡- ክርስቶስ ደሙን አፍስሶ አድኖናል፤ ስለ ስሙም በሰማዕትነት ደማችንን ማፍሰስ ይገባናል የማለት፤ ነጩ፡- የጥምቀት በጥምቀትም የሚገኝ ስርየተ ኃጢአት፤ ሰማያዊ፡- በጸጋ ልጅነት አግኝቻለኹ፤ ሰማያዊ አባት አለኝ፤ ሰማያዊ ርስት መንግሥተ ሰማይ ይቆየኛል፤ ስለዚኽም በሰማያዊ ግብር ጸንቼ መኖር በሰማያዊት ሕግ ሕገ ክርስቶስ ወንጌል ተመርቼ መኖር ይገባኛል እንደማለት ነው፡፡
Ethiopia, with a cross branded on her foreheadበኢትዮጵያ ክርስትና የገባው በዘመነ ሐዋርያት በመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ ይኹንና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ጵጵስና ከሌሎች ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያን ጋራ የዕኩልነት ማዕርግ ያገኘችው በአራተኛው ምእት ዓመት በቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን እንደኾነ ተረጋግጧል፡፡ በዚኽ ዘመን አቡነ ሰላማ ሕዝቡን አጥምቀው ወደ ክርስትና ሲመልሱ ለክርስትናቸው ምልክት ከግንባራቸው ላይ እየበጡ መስቀለኛ ምልክት ያደርጉላቸው እንደነበር ይተረካል፡፡
ከአቡነ ሰላማ የጀመረው ማዕተብ የማሰር ትውፊት በዘጠኙ ቅዱሳን ዘመንም እየተስፋፋ ሔዶ በቤተ ክርስቲያን ክርስትና ለሚነሡ ኹሉ ሥርዐተ እምነታችን ኾኖ ቆይቷል፡፡ እስከ አኹንም በተለይ በሰሜናውያን ዘንድ በመበጣትም ኾነ በንቅሳት ለክርስትናቸው ምልክት መስቀል ከግንባራቸው ማድረግ የጸና ልምድ ኾኖ ይታያል፡፡
* * *
ማዕተብ ያላሰረ ኦርቶዶክሳዊ የአባቶቹን የተቀደሰ ክርስቲያናዊ ትውፊት እንዳልተቀበለ ያስቆጥረዋል፡፡ በምሳሌያዊ አነጋገርም ሃይማኖት አልባውን ማለትም ክርስቲያን ያልኾነውን ማተብ የለሽ፣ ያልተጠመቀ፣ አረሚ ይሉታል፡፡ ክርስቲያን በማተቡ መነኵሴ በቆቡ እንዲታወቅ ማተብ አልባ መኾን ደግሞ ክርስቲያን ይኹን ያልተጠመቀ ለመለየት ያስቸግራል፡፡ በመለዮዋቸው ሌሎች እንዲታወቁ ክርስቲያን በማተቡ ክርስትናውን ሲያሳውቅ ኖሯል፡፡
በተለመደው አነጋገር÷ እገሌ ማተብ አለው፤ ባለማተብ ነው ሲባል እገሌ ታማኝ ክርስቲያን ነው፤ እውነተኛ ሐቀኛnigel-pavitt--ethiopia ነው የማለትን ትርጉም ይሰጣል፡፡ ባለማተቢቱ ሲባል ከአሚን ባሏ የረጋች ከባሏ ሌላ የማታውቅ እውነተኛ ታማኝ ክርስቲያን የማለት ፍች አለው፡፡ በዚኽ ምክንያት በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ የማተብ ትርጉም ከፍተኛ ቁምነገርን አዝሎ ይገኛል፡፡
አንዲት ሀገር ነፃና ሉዓላዊ መኾኗ የሚታወቀው ወይም ራሷን የቻለች መንግሥት ያላት ከባዕድ ቀንበር ቅኝ ግዛት ነፃ የወጣች መኾኗ በቀዳሚነት የሚለየው በባንዴራዋ ምልክትነት እንደኾነ እንደዚኹም አንድ ክርስቲያን በክርስቶስ አምኖ በጥምቀት ከዲያብሎስ ቁራኝነት ነፃ መውጣቱ፣ ነፃነት ያለው አማኝ መኾኑ የሚታወቀው በማተቡ ምልክት ነው፡፡ ለደብዳቤ፣ ለጽሑፍ ዓርማ ማኅተም ፊርማ እንደሚያስፈልገው ያም ለመተማመኛ እንደሚያገለግል ጥቅሙ ታውቆ ይሠራበታል፡፡
በዚኹ አንፃር የክርስቲያን ማዕተቡም ሃይማኖታዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ በቅድሚያ፣ በልቡ የሚያምነው ሃይማኖት ክርስትናን ሳያፍርበት በአንገቱ ባለው ማተብ መግለጹ በክርስትናው አለማፈሩን፣ ክርስትናኽን ካድ ማተብኽን በጥስ የሚል ዐላዊ ቢመጣና ያን ምልክት አይቶ ቢሠዋው የሰማዕትነት ክብር ያገኘበታል፡፡ ያም ባይኾን በማተቡ ምልክትነት በመናፍቃንና በኢአማንያን የሚቀበለው ዘለፋ ስለ ክርስቶስ መስቀል እንደተሸከመ ያስቆጥረዋል፡፡
ኹለተኛው፣ ያለጥርጥር ክርስቲያን መኾኑ ታውቆለት ከክርስቲያን ወገኖች ጋራ ተሳትፎውን ማከናወን ይችላል፡፡ ማተብ ከሌለው ግን ክርስቲያን ይኹን ያልተጠመቀ ስለማይታወቅ በሃይማኖት ዜጎች ዘንድ በቀላሉ ተቀባይነት ማግኘት አይችልም፡፡ ሦስተኛ፣ ከማይታወቅበት አገር እንደወጣ በበሽታም ይኹን በአደጋ ሕይወቱ ቢያልፍ በማተቡ መታወቂያነት የክርስቲያን ሥርዐት ተፈጽሞለት በቤተ ክርስቲያን ሊቀበር ይችላል፡፡
አራተኛ፣ ማተብና መስቀል ያለው ክርስቲያን በውኃ ዋና ወይም በበረሓ ጎዳና በውኃ የሚኖሩ ወይም በበረሓ ያሉ አጋንንት በቀላሉ ሊለክፉት አይችሉም፡፡ ይህም በየጠበሉ ስፍራ በተኣምራት ተረጋግጧል፡፡ አጋንንት የለከፏቸው ሰዎች ማተብና መስቀል አይወዱም፡፡ የሰፈረባቸው ርኩስ መንፈስ ማተብ እንዲበጥሱ መስቀል እንዲጥሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ማተብ በሰይጣን ዘንድ ከተጠላ በአጋንንት ላለመለከፍ የማዕተቡ መኖር ይጠቅማል ማለት ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች የማዕተብ ሥርዐትን ለመቃወምና ዘመናውያን መስለው ለመታየት ‹‹እምነት በልብ ነው›› ይላሉ፤ ተሳስተዋል! ሃይማኖት የልብ ብቻ አይደለም፤ የጠቅላላው ሕዋሳት ኹሉ ናት፡፡ እግዚአብሔርን ስንወደውና ስናመልከው በልባችን ብቻ ሳይኾን በአፋችንም በአንገታችንም በጠቅላላው ሰብአዊ ተፈጥሯችን ኹሉ መኾን ይገባዋል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር የጠቅላላው ሰውነታችን አምላክና ፈጣሪ ስለኾነ ነው፡፡ ‹‹ስለዚኽ በሰው ፊት የሚመሰክርልኝ ኹሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለኹ፤ በሰው ፊትም የሚክደኝን ኹሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለኹ፡፡›› (ማቴ.፲÷፴፪÷፴፫)
በዚኽ ቃለ ወንጌል መሠረት በኢአማንያን ዘንድ ክርስቲያን መኾናችንን የምንገልጸው በልባችን ብቻ ሳይኾን በቃላችንና በሥራችንም ጭምር ነው፡፡ በአንገታችንስ እንዳንመሰክርለት ማን ያግደናል? በአንገታችን ባለው ማዕተብም ለእግዚአብሔር እንመሰክራለን፡፡ የስሙን ምልክት በአንገታችን እናኖራለን፤ አናፍርበትም!! የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ በጥምቀታችን እንደምንመሰክር የጥምቀታችንንም ዓርማ በማተባችን እናረጋግጣለን፡፡ (ሮሜ ፲፮÷፲፫፤ ኢዩኤ. ፪÷፴፪፤ ሮሜ ፮÷፩-፭፤ ማቴ.፭÷፲፩-፲፪፤ ፩ኛጴጥ.፫÷፳፩-፳፪፤ ፬÷፲፪-፲፮)
ከወንጌል የተለየች ትምህርት እንዳንቀበል ሐዋርያት አስጠንቅቀውናል፡፡ መላእክት በራእይ ገልጸውልናል፤ ከእግዚአብሔር አግኝቻለኹ ብለው የሚመጡትን መናፍስት እንድንመረምራቸው በቅዱሳት መጻሕፍት ታዝዘናል፡፡ ማተብ የማሰር የተቀደሰ ክርስቲያናዊ ትውፊታችንን የሚቃወሙ በክርስቶስና ሞትና ትንሣኤ የማያምኑ ተረፈ አይሁድ ስለኾኑ ተቃውሞውን ዋጋ ሳንሰጠው ማተባችንን እናጠብቃለን፡፡ ‹እንደ ውሻ በአንገታችኹ ገመድ አስራችኹ› ተብለን በመነቀፋችንም እንደሰትበታለን እንጂ አንሠቀቅም፡፡ ውሻ ለጌታው ታማኝ ነው፡፡ ሌሎች የተለከፉ ያበዱ ዘላን ውሾች እንዳይለክፉትና ከሞት እንዳያደርሱት ወይም ወንበዴዎች በሥጋ መርዝ ቀብተው ለሥጋው ሲሣሣ እንዳይገድሉት ትንሽ ጎጆ ሠርቶለት ቢያስረው ለውሻው ሕይወት አስፈላጊ እንደኾነ በኹሉም የታወቀ ነው፡፡
an Ethiopian diptych icon, illustrating scenes from the life of Christ, mostly his Passion በዚኹ አንፃር ክርስቲያን ለክርስቶስ ታማኝ በመኾኑ በነፍሱ ሞግዚት በቄሱ እጅ ከሕፃንነቱ ጀምሮ የድኅነቱ ምልክት በሚኾን አንገቱ በማዕተበ ክርስትና ይታሰራል፡፡ ማዕተብ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ስለ እኛ ቤዛ ለመኾን የብረት ሀብል /የብረት ገመድ/ በአንገቱ ታስሮ በአይሁድ መጎተቱን ስለሚያስታውሰን ለታማኝነታችንና ለክርስቲያንነታችን ምልክትነቱ ማረጋገጫ ስለኾነ አናፍርበትም፡፡ በድርሳነ ሰንበት ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ የውሻን ታማኝነት ለክርስቲያን ታማኝነት ምሳሌ አድርጎ ገልጾታል – ‹‹ከልብሰ የአምር እግዚኡ፤ ውሻ ጌታውን ያውቃል››፡፡ ጌታችንም በቅዱስ ወንጌል በውሻ የተመሰለችውን ከነናዊቷን ሴት ስለ ታማኝነቷ አድንቋታል፤ ልጅዋንም ፈውሶላታል፡፡(ማቴ.፲፭÷፳፩-፳፰)
ማዕተብን ከሚቃወሙ አንዳንዶች ‹‹ጽዳት ያጎድላል›› በማለት ያመካኛሉ፡፡ በርግጥ የጠንቋይ ክታብ የቃልቻ ግሣንግሥ መሰብሰቢያ ካደረጉት የሥጋ ንጽሕናን ብቻ ሳይኾን የሚያጎድለው የነፍስንም ጽዳት የሚያጎድል መኾኑ ዕውቅ ነው፡፡ ማተብ እና መስቀሉ ግን ጽዳት ያጎደለበት ጊዜ ስለሌለ ሰበብ አያዋጣም፡፡ ስለዚኽ የክርስትናችንን ዓርማ የነፍሳችንን ሰንደቅ ዓላማ በነፃነት ስናውለበልብ ለመኖር ያብቃን፡፡ አሜን፡፡
ምንጭ፡- መለከት መጽሔት፤ ፩ኛ ዓመት ቁጥር ፮፤ ሚያዝያ ፲፱፻፹፭ ዓ.ም.
About these ads

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...