ማክሰኞ 23 ዲሴምበር 2014

የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በደብረ ሊባኖስ አንድነት ገዳም





ታኅሣሥ 13 ቀን 2007 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
dscn3853ማኅበረ ቅዱሳን 7ኛውን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በደብረ ሊባኖስ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም ታኅሣሥ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. አካሔደ፡፡

መነሻውን አዲስ አበባ ከሚገኘው ዋናው ማእከል ያድረገው ጉዞ ከለሊቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ከ80 በላይ በሚሆኑ አንደኛ ደረጃ አገር አቋራጭ አውቶቡሶች ከ5000 በላይ ምእመናንን በመያዝ ተንቀሳቅሰዋል፡፡

dscn3547መርሐ ግብሩ በገዳሙ አባቶች በጸሎተ ወንጌል ከረፋዱ 4፡30 ተጀምሯል፡፡ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ማትያስ የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ የገዳሙ 12ቱ ንቡራነ እድ፤ እንዲሁም የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች በተገኙበት “ቅንነት ግን ፊቱን ታየዋለች” መዝ. 11፡7 የሚለውን ጥቅስ መነሻ በማድረግ የተዘጋጀው 7ኛው የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በመዝሙራቱ፤ እንዲሁም በስብከተ ወንጌል አገልግሎቱ ሲቀርብ ውሏል፡፡dscn3525

በዚህም መሠረት በጠዋቱ መርሐ ግብር ክፍል አንድ የወንጌል ትምህርት የማኅበረ ቅዱሳን መደበኛ ሰባኬ ወንጌል በሆኑት በመምህር ምሥጢረ ሥላሴ ማናዬ “በቅንነት የሚሄድ ይድናል” ምሳ.28፡18 በሚል ርእስ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡

የደብረ ሊባኖስ ገዳም ገዳማዊ ሥርዓቱ እንደተጠበቀ ቢሆንም የጎርፍ አደጋ፤ የብዝኅ ሕይወት መመናመን፤ የሕገ ወጥ የመሬት ወረራና ሌሎችም ችግሮች እየተፈታተኑት ይገኛል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በገዳሙና በማኅበረ ቅዱሳን ባለሙያዎች ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ ፕሮጀክቱን አስመልከቶ የተዋቀረው ኮሚቴ ተወካይ በዲያቆን ቱሉ ስለ ጥናቱ ገለጻ ተደርጓል፡፡

በቀረበው ጥናትም የገዳሙ የወደፊት አቅጣጫና ዕጣ ፈንታ ያሳሰባቸው የገዳሙ አባቶች በ2003 ዓ.ም. ለማኅበረ ቅዱሳን በደብዳቤ በማሳወቃቸው ጥናቱን ለማጥናት እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡

የተቀረጹት 11 ፕሮጀክቶች በሦስት ዙር በመክፈል እጅግ አንገብጋቢ የሆኑትን፣ የመጸዳጃና የአካባቢ ንጽሕና፤ የመሬት መንሸራተርትና የጎርፍ አደጋ፤ የመነኮሳት በዓት ችግር፤ የአብነት ትምህርት ቤት አደጋ ላይ መሆኑ፤ መቃብር ቦታ ችግር ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንደሚሰሩ የጠቀሱት ዲያቆን ቱሉ በሁለተኛው ዙር የአብነት ትምህርት ቤትና የሥልጠና ማእከል ግንባታ፤ መኪና ማቆሚ ቦታ ዝግጅት፤ መቃብር ሥፍራ ዝገጅት ፕሮጀክች እንዲሁም በሦስተኛው ዙር የጤና ጣቢያ ግንባታ፤ የሁለገብ ሕንፃ ግንባታ፤ የአስኳላ ትምህርት ቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች ይተገበራሉ ብለዋል፡፡

በቅድሚያ ሊሰሩ ከታቀዱት ውስጥ 24 ክፍል ያለው መጸዳጃ ቤት ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መሥጠት መጀመሩን፤ 8 ክፍሎችን የያዘ የገላ መታጠቢያና መጸዳጃ ቤት መጠናቀቁን፤ የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት /ቤዝመንት/ እየገፋ ያለውን ጎርፍ ለመከላከል 100 ሜትር ርዝመት እና 10 ሜትር ቁመት ያለው የጎርፍ መከለያ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ፤ በቅርቡም 2500 ሰው ማስተናገድ የሚችል የእንግዳ ማረፊያና ሁለገብ አዳራሽ ለመሥራት ዲዛይኑ አልቆ ቦታው በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡

dscn3668ከሰዓት በኋላ የተካሔደውን መርሐ ግብር በማኅበረ ሰላም መዘምራንና በሊቀ ዲያቆን ምንዳዬ ብርሃኑ ያሬዳዊ ዝማሬ በማቅረብ ተጀምሯል፡፡

ሁለተኛው የወንጌል ትምህርት በደብረ ገነት ሞጣ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሐዲሳትና የፍትሐ ነገሥት ጉባኤ ቤት መምህር በሆኑት መምህር ወልደ ትንሣኤ “ቸልተንነት” በሚል ርእስትምህርት ተሰጥቷል፡

dscn3740ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰላሌና ሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልእክት “ዛሬ ባየሁት ነገር በጣም ተደስቻለሁ፤ በእንደዚህ ያለ ሰፊ ጉባኤ ተገኝቼ አላውቅም፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ `በጉባኤ መካከል እያለን ብቻችንን የቆምን ይመስለናል` ይላል፡፡ እኔም ምንድነው ነገሩ፤ የት ነው ያለሁት እስክል ድረስ በመንፈሳዊ ተመስጦ ውስጥ ገብቼ ነበር፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን በዚህ ታላቅ ገዳም ይህንን ታላቅ ጉባኤ በማድረጉ ምእመናን እምነታችሁን በሥራ እየተረጎማችሁት መሆኑን ያየሁበት ነው. . . ክርስቲያናዊ ሥራ እየሠራ ያለ ክርስቲያን መሥጋት የለበትም፡፡ ፈቃዱን እየፈጸሙ የሚያገለግሉ ሁሉ ነፍሳቸው በአደራ ጠባቂው በእግዚአብሔር እጅ ላይ ነው፡፡ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አደራ ሰጥታችሁ ክርስቲናዊ አገልግሎታችሁን እስከ መጨረሻው ድረስ እንድትፈጽሙ አደራ እላለሁ” ብለዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ማትያስ በሰጡት ቃለ ምእዳን “ልጅ አባቱ አይዞህ ካለው ካሰበው ሁሉ ነገር ላይ መድረስ ይችላል፡፡ በእግዚአብሔር ትእዛዝና ሕግ የሚጓዝ ብፁዕ ነው እንዳለው ቅዱስ ዳዊት የምንመካውም ኃይላችንም እግዚአብሔር ስለሆነ በርትታችሁ አገልግሎታችሁን ፈጽሙ” ብለዋል፡፡

“ወኩኑ ታቦተ መንፈሳዌ ለክህነት ቅድስት ወንጽሕት፤ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ” /፩ኛ ጴጥ. ፪፥፭/





ታኅሣሥ 14ቀን 2007 ዓ.ም.
መምህር ኅሩይ ባዬ
የዲያቆናት አለቃ የመጀመሪያው ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ በሠላሳ አምስት ዓመተ ምሕረት በድንጋይ ተወግሮ ሰማዕትነትን ተቀበለ፡፡ ያን ጊዜም በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምነው ክርስቲያን የሆኑ የአይሁድ ወገኖች ተበተኑ፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም መከራ ውን ሳይሠቀቁ እምነታቸውን ጠብቀው በሃይ ማኖት እንዲጸኑ በስድሳ ዓመተ ምሕረት መጀ መሪያይቱን መልእክት ለተበተኑ ምእመናን ጽፎላ ቸዋል፡፡

ወኩኑ ታቦተ መንፈሳዌ ለክህነት ቅድስት ወንጽሕት፤ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈ ሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ ሲል ሰማያዊ ጥቅም ከማያሰጥ ከክህነተ ኦሪት በተለየ ለክህነተ ወን ጌል መንፈሳዊ ማደሪያ ለመሆን ተዘጋጁ ማለቱ ነው፡፡ ቅድስት ማለቱም ምሳሌያዊ ከሆነው የኦ ሪት ክህነት ተለይቶ አማናዊ ክህነትን ለመ ያዝ የእግዚአብሔር ማደሪያ መንፈሳዊ ቤት ሆኖ መሠራት ስለሚያስፈልግ “ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ” እያለ ይጽፋል፡፡

በዚህ ትምህርታዊ ስብከት ካህን የሚለውን ቃል በመተርጐም የካህናትን ተልእኮ በማመልከት የሓላፊነቱን ታላቅነትና ክቡርነት እንመለከታለን፡፡ በሁለተኛው ክፍልም ክህነት ከእግዚአብሔር የተቀበልነው፣ የታደልንለት እና የተጠራንለት አደራ በመሆኑ ሥልጣነ ክህነታችንን ጠብቀን ራሳችንን፣ ቤተ ክርስቲያናችንን፣ እምነታችንን፣ እና ምእመናንን እንዴት መጠበቅ እንዳለብን እንማራለን፡፡

“ተክህነ” የሚለው ቃል ተካነ አገለገለ ክህነትን ተሾመ /ተቀበለ/፤ በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል ቆሞ ለማገልገል ካህን ተባለ የሚለውን ትርጓሜ ያመለክታል፡፡ “ክሂን” ከሹመት በኋላ ማገልገልን፤ “ተክህኖ” ከማገልገል በፊት መሾምን የሹመትን ጊዜ የተቀበሉበትን ዕለትና ሰዓት ያሳያል፡፡

ክህነት ቢልም መካን ማስካን ካህንነት ተክኖ ማገልገልን ያሳያል፡፡ ካህን የሚለውን ቃል ሶርያ ውያን “ኮሄን”፣ ዕብራውያን “ካህን”፣ ሲሉት ዐረ ቦች ደግሞ ካህና በማለት ይጠሩታል፡፡ ካህን የሚ ለውን ቃል በቁሙ ቄስ ጳጳስ የእግዚአብሔር አገልጋይ የሕዝብ መሪ አስተማሪ መንፈሳዊ ሀብት ብለው አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ይተረጉሙ ታል፡፡

እነዚህን የመዝገበ ቃላት ትርጓሜዎች እንደ ዋልታ አቁመን ጠቅላላ ትርጓሜ መስጠት ይቻ ላል፡፡ ክህነት “ተክህነ” አገለገለ ከሚለው የግእዝ ግስ ይወጣል፡፡ ክህነት የሥልጣኑ ስም ሲሆን አገልጋዮቹ ካህናት ይባላሉ፡፡ ክህነቱ የሚገኝበት መንፈሳዊ ምሥጢርም ምሥጢረ ክህነት ይባላል፡፡ በሚታይ የአንብሮተ እድ አገልግሎት የማይታይ የሥልጣነ ክህነት ሐብት ይገኝበታልና ምሥጢር የተባለበት ምክን ያትም በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ስለሚገኝበት ሲሆን ምሥጢረ ክህነትን የጀመረው /የመሠረተው/ ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

በክቡር ደሙ የዋጃትንና የመሠረታትን ቤተ ክርስቲያን እንዲያገለግሉ ካህናትን የለየ፣ የጠራና የሰየመ አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ከትንሣኤው በኋላ የመነሣቱን አዋጅ ለማብሰር ወደ ዓለም ሲላኩ በክህነታቸው ታላላቅ ተአምራትን አድርገዋል፡፡ /ማር. ፲፮፥፲፮/ ያስሩም ይፈቱም ነበር፡፡ /ማቴ. ፲፰፥፲፰/ ይህ የማሰርና የመፍታት ሥልጣን እስከ ኅልፈተ ዓለም የሚቀጥል መሆኑን አምላካችን በቅዱስ ወንጌል አስተም ሯል፡፡ /ማቴ. ፳፰፥፳/

ክህነት በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ሦስት ደረጃዎች አሉት፡፡ እነርሱም ዲያቆን፣ ቄስ፣ ኤጲስ ቆጶስ በመባል ይታወቃሉ፡፡ የአንጾኪያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ አግናጥዮስ እነዚህን ሦስት የክህነት ደረጃ ዎች እንዲህ በማለት ገልጿቸዋል፤ “ለእግዚአብሔር የሚገባችሁን ሁሉ ለማድረግ ፍጠኑ፤ የሚመ ራችሁ ኤጲስ ቆጶስ የእግዚአብሔር እንደራሴ ነው፡፡ ቄሱም እንደሐዋርያት ዲያቆናትም ለክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ባለአደራዎች ናቸውና”

በሌላ አገላለጥ ከሦስቱ ጾታ ምእመናን /ወንዶች፣ ሴቶችና ካህናት/ አንዱ ካህን ነው፡፡ ካህን ከወንዶችና ከሴቶች ምእመናን በተለየ ከፍ ያለ ሓላፊነት አለው፡፡ ይህ ሓላፊነት ምድ ራዊ ሳይሆን ሰማያዊ፤ ሥጋዊ ሳይሆን መንፈ ሳዊ ሓላፊነት ነው፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ አንድ ወጣት ቅስና ለመቀበል ፈልጐ ወደ እርሳ ቸው ሔደ፡፡ ቅዱስነታቸውም አሁን የምሰጥህ የክ ህነት ሥልጣን ሹመት ሳይሆን ሓላፊነት ነው በማለት ተናግረዋል፡፡

ሹመት ደረት ያቀላል፤ ሆድን ይሞላል፤ ሓላ ፊነት ግን ያሳስባል፣ ያስጨንቃል፣ እንቅልፍ ያሳ ጣል፣ ክህነት ሓላፊነት በመሆኑ አንድ ካህን ሳይ ታክትና ሳይሰለች በጸሎት በጾምና በስግደት ስለ ራሱ ኃጢአት እና ስለ መንፈሳዊ ልጆቹ ክርስቲ ያናዊ ሕይወት ስለሚጨነቅ ምንጊዜም ቢሆን ዕረ ፍት የለውም፡፡ አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ግልገሎቼን አሠማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጎቼን አሠማራ” /ዮሐ. ፳፩፥፲፮/ ብሎ ለካህናት የኖላዊነትን ሓላፊነት የሰጠበት የአደራ ቃልም እንደዋዛ የሚታይ አይደለም፡፡


ካህን ካህን ከመሆኑ አስቀድሞ ምእመናንን የማስተማር ብቃቱ፣ ቤተሰቡን የመምራት ችሎ ታው፣ የአንድ ሴት ባል መሆኑ፣ ቤተሰባዊ ሓላፊ ነቱን የመወጣት አቅሙ፣ ልጆቹን የማስተዳደር ክሂሎቱ እና ከሰዎች ጋር ያለው የሠመረ ግንኙ ነቱ ጤናማ ሊሆን እንደሚገባ ቅዱሳት መጻሕ ፍት ያስረዳሉ፡፡

ካህን ከሕይወቱ ሊያስወግዳቸው የሚገቡ ክፉ የሆኑ ጠባያትም በመጽሐፍ ተዘርዝረዋል፡፡ ካህን ለብዙ የወይን ጠጅ የማይጎመጅ /የማይ ሰክር/፣ በሁለት ቃል የማይናገር፣ ከፍቅረ ንዋይ የራቀ፣ አጥብቆ ገንዘብን የማይወድ፣ በንጹሕ ሕሊና የሃይማኖትን ምሥጢር የሚጠብቅ፣ ግልፍተኛ ያልሆነ፤ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በአንጻሩም ትሑት፣ የማይጋጭ፣ ይቅር የሚል፣ ትዕግሥተኛ የሆነ እንደሆነ ለሚመራቸው ምእመናን ትክክለኛ አርአያ መሆን ይችላል፡፡

ካህናት በሐዋርያት መንበር ተቀምጠው የማሠርና የመፍታትን ሓላፊነት ይወጣሉ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደጻፈልን “ካህናት በምድር የፈጸሙትን ጌታ በሰማይ ያጸናላቸ ዋል፤ የባሮቹን /የካህናትን/ አሳብ ጌታ ይቀበለ ዋል” በመሆኑም ካህናት በምድር ላይ የሚፈጽሙአ ቸውን ምሥጢራት እግዚአብሔር በሰማያዊ ምሥ ጢር ተቀብሎ ያከብራቸዋል፡፡
ኤጲስ ቆጶሳት መዓርገ ክህነቱን ለሚመለከ ታቸው ወገኖች ከመስጠታቸው በፊት የቅድ ሚያ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ፤ ምእመናንም በጉዳዩ ላይ አሳብና አስተያየታቸውን ለኤጲስ ቆጶሱ ቢናገሩ መልካም እንደሆኑ የሚደነግጉ መጻ ሕፍት አሉ፡፡ ስለሆነም

ካህኑ ከመሾሙ በፊት፡-

1. የሃይማኖትን ምሥጢር ጠንቅቆ የሚያውቅ መሆን እንዳለበት ሐዋርያት በጉባኤ ኒቅያ ደንግገዋል፡፡ /ጉባኤ ኒቅያ ፫፻፳፭ ቀኖና ፲፱/
2. አዲስ አማኒ ያልሆነ /ጉባኤ ኒቅያ ፫፻፳፭ ቀኖና ፪-፱/
3. የመንፈስ ጤንነት ያለው /የሐዋ. ቀኖና ፸፰/
4. ዕድሜው ከሠላሳ ዓመት ያላነሰ፤ ሊሆን እንደ ሚገባ /ስድስተኛው ሲኖዶስ ቀኖና ፲፫/ በግልጥ ያስቀምጣል፡፡

የካህናት ተልእኮ

የኤጲስ ቆጶሳት ተልእኮ ቀሳውስትን እና ዲያቆናትን ይሾማሉ፣ ያስተምራሉ፣ ያጠምቃሉ፣ ያቆርባሉ፡፡ በሀገረ ስብከታቸው ያሉት ምእመናን ማኅበራዊና መንፈሳዊ ችግር ሲደርስባቸው ይመክ ራሉ፣ ያጽናናሉ “ሕዝቡን ጠዋትና ማታ ለነግህና ለሠርክ ጸሎት በቤተ ክርስቲያን ይገኙ ዘንድ” ያዝዟቸዋል፡፡

የቀሳውስት ተልእኮ፡- እንደ ኤጲስ ቆጶሱ ያስተ ምራሉ፤ ያጠምቃሉ፣ ያቆርባሉ፡፡

የዲያቆናት ተልእኮ፡- ለኤጲስ ቆጶሱና ለካህኑ ይላላካሉ፤ ምሥጢራትን ግን የመፈጸም ሓላፊነት የላቸውም፡፡
ከእነዚህ መሠረታዊ የክህነት ደረጃዎች ሌላ በቤተ ክርስቲያን የሚታወቁ መዓርጋት አሉ፡፡ እነርሱም ንፍቅ ዲያቆን፣ አንባቢ /አናጉንስጢስ/ መዘምር፣ ኀፃዌ ኆኅት /በረኛ/ በመባል ይታወቃሉ፡፡ ንፍቅ ዲያቆን ዋናውን ዲያቆን ይረዳል፡፡ አንባቢ /

አናጉንስጢስ/ በቅዳሴ ጊዜ መልእክታትን ያነብ ባል፡፡ መዘምር ደግሞ የመዝሙር አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ኀፃዌ ኆኅት ቤተ ክርስቲያንን ይጠር ጋል፣ ያጸዳል፣ ያነጥፋል፣ ደወል ይደውላል፣ በጸሎት ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን ይከፍታል ይዘጋል፡፡
ከእነዚህ የተቀብዖ ስያሜዎች ውስጥ ፓትር ያርክ የሚባለው መዓርግ ከሊቃነ ጳጳሳት መካከል ለአንዱ በፈቃደ እግዚብሔር በምርጫ ይሰየ ማል፡፡

ይህ የመዓርግ ስም የተጀመረው በአምስተ ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን በዚህ የመዓርግ ስም ይጠሩ የነበሩት የሮም፣ የእስክንድርያና የአን ጾኪያ ታላላቅ ከተሞች አባቶች /መጥሮ ፖሊሶች/ ነበሩ፡፡ በኋላ ግን ራሳቸውን ችለው የሚተዳደሩ አገሮች ሁሉ የየራሳቸውን ፓትርያርክ ሹመዋል፡፡ ፓትርያርክ ማለት በግሪኩ ቋንቋ ርእሰ አበው /አባት/ ማለት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስ ቲያን ሥርዐት ሦስቱ ዐበይት የክህነት መዓርጋት ዲቁና ቅስና ኤጲስ ቆጶስ ናቸው፡፡ ንፍቀ ዲቁና አንባቢ፣ መዘምርና ኀጻዌ ኆኅት በመባል የሚታ ወቁት አራቱ ንኡሳን መዓርጋት በአገልግሎት ውስጥ በግልጽ የሚታዩና በዲቁና ወስጥ የሚጠ ቃለሉ መዓርጋት ናቸው፡፡
ሥልጣነ ክህነት የነፍስ ሕክምና አገልግሎት በመሆኑ ልዩ ጥንቃቄና ክብካቤ ያሻዋል፡፡ ሥልጣነ ክህነት በዘመድ፣ በዘር፣ በአገር ልጅነት በገንዘብ አይሰጥም፡፡ ለመሾም ተብሎም እጅ መንሻ መስ ጠትና መቀበል ፈጽሞ የቤተ ክርስቲያን ትው ፊት፣ ሥርዐትና ቀኖና አይደለም፡፡

የካህናትን ክብር ካስተማሩን አበው መካከል አንዱ ቅዱስ አትናቴዎስ በቅዳሴው “ኦ ካህናት አንትሙ ውእቱ አዕይንተ እግዚአብሔር ብሩሃት ተናጸሩ በበይናቲክሙ አሐዱ ምስለ ካልዑ፤ ካህ ናት ሆይ ብሩሃን የእግዚአብሔር ዓይኖች እናንተ ናችሁ እርስ በርሳችሁ አንዱ ካንዱ ጋራ /ተያዩ/ ተመለካከቱ” ይላል፡፡ ይህም በችግሮቻችን ዙርያ መወያየት፤ መነጋገርና መደማመጥ የሚያስፈልግ መሆኑን ያስረዳናል፡፡

“የኩነኔ አገልግሎት ክብር ከሆነ ይልቅ የጽድቅ አገልግሎት በክብር አብዝቶ ይበልጣልና” /፪ኛ ቆሮ. ፫፥፱/ እንዳለው ሐዋርያው የክህነት አገልግሎት የተለየ እና ክቡር መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ክህ ነት ከእግዚአብሔር የተገኘ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ወደ እግዚአብሔርም የሚያደርስ ታላቅ መሰላል ነው፡፡

የሥርዐተ ጥምቀት፤ የሥርዐተ ቁርባን፤ የሥርዐተ ተክሊልና የምሥጢረ ንስሐ መፈጸሚያና ማስፈጸሚያ መንፈሳዊ መሣሪያ ሥልጣነ ክህነት መሆኑን ስንረዳ የምንሰጠው ክብርም የተለየ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ “ወወሀቦሙ ሥልጣነ ዘከማሁ ይእስሩ ወይፍትሑ ኲሎ ማእሠረ አመጻ፤ እንደ እርሱ የኃጢአትን ማሠሪያ ያሥሩና ይፈቱ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” /ዮሐ. ፳፥፳፪-፳፫/ መዓርጉ ክቡር በመሆኑ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ክቡር የሆነውን ክህነት አክብረን እንድንከብርበት መለኮ ታዊ ኃይሉ ይርዳን፡፡

ሐሙስ 11 ዲሴምበር 2014

ወእሙሰ ተአቅብ ኩሎ ዘንተ ነገረ ወትወድዮ ውስተ ልባ /እመቤታችን ግን ይህን ሁሉ ነገር ታስተውለው፤ በልቡናዋም ትጠብቀው ነበር፡፡/ሉቃ 2፡51/


ዲ/ን ታደለ ፈንታው
 መግቢያ
አስቀድመን መሪ ኃይለ ቃል አድርገን የተነሣንበት አንቀጽ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ላይ አድሮ የተናገው ቃል ነው፡፡  የእመቤታችን ፍቅር በውስጡ ጥልቅ መሆኑ፣ ነገረ ማርያም የገባው መሆኑ የተገለጠበት ፍካሬ ቃል ነው፡፡ የእርሷስ ፍቅር በሌሎች ሐዋርያትም ላይ አለ፤ በጎላው በተረዳው ለመናገር ያህል ነው እንጂ፡፡

በድርሳነ ኡራኤል ላይ እንደተገለጠው እመቤታችን በቤተ ዮሐንስ ሳለች ወንጌላዊው ከሚያስተምርበት ውሎ ሲመለስ እንደምን ዋልሽ አላት፤ እርሷ ግን አልመለሰችለትም፡፡ የጌታዬ እናት ለምን ዝም አለችኝ ብሎ አርባ ቀን ሱባዔ ያዘ፤ በአርባኛው ቀን መልአኩ ቅዱስ ኡራኤል ተገልጦ እመቤታችንን የልጅሽን ወዳጅ ዮሐንስን ለምን ዝም አልሺው አላት፤ እርስዋም ልጄ ወዳጄ ሰማያዊውን ምሥጢር እያሳየኝ አላየሁትም ነበር አለችው፡፡ የወንጌላውያን ነገር እጅግ ያስደንቃል፡፡

ቅዱስ ሉቃስ ከተነናገረው ገጸ ምንባብ አንዱን ቃል ብቻ ወስደን ብንመለከት ነገረ ማርያም ሊደረስበት የማይችል ሩቅ፣ ሊመረመር የማይችል ረቂቅ፣ ጥልቅ ሰማያዊ ምሥጢር የተቋጠረበት መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሉቃስን ወንጌል ከተመለከቱ በኋላ የእመቤታችን የአሳብ ልዕልና  የተገለጠበት ወንጌል መሆኑን መስክረዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ አንዱን ሐረግ “ይህንን ሁሉ ነገር” የሚለውን እንመልከት፡፡

ነገር ምንድን ነው)
ነገር ብዙ ነገርን ያመለክታል፤ መጻሕፍት ነገር ሲሉ ልዩ ልዩ ምስጢራትን ያመለክታል፡፡ ለዓብነት ያህል የሚመለከተውን መመልከት ይገባል፡፡

1.    ነገር ምስጢር ነው፡፡
ለብዙ ሰው የማይነገር፣ አንድ ሰው በኅሊናው የሚይዘው፣ በልብ የሚደመጥ በአዕምሮ የሚነከር፣ ልመና፣ ርዳታ፣ ምሥጢር፣ ምሥክርነት፣ የርኅራኄ ሁሉ ቃል፣ ይህንና የመሳሰለው ሁሉ ነገር ይባላል፡፡ የአገራችን ሰው «አንድ ነገር አለኝ´ ሲል ሽምግልና ሊሆን ይችላል፤ ተግሳጽ ሊሆን ይችላል፤ ጥያቄ ሊሆን ይችላል፤ መልስ ሊሆን ይችላል፤ ቁጣ ሊሆን ይችላል፤ ምሕረት ሊሆን ይችላል፤ ቸርነት ሊሆን ይችላል፤ ይህንንና የመሳሰለው ሁሉ መደቡ ነገር ነው፡፡ ነገር ሰውየው በያዘው መጠን ይገለጣል፡፡ እግዚአብሔር በሰው ልቡና ውስጥ ያስቀመጠው ነገር ብዙ ነውና፡፡

2ኛ. ነገር በሰው ልቡና ውስጥ ያለ አሳብ ነው
የአገራችን ሰው አተያይን አይቶ፤ አካሄድን መርምሮ ይሄ ሰው ነገር ፈልጎኛል ይላል፡፡ ባለው ግንኙነት ላይ ተመሥርቶ ብቀላ ይሁን፣ ጥላቻ፣ መርገም ይሁን፣ ስጦታ፣ ወይም ሌላ፤ ባለው የፍቅር ግንኙነት ላይ ተመሥርቶም ይሁን ከዚህ ውጭ በአንድ ቋንቋ ተጠቃልሎ ነገር ብሎ ይጠራዋል፡፡

የቅዳሴ ማርያም ደራሲ አባ ሕርያቆስ ልቡናየ በጎ ነገርን አወጣ በማለት ድርሰቱን ይጀምራል፡፡ ያ በጎ ነገር በቅዳሴ ማርያም ውስጥ ተጠቃልሎ የቀረበ ነው፡፡ በዚያ ቅዳሴ ውስጥ ምን አለ) ወአነ አየድዕ ቅዳሴሃ ለማርያም አኮ በአብዝኆ አላ በአውኅዶ፡፡ ወአነ አየድዕ ውዳሴሃ ለድንግል አኮ በአንኆ በቃለ ዝንጋዔ አላ በአኅጽሮ ወአነ አየድዕ እበያቲሃ ለድንግል፡፡  እኔም የድንግልን ገናናነነቷን እናገራለሁ በማብዛት አይደለም በማሣነስ ቃል እንጂ ብሎ ነገረ ማርያምን፤ ወእቀውም ዮም በትሕትና  ወበፍቅር  በዛቲ ዕለት ቅድመ ዝንቱ ምስጢር  ብሎ ምስጢረ ቁርባንን፤ ኦ ማርያም በእንተዝ ናፈቅረኪ ወናዐብየኪ  እስመ ወለድኪ ለነ መብልዐ ጽድቅ ዘበአማን ወስቴ ሕይወት ዘበአማን፤ ማርያም ሆይ የሕይወት መብልን የሕይወት መጠጥን ወልደሽልናልና ከፍ ከፍ እናደርግሻለን በማለት /ምስጢረ ስጋዌን / ነገረ ቅዱሳንን፣ ተልእኮ ሐዋርያትን፣ ምልጃ ጳጳሳትን፣ ነገረ ሊቃውንትን፣ ሃይማኖተ ሠለስቱ ምእትን፣ ሃይማኖታቸው የቀና ቀሳውስትን፣ ዲያቆናትን፣ ደናግልን፣ መነኮሳትን ፣ መኳንንትን ፣ መሳፍንትን፣ በቀናች ሃይማኖት ያረፉ አበውንና እመውን፣ የሃይማኖት አርበኞችን አዳምን፣ አቤልን፣ ሴትን፣ ሄኖክን፣ ኖኅን ሴምን፣ አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብን፣ ዮሴፍን፣ ሙሴን፣ አሮን ካህንን፣ ጌዴዎንን፣ ኢያሱ መስፍንን፣ እሴይን፣ አሚናዳብን፣ ሰሎሞን፣ ኤልያስን፣ ኤልሳዕ ነቢይን፣ ኢሳይያስን፣ ዳንኤልን፣ ዕንባቆምን፣ ሕዝቅኤልን፣ ሚክያስን፣ ሲሎንዲስን፣ ናሖምን፣ ዘካርያስን፣ ያነሣበትን ቃል በመጠቅለል ነገር በማለት ይጠራዋል፡፡ በዚህ የቅዳሴ ቃል ምስጢረ ሥላሴ አለ፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም አስቀድሞ ልቡናየ በጎ ነገርን አወጣ ብሎ ነበረ፡፡ በመዝሙረ ዳዊት ስለ ጽድቅ፣ ስለ ክብርና አሳር፣ ስለ ፍቅርና ጥላቻ፣ ስለ ዘላለም ጽድቅና ኩነኔ፣ ስለ ክፋትና በጎነት፣ ስለ መልካምነትና ክፋት፣  ስለ ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ ፣ ምሥጢረ ጥምቀት፣ ምሥጢረ ቁርባን ፣ ምሥጢረ ትንሣዔ ሙታን፣ ሁሉ ተጠቅልሎ ቀርቧል ይህ ሁሉ ምሥጢር በአንድነት ተጠቃልሎ ነገር ይባላል፡፡

3ኛ. ነገር ታሪክ ነው፡፡
መጽሐፍት ነገር ሲሉ ታሪክ ማለታቸው ነው፡፡ ነገረ ማርያም፣ የእመቤታችን ታሪክ የተጠቀለለበት መጽሐፍ ነው፡፡ ነገረ ክርስቶስ የክርስቶስን ነገር የሚናገር፤ ነገረ ሥላሴ የሥላሴን ነገር የሚናገር፣ ነገረ መላእክት፣ እንዲህ እያልን የምንናገረው ነገር ታሪክን የሚናገር ነው፡፡

4ኛ. ነገር ምስጢር ነው
ምሥጢር ብዙ ወገን ነው፡፡ የሚነገርና የሚገለጥ አለ፤ የማይነገርና የማይገለጥ አለ በአንድነት ተጠቃልሎ ነገር በማለት ይጠራል፡፡ ምሥጢር ለሁሉም ወገን አይነገርም፤ ለምሳሌ የሃይማኖት ምሥጢር በእምነት ለተጠሩ፣ ሰማያዊውንና መንፈሳዊውን ነገር ለሚረዱ፣ ከሥጋ ፈቃድና አሳብ በላይ ለሆኑ እንደ መንፈስ ፈቃድ ለሚመላለሱ ወገኖች እንጂ ለሁሉ ሰው የሚነገር አይደለም፡፡ ምሥጢር የማይነገረው በሚከተሉት ዓበይት ምክንያቶች ነው፡፡

ሀ. የሚሰጠው ጥቅም ከሌለ አይነገርም፡፡
ለ. የሚቀበለው ሰው አቅም ከሌለው አይነገርም፡፡
ሐ. ተናጋሪውና ሰሚው በእርግጠኝነት የማይደርሱበት ከሆነ አይነገርም፡

ልደተ ወልድ እም አብ ምጽአተ መንፈስ ቅዱስ እም አብ ኢይትነገር አላ ይትነከር፡፡ የወልድ ከአብ መወለድ፤ የመንፈስ ቅዱስ ከአብ መሥረጽ ይደነቃል እንጂ አይነገርም፡፡ ይህ ሁኔታ በሊቃውንት ውስጥ የሚኖር ነው፡፡ ይሄንን የሚመስል ሌላም ነገር አለ፡- በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ  የቆጵሮስ  ሊቀጳጳስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሦስቱ በእግዚአብሔር የዝምታ ሸማ የተጠቀለሉ ድብቅና ጣፋጭ ምሥጢራት በማለት የሚገልጣቸው ነገሮች አሉ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡፡

1.    የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘላለማዊ ድንግልና
2.    አማኑኤል ጌታን መውለዷ
3.    የማይሞተው አምላክ ሞት ናቸው፡፡

አስቀድመን ካነሣነው ነገር ተነሥተን የምንደርስበት ድምዳሜ አለ እርሱም በመጠን የሚነገር ፣ በመጠን የማይነገርና ፈጽሞ የማይነገር፣ መኖሩን ነው፡፡ ፈጽሞ የማይነገረው ነገር ምክንያቱ መጠኑና ልኩ ስለማይታወቅ ነው፡፡ በመጠን የሚነገር ያልነው በሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤልና የጌታ እናት በምትሆን በቅድስት ድንግል ማርያም መካከል የነበረውን ዓይነት ነገር ነው፡፡ ቅድስት ድንግል መልአኩን ሴት ያለ ወንድ ምድር ያለ ዘር ታብቅል የሚለውን ጥያቄ ከየት አገኘኸው ብላ በጠየቀችው ጊዜ የቅዱስ ገብርኤል መልስ የተነገረው በመጠን ነው፡፡ እርሱም «ለእግዚአብሔር የሚሣነው ነገር የለም ´ የሚል ነው፡፡

መልአኩ ከዚህ በላይ መሄድ አልፈለገም፡፡ ሥጋዊ ባሕርይ ሌላ መለኮታዊ ባሕርይ ሌላ ነው፤ በሊቃውንት የሚተነተነው ነገር የሚደነቅ እንጂ የመለኮትን ባሕርይ የሚገልጥ አይደለም፡፡ የተሸፈነ ምሥጢር አለ ሰው ሊረዳው የማይችል፣ የማይገነዘበው ምሥጢር፣ እጹብ እጹብ በማለት የሚያደንቀው ምሥጢር፡፡ አሁን ወደ ዋናው ነገር እንምጣ፡-
እናቱም ይህን ነገር ሁሉ ትጠብቀው ነበር አለ ወንጌላዊው፡፡ ወንጌላዊው ይህን ሁሉ ነገር በማለት የተናገረው ነገር ምንድን ነው)

ይህን ሁሉ ነገር
    ከቤተ መቅደስ ይጀምራል፡፡ አስቀድሞ በቤተ እሥራኤል ደናግል በቤተ መቅደስ የሚቀመጡበት ልማድ አልነበረም፡፡ በርግጥ በኦሪቱ ነቢይት በቤተ መቅደሱ ታዛ ነበረች፡፡ የነቢይቱ በቤተ መቅደስ መኖርና የአምላክ እናት በቤተ መቅደስ መኖር ይለያያል፡፡ ነቢይቱ በቤተ መቅደስ የነበረችው በራሷ ምርጫ ስለ ራሷ ኃጢአት ተገብታ ነው፤ ቅድስት ድንግል ማርያም ግን በአምላክ ምርጫ ነው፡፡ ነቢይቱ በምናኔ ነው፤ እመቤታችን ግን ካህናቱ ተቀብለው መላእክት ምግቧን አቅርበው ነው፤ ስለዚህም ነው አባ ሕርያቆስ ኦ ድንግል አኮ ኅብስተ ምድራዌ ዘተሴሰየኪ አላ ኅብስተ ሰማያዌ እምሰማየ ሰማያት ዘበሰለ፡፡ ኦ ድንግል አኮ ስቴ ምድራዊ  ዘሰተይኪ፤ አላ ስቴ ሰማያዊ እምሰማየ ሰማያት ዘተቀድሐ፡፡ ድንግል ሆይ ምድራዊ ኅብስትን የተመገብሽ አይደለም ከሰማየ ሰማያት የተገኘ ነው እንጂ፡፡ ድንግል ሆይ ምድራዊ መጠጥን የጠጣሽ አይደለም ከሰማየ ሰማያት የተቀዳ ነው አንጂ፡፡ በማለት የሚያመሰግናት፡፡ ይህንን ሁሉ ነገር በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር፡፡

     ዐሥራ አምስት ዐመት ሲሞላት አይሁድ በምቀኝነት ከቤተ መቅደሳችን ትውጣልን አሉ፡፤ ልማደ አንስት በእርሷ እንደሌለ እያወቀች ንጽሕናዋን አልተከላከለችም፤ አልተቃወመችም እኔ እንዲህ ነኝ፣ እንዲያ ነኝ አላለችም፡፡ ቤተ መቅደሱን ለቃላቸው ወጣች ይህን ሁኔታ የሚያውቀው ወንጌላው ጥቅልል አድርጎ ይህንን ሁሉ ነገር በማለት ገለጠው፡፡

    በድንግልና ተወስና አምላኳን ለማገልገል ቁርጥ ኅሊና ኖሯት ሳለ የዐሥራ ሁለቱ ነገደ እሥራኤል በትር ተሰብስቦ ተጸልዮ ዕጣው ለዮሴፍ ወጥቶ ወደ ዮሴፍ ቤት መሄዷን አልተቃወመችም፡፡  በኅሊናዋ ታሰላስለው ነበር፤ ጥያቄ አንስታ አታውቅም፤ ይህን ሁሉ ነገር  በአንክሮ ትከታተለው ነበር፡፡

    የመልአኩ ብስራት ትጸንሲ ሲላት  በድንግልና ለመኖር የወሰነች ስለነበረች ይህ አንዴት ዓይነት ሰላምታ ነው ብላ አሰበች፤ መልአኩ በድንግልና ጸንሳ በድንግልና እንደምትወልድ ሲነግራት እንደቃልህ ይደረግልኝ እኔ የእግዚአብሔር ባሪያው ነኝ ያለችውን ነገር ሁሉ በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር፡፡

    ከጸነሰች በኋላ ዮሴፍ  መኑ ቀረጸ አክናፈ ድንግልናኪ ብሎ በጠየቃት ጊዜ መልአኩ ገብርኤል አክብሮ ከነገረኝ ነገር በስተቀር ሌላ እንደማላውቅ እግዚአብሔር ያውቃል  የሚለውን ነገር ሁሉ በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር፡፡

    ከዚያም በኋላ በቤተልሔም አማኑኤል ጌታን ስትወልድ እንስሳት ሲያሟሙቁት፣ እረኞች ሲያገለግሉት፣ ነቢይቱ ሐና ስታመሰግነው፤ ስምዖን በቤተ መቅደስ ስለ ሕፃኑ ትንቢት ሲናገር ይህ ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ምልክት ሆኖ ተሾሟል፤ በአንቺም በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል ሲላት ይህንን ሁሉ ነገር በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር፡፡

    በስደቱ ጊዜ የደረሰበትን መከራ፣ ረሃቡን፣ ጽሙን፣ ድካሙን በመንገዷ ሁሉ የፈሰሰውን የሕፃናት ደም እየተራመደች ልጇን ይዛ መሰደዷን በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ ጉድ እንዴት እንዳወጣት በስደቷ ጊዜ የሽፍታ ባህታዊ አዘጋጅቶ እንዴት ልጇን ተቀብሎ እንዳሻገረላት፣ ደንጋዮች ታንኳ ሆነው እንዴት ባሕርን እንዳሻገሯት  ታስተለው ነበር፡፡ ልጇን ልተተ ሕፃናት ፈጽሞ እንዴት እንዳደገ፣ በነፋስ አውታር በደመና ዐይበት ውኃ ቋጥሮ እንዴት እንዳገለገላት፤ ልጇ በፀሐይ በነፋስ አውታር እንዴት እንደተራመደ እየተመለከተች ይህንን ሁሉ ነገር በልቡናዋ ትጠብቀው ነበር፡፡

     በዐሥራ ሁለት ዓመቱ በሊቃውንት መካከል ተገኝቶ ሲከራከር ሊቃውንቱን ሲያስደምም ታስተውለው ነበር፡፡

    ከሊቶስጥራ እስከ ጲላጦስ አደባባይ ከዚያም እስከ ቀራንዮ አደባባይ የተፈጸመበትን ነገር ሁሉ ታስተውለው ነበር፤ ይህ ሁሉ ተጠቅልሎ ለእርሷ ነገር ነበር፡፡ ይሄንንና የመሳሰለውን ነው ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ እናቱም ይሄንን ሁሉ ነገር በልቧ ትጠብቀው ነበር በማለት የገለጠልን፡፡ ልመናዋ ክብሯ የልጇም ቸርነት ይደርብን አሜን፡

ማክሰኞ 9 ዲሴምበር 2014

ቀንሰናል?! እንዴት?! ለምን?!


አትም ኢሜይል

ኅዳር 25 ቀን 2007 ዓ.ም.
ባሳለፍናቸው ሳምንታት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ልዩ ልዩ አስተዳደራዊ ጉባኤያትንና ውሳኔዎችን አስተላልፋለች፡፡ የመጀመሪያው ቅዱስ ፓትርያርኩ በአዲስ አበባ ከሚገኙ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች ጋር «በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተዳደራዊ አስተሳሰብን ማበልጸግ» በሚል መሪ ቃል ያደረጉት ጉባኤ ነው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፭ በተደነገገው መሠረት የተደረጉት ሠላሳ ሦስተኛው መደበኛ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ እና የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ምልአተ ጉባኤ ናቸው፡፡

በእነዚህ ጉባኤያት በርካታ ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚመለከቱ ወሳኝ ጉዳዮች ተነሥተዋል፡፡ በተለይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ድረ ገጽ ላይ ከወጡት የድምፅ ወምስል ክሊፖች ለመረዳት እንደሚቻለው /በዚህ መምሪያው ሊመሰገን ይገባል/ ሁሉንም ጉባኤያት የመሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በቤተ ክርስቲያኗ የዛሬ ሐዋርያዊ እንቅስቃሴና የነገ ገጽታ ላይ ከፍተኛ አደጋ አምጥተዋል የሚባሉ መሠረታዊ ጉዳዮችን ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡

ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግሮች ተብለው በቅዱስነታቸው ከተነሱት ጉዳዮች አንዱና ዋናው የቤተ ክርስቲያኗ ምእመን ቁጥር መቀነስ የሚል ነው፡፡ ይህ ችግር ቤተ ክርስቲያኗም ይሁን በሥሯ ያለ ማንኛውም አካል በግልጽ አንሥቶት የማያውቅ ከባድና ሁሉንም የሚያሳስብ ጉዳይ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ቢያንስ በመምሪያው ድረ ገጽ ከተቀመጠው የድምፅ ወምስል ሰነድ ለመረዳት እንደሚቻለው በቅዱስ ፓትርያርኩ በቀረቡት ችግሮች ላይ በጉባኤው በቂ ውይይት ተደርጎባቸዋል ማለት አይቻልም፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መሰብሰቢያ አዳራሽ ከተደረገው ጉባኤ ለመረዳት እንደተቻለው ቅዱስ ፓትርያርኩ አሳሳቢ ነው ብለው ባነሡት በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲወያዩና የመፍትሔ ዐሳብ እንዲያቀርቡ የተጋበዙት ጉባኤተኞች ውኃ የሚቋጥር ዐሳብ ሊሰጡበት አልቻሉም፡፡

የተነሣው አሳብ በእርግጥ እውነት ከኾነ የቤተ ክርስቲያኗን አካላት በምልአት ሊያሳስብና ሊያስጨንቅ ይገባ ነበር፤ ነገር ግን ጉባኤተኞቹ ይህንን ዐቢይ ጉዳይ ትተው ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ የአስተያየታቸው ትኩረት በቅዱስ ፓትርያርኩ የመግቢያ ንግግር ወደ መጨረሻ በተነሣው የማኅበራት በተለይም ማኅበሩ እያሉ ሲያብጠለጥሉት በነበረው ማኅበረ ቅዱሳን ላይ ብቻ ነበር፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ሕገ ቤተ ክርስቲያንን በማክበር በቅዱስ ሲኖዶስ ታውቆ፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ መዋቅር ታቅፎ፣ በጎ ሕሊና ያለው ሰው ሁሉ ሊመሰክረው የሚችለው ለቅድስት ቤተ ክርስ ቲያን ወቅታዊነት ያለው ሰፊ አገልግሎት እየሰጠ ያለ ማኅበር ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአስተያየት ሰጪዎቹ የምቀኝነትና የጥላቻ ንግግር ማኅበሩ የበለጠ ጠንክሮ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ያነሧቸውን ዐበይት ችግሮች በመፍታት ሒደት አሁን ከሚያደርገው የበለጠ የድርሻውን እንዲወጣ የሚያበረታታ ሳይሆን አገልግሎቱን ሽባ ለማድረግ የ«ስቅሎ፣ ስቅሎ» ዓይነት ውትወታ ነበር፡፡ ለማንኛውም በዚህ ጉዳይ ላይ ማተት የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አይደለም፡፡ ዓላማው ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ልንወያይባቸው ይገባል ብለው ካቀረቧቸው ወቅታዊ ችግሮች ከላይ በተጠቀሰው የምእመናን ቁጥር መቀነስ ላይ መጠነኛ አስተያየት ለመስጠት ነው፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሁሉም ጉባኤያት መክፈቻ ንግግሮቻቸው ላይ ስለ ቤተ ክርስቲያኗ ምእመናን ቁጥር መቀነስ፣ የቀነሰውም በቤተ ክርስቲያኗ ታቅፈው ሲያገለግሉና ሲገለገሉ የነበሩ ምእመናን በልዩ ልዩ ምክንያት እናት ቤተ ክርስቲያናቸውን ትተው ወደ ሌሎች በመሔዳቸው እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ግንዛቤአቸው መረጃ አድርገው ያቀረቧቸው በ1987 ዓ.ም. እና በ1999 ዓ.ም. በመንግሥት የተደረጉ ሁለት የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤቶችን ነው፡፡

በመሠረቱ እንደ ቤተ ክርስቲያን በመንግሥት ከተደረገው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት ተነሥቶ ይህንን ማለት ሊከብድ ይችላል፡፡ እንደሚታወሰው ቅዱስ ፓትርያርኩ በንግግራቸው በመረጃነት የጠቀሱትን የ1999 ዓ.ም. የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት ቤተ ክርስቲያን በኦፊሴል ልትቀበለው እንደምትቸገር ገልጻ ነበር፡፡ በወቅቱ ቤተ ክርስቲያኗ ያቀረበቻቸው የመከራከሪያ ነጥቦች በቆጠራው ከስምንት መቶ በሚበልጡ ገዳማት፣ ከ1000 በሚበልጡ አብነት ት/ቤቶች የሚገኙ መነኮሳትን፣ መነኮሳዪያትን እንዲሁም ተማሪዎችን አላካተተም፣ በአንዳንድ ክልሎችና ከተሞች ከተደረገው ቆጠራ የመጣው ውጤትም ተአማኒ አይደለም የሚሉ ነበሩ፡፡

በዚህም የተነሣ፤ ምንም እንኳን ባትተገብረውም፤ በወቅቱ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ በራሷ በጀትና መንገድ ምእመኗን እንደምትቆጥር አሳውቃ ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የቤተ ክርስቲያኗ ምእመናን ቁጥር ቀንሷል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም፤ ወይም ለመናገር ጥቂት የጥናት ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያ ርኩ በግልጽ ችግሩ እንደነበረና አሁንም ቀጥሎ የሚታይ እንደኾነ አንሥተዋል፡፡ አያይዘውም የቤተ ክርስቲያኗ አባቶች ይህንን ብለን ብንወያይ ሌሎች ይሳለቁብናል ማለትን ትተው «በሽታውን የደበቀ መድኀኒት የለውምና በግልጽ እንወያይ» ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በመሠረቱ በሁሉም ጉባኤያት እንደተገለጸው የቤተ ክርስቲያኗን ደማቅ ሐዋርያዊ ጉዞ የሚገዳደሩ ጉዳዮችን በግልጽ አንሥቶ መወያየት፣ ሁሉንም የሚያስማማ ጠቃሚ የውሳኔ አሳብ ማሳለፍ፣ ለውሳኔው ተግባራዊነት መትጋት ቤተ ክርስቲያኗን እንዲመሩ ከተቀመጡ አባቶች የሚጠበቅ ነው፡፡ በመሆኑም ምናልባት በጉዳዮች ላይ ግልጽ ውይይት መደረግ መጀመሩ የሚያስደስት ነው፡፡ ባሕሉ በደረጃ ወደ ሁሉም የቤተ ክርስቲያን አካላት /ካህናት፣ ምእመናን፣ አገልጋዮች ወዘተ./ ወርዶ ተግባራዊ ሊኾን ይገባል፡፡

ይህ ጉዳይ በቤተ ክርስቲያኗ ከፍተኛ የአስተዳደር ጉባኤያት በይፋ ተገልጾ ውይይት ሲደረግበት በቤተ ክርስቲያን ልጆች አእምሮ ሊነሣ የሚችለው ጥያቄ «በእርግጥ ቀንሰናል እንዴ?» የሚል እንደሚኾን ግልጽ ነው፡፡ ይህ ጥያቄአችን አዎንታዊም ይሁን አሉታዊ መልስ የሚያገኘው በጉዳዩ ላይ ተጨባጭ ጥናት ሲደረግ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ረገድ ሊካዱ የማይችሉ እውነታዎችን ማንሣት ይቻላል፡፡ ዛሬ በግልጽ ከመታወቅ አልፈው በተለያዩ ጊዜያት ውይይት ከተደረገባቸውና ሊደረግባቸው ከሚገቡ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ችግሮች በመነሣት ጥቂት ቁጥር ያላቸው ምእመናን ከነበሩበት ቦታ እንደሌሉ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ ሁሉንም ያሳሰቡ አስተዳደራዊ ችግሮች ካልተቀረፉ ዛሬ ጥቂት ያልናቸው ምእመናን ተበራክተው በነበሩበት ላናገኛቸው ሊሸሹ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ የተወሰኑ ምእመናን ርቀውናል ስንል ቃሉ ሊያሳብቅ እንደሚችለው ሁሉም ቤተ ክርስቲያኗን ሙሉ በሙሉ ትተው ወደ ሌላ እምነት ሔደዋል ማለት አይደለም፡፡ በመሆኑም ዛሬ በልዩ ልዩ ምክንያት በነበሩበት የሌሉ ምእመናንን በሚከተሉት አራት ክፍሎች መድበን ማየት እንችላለን፡፡

1. አገልግሎት ያቆሙ፡-
የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት ከነሙሉ ሙቀቱና ምልአቱ ትውልድን ተሻግሮ ለእኛ የደረሰው፤ በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ፍቅርና ትምህርት ተስበው ባላቸው ሁሉ ባገለገሉ ምእመናን ነው፡፡ በየዘመኑ ከተጻፉ መጻሕፍት እንደምንገነዘበው እነዚህ ምእመናን በገንዘባቸው፣ በጉልበታቸው፣ ነፍሳቸውን ለሕልፈት በመስጠት ጭምር ቤተ ክርስቲያኗን ሲያገለግሉ ድጋፍና ኃይል የሆናቸው የአባቶች የሕይወት ጥንካሬ፣ ለልጆቻቸው የነበራቸው ፍቅርና ክብካቤ ነበር፡፡

ምእመናንን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመጡ የሚያደርግ የአበው መልካም የሕይወት ፍሬ ዛሬ ፈጽሞ የለም ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ ዛሬም ቢሆን ምንም እንኳን መጥፎው ጎልቶ እየታየ ማንነታቸውን የከለለ ቢመስልም ስለ እውነት ሕይወታቸውን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሰጡ፣ ምእመናንን በስስት የሚመለከቱ አባቶች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም እንደሚያውቀው ዘመኑ ካባው ለቤተ ክርስቲያኗ አገልግሎት፣ ለምእመናን ሕይወት ግድ የሌላቸው የትንቢት መፈጸሚያ የሆኑ አንዳንድ ግለሰቦች በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ተሹመው እዚህም እዚያም የሚገኙበት ነው፡፡

በእነዚህ ግለሰቦች መጥፎ ሥነ ምግባር የተነሣም እንደ ቅዱስ ፓትርያርኩ አባባል በሁሉም የአገልግሎት ትጋታቸው ከፊት ቆመው የነበሩ በርካታ ምእመናን «የመንፈስ ስብራት እየደረሰባቸው» ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያላቸውን የጸሎት ግንኙነት ሳያቆሙ በየቦታው ራሳቸውን ከአገልግሎት አግልለዋል፡፡ የእነዚህን ምእመናን ቁጥር በተወሰነ ደረጃ ለማወቅ በተለይ በአዲስ አበባና ታላላቅ ከተሞች በሚገኙ አጥቢያዎች በሰበካ ጉባኤና ልማት ኮሚቴ አባልነት ታቅፈው ሲያገለግሉ የነበሩ ምእመናን ዛሬ ያሉበትን ሁኔታ ቀረብ ብሎ ማጥናት ይበቃል፡፡ ቤተ ክርሰቲያን በሰጠቻቸው ሥልጣን የምእመናን ገንዘብ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ይዋል ብለው ሹማምንቱን የሞገቱ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የቤተ ክርስቲያን ልጆች በደረሰባቸው ጫናና ግፊት ከአገልግሎት ራሳቸውን አግልለው ታዛቢ ሆነዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያን ሙስና ይጥፋ፣ ብልሹ አስተዳደር ይስተካከል ብለው የሚታገሉ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉ የአገልግሎት ተቋማትም የሌለ ስም እየተሰጣቸው የሚሳደዱት አገልግሎታቸውን አቁመው ዘወር እንዲሉና ቤተ ክርስቲያኗ ያሰቡትን ለማድረግ የተመቸች ለማድረግ ነው፡፡ ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ ምናልባት ነገ ከነገ ወዲያ ወዶና ፈቅዶ ሊያገለግል ወደ ቤተክርስቲያን የሚመጣ እንዳይጠፋ ያሰጋል፡፡

2. ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመሔድ የታቀቡ፡-
በግል የሥራ ጫናና ድካም የተነሣ ዕለት ዕለት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔደው ከአምላካቸው ጋር የማይገናኙ እንዳሉ ሁሉ፤ በቤተ ክርስቲያን በሚያዩአቸው ችግሮች በመሳቀቅ ቤት መጸለይን እንደ አማራጭ የወሰዱ ምእመናንም በርካታ ናቸው፡፡ ምእመናን ቃሉ ይሰበክበት ዘንድ በሚገባው ቅዱስ ቦታ ግለሰቦች ሲሰበኩበት፣ ቤተ ክርስቲያንን በደሙ በመሠረተልን መድኀኔዓለምና እሱ በመረጣቸው ቅዱሳን ፋንታ ሹማምንቱ ሲወደሱበትና የሌላቸው ሕይወት ሲሰበክበት ሲመለከቱ ቅዱስነታቸው እንደተናገሩት መንፈሳቸው ይሰበራል፡፡ በመሆኑም የሚበረታታ ባይኾንም የቤተ ክርስቲያናቸው ድምፅ እየናፈቃቸው፣ መዓዛ ቅዳሴውና ዕጣኑ ውል እያላቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን መሔድን በመሰቀቅ ቤታቸው ተወስነው የተቀመጡ ምእመናን በርካታ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

3. እምነትን ያቆሙ፡-
እምነት ቃሉን ተረድቶ በቃሉ ባለቤት አምኖ እንደቃሉ የሚኖሩት ሕይወት ቢሆንም፤ ሰው አይተው ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡ፣ ሰውን ተደግፈው በቤተ ክርስቲያን የሚኖሩ ሰዎች መኖራቸው ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ያለ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ለሚኖራቸው ጥንካሬ መሠረቱ የሚያዩአቸውና የሚደገፏቸው ሰዎች ጥንካሬ ነው፡፡ ለምእመናን ሕይወት መጠንከር ከፊታቸው ቆመው የሚሰብኳቸው ሕይወት መጠንከርና የሚሉትን ሆነው መገኘት፣ እንዲሁም ቀድሰው የሚያቆርቧቸው፣ የሚናዝዟቸው ካህናት ጥንካሬ ወሳኝነት አለው፡፡

በዐውደ ምሕረቱ በሕይወቱ አርአያ ሆኖ የሚታይ ሲጠፋ የምእመናን ሕይወት አልጫ ይሆናል፡፡ አልጫነቱ ሲበዛ ደግሞ ወደ እምነት አልባነት ይለወጣል፡፡ በዚህ የተነሣ ትላንት በየትኛውም መንገድ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው የእምነትን ሕይወት ዳዴ ማለት የጀመሩ ምእመናን በትምህርት፣ በምክርና በመልካም ሕይወት የሚያንፃቸው ሲያጡ እምነትን ወደ መተው ይሔዳሉ፡፡ በዚህም ረገድ ምንም እንኳን ቁጥራቸው ይህን ያህል ነው ብሎ መናገር ባይቻልም በዚህ ሥር ሊታቀፉ የሚችሉ ምእመናን ሊኖሩ እንደሚችሉ መካድ አይቻልም፡፡

4. እምነታቸውን የቀየሩ፡-
ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን አጠቃላይ ሒደት አማኞችን ከሚገዳደሯቸው በርካታ ምክንያቶች የተነሣ ሙቀትና ሕይወት ከምትሆን የቤተ ክርስቲያን አንድነት ተለይተው ወደ ሌሎች ጓዳ የሚገቡ ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያናችን ካጋጠሟት ውስብስብ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ጋር ሲነጻጸር በዚህ ርእስ ሥር ሊመደቡ የሚችሉት በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡

ከላይ ካየናቸው የምእመናን ሽሽት መገለጫዎች በየትኛውም ይጠቃለሉ ቁጥራቸው ጥቂት ይሁን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ከእናታቸው ሙቀት መራቃቸው ያሳስባል፡፡ ሁላችንንም ዐቅፋ የያዘች ቤተ ክርስቲያን «ክርስቶስ ለአንዲት ነፍስ ሲል ወደ በረሃ ወረደ» የሚለውን ንባብ አመሥጥራ የምትሰብክ ለልጆቿ ተቆርቋሪ እናት ናትና፡፡ በመሆኑም በቅዱስ ፓትርያርኩ ደረጃ እንደዚህ ዓይነት ዜና ሲታወጅ ስንሰማ ሁላችንም ለምን? እንዴት? ብለን መጠየቅ ይገባናል፡፡ መጠየቅም ብቻ ሳይኾን ይህ የሆነበትን ምክንያት ከሥሩ ተረድተን መፍትሔውን በመፈለግ ረገድ በያለንበት ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

ለመሆኑ ጥቂትም ቢሆኑ ምእመናን ለምን ከቤተ ክርስቲያን ራቁ? የራቁት ወደ ቀደመ ቦታቸው እንዲመለሱ፤ ያልሸሹት በቦታቸው እንዲጸኑ ምን ይደረግ? ምእመናንን ከቤተ ክርስቲያን በተለያየ ደረጃ እንዲርቁ በሚያደርጓቸው ምክንያቶች ዙሪያ ያልተባለ ነገር እና ያልተሰጠ የመፍትሔ ዐሳብ የለም፡፡ የችግሩ ተጠቃሚም ኾነ የችግሩ ተጎጅ፣ ችግሩን ለመፍታት ሙሉ ሥልጣን ያለውና ዘወትር ስለ ችግሩ እያወራ ከማልቀስ በቀር ምንም ሊፈይድ ያልቻለው፤ ሁሉም ዛሬ ቤተ ክርስቲያኗን ስለገጠሟት ልዩ ልዩ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ሲናገር ይሰማል፡፡ በአጭሩ የዕውቀት ችግር የለም፡፡ የጠፋው ችግሮቹ የሚቀረፉበትን እርምጃ የመውሰድ ቁርጠኝነት ነው፡፡

ከላይ እንደተገለጠው ቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ዘመን ክፉኛ እንድትፈተን ያደረጓት ምክንያቶች በርካታና የሚታወቁ ናቸው፡፡ አንድም የተባለውን ሁሉ በመድገም መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ ሦስት ምክንያቶችን እናንሣ፡፡

ብልሹ አስተዳደር፡-
ቅዱስ ፓትርያርኩ በመግቢያ ንግግሮቻቸው ለምእመናን መራቅ በምክንያትነት ካነሧቸው ጉዳዮች ውስጥ አስተዳደራዊ ብልሹነት አንዱ ነው፡፡ እንደ ቅዱስነታቸው አገላለጽ ይህ አስተዳደራዊ ብልሽት በምእመናን ላይ ከፍተኛ «የመንፈስ ስብራት» እያደረሰ በመሆኑ ለሽሽታቸው ምክንያት ሆኗል፡፡ ዛሬ ቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደራዊ ብልሽት እየፈተናት ይገኛል ስንል ማብራሪያ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም፡፡ ከላይ እንዳልነው አልሚውም አጥፊዉም ችግሩን እኩል ሲያነሣ ሲጥለው፣ ሲቋጥር ሲፈታው የሚውል ጉዳይ ነውና፡፡

ቅዱስነታቸው ዛሬ ቤተ ክርስቲያኗን ክፉኛ እየተፈታተናት ያለውን የአስተዳደር ብልሽት መገለጫዎች «ወንጌል ከሚያዝዘው የተቃረነ መሥራት፣ ጉቦ መቀበል፣ በዘር በጎጥ በመደራጀት ሰላማዊውን ሰው መበደል፣ ያልደከሙበትን የሕዝብ ሀብት ማባከን፣ ለአገልግሎት በመትጋት ለምእመናን አርአያ አለመሆን፣ ከራስ በላይ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር አለመቆርቆር» በማለት በግልጽ አስረድተዋል፡፡ በእውነቱ ይህ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ምዕራባውያን የችግሩን ምንጭ ማወቅ ከሙሉ መፍትሔው ግማሹን እንደመሥራት ነው እንደሚሉት ዛሬ ቤተ ክርስቲያኗ እንደተቋምና ልጆቿ በየቦታው የሚያዝኑበትን አስተዳደራዊ ችግር በግልጽ ተረድቶ መፍትሔ ያስፈልገዋል በማለት በግልጽ ማቅረብ ይበል የሚያሰኝና በሁሉም የቤተ ክርስቲያኗ መዋቅር ሊለመድ የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

እውነት ነው፤ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ የኾነ አስተዳደራዊ ችግር ይታይባታል፡፡ መሪና ተመሪ በማይታወቅበት ሁኔታ፤ ሀይ ባይ የሌለ እስኪመስል ድረስ በአስተዳደር የተቀመጡ በርካታ አካላት ቅዱስነታቸው እንዳሉት ከወንጌል ፍጹም በተቃረነ ሁኔታ ጉቦ ሲቀበሉ፣ ለምን ብሎ የጠየቀን ሲያሳድዱ፣ ምእመናን እንባቸውን አብሰው ሙዳዬ ምጽዋት በሚጥሉት ሳንቲም የግል ኑሯቸውን ሲያደላድሉ ይታያል፡፡ ይህ የሚደረገው ደግሞ በማን አለብኝነት ፀሐይ እየሞቀው በዐደባባይ፣ ስለሆነ ግድፈቱን የሚያዩ ምእመናን በእጅጉ እያዘኑ፣ የጸኑት ከቤተ ክርስቲያኗ ቅጽር ሳይሸሹ የሚሆነውን እያዩ ዕድሜ ለንስሐ ለሰጠ አምላክ ይጮኻሉ፡፡

በዓይናቸው የሚያዩትንና በጆሯቸው የሚሰሙትን መታገሥ ያልቻሉት ደግሞ ዘወር ማለትን መርጠው መዳረሻቸውን የጸኑት አባቶች የሚገኙባቸውን በሩቅ ያሉ ገዳማት አድርገው ከአምላካቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ቀጥለዋል፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉት ደግሞ በቤታቸው ተወስነው ይጸልያሉ፡፡ ማመን እንዲህ ከኾነ ብለው ከፈጣሪያቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ያቋረጡም እንዳሉ ሊካድ አይችልም፡፡ መማረሩና ማዘኑ ከግል ድካማቸው ጋር ተደምሮ ከቤተ ክርስቲያን ዕቅፍ ወጥተው ወደ ሌሎች የሔዱም አይጠፉም፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው በየደረጃው የሚቀመጡት አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከሚያሳዩት አስተዳደራዊ ጥሰትና ተመዝኖ መቅለል የተነሣ ነው፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ ይህንን ጉዳይ በግልጽ አንሥተው ለውይይት ማቅረባቸው ሊያስመሰግናቸው ይገባል፡፡ ይሁን እንጂ ችግሮቹ መነገራቸው ብቻ አይበቃም፡፡ መፍትሔአቸው ላይ በፍጥነትና በትጋት አቅጣጫ ማስቀመጥና እንዲረባረቡበትም ማድረግ፣ ሰነፎችንና የሚያሰንፉትን ትቶ ጠንክረው የሚያጠነክሩትን ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ በተነሡትም ይሁን ባልተነሡት በርካታ አስተዳደራዊ ችግሮች ላይ አስተዳደራዊ ቁርጠኝነት ከሌለ መቀረፍ ቀርቶ ፈቅ ሊሉ አይችሉም፡፡

ቅዱስነታቸው ካለባቸው ሓላፊነት ተነሥተው እንወያይ ብለው ቁልፍ ችግሮችን በግልጽ ሲያስቀምጡ፤ በቅዱስ ፓትርያርኩ በተመራው ጉባኤ የተሳተፉት የተወሰኑ ቡድኖች ጉዳዩን ወደዬት አቅጣጫ ወስደው ቤተ ክርስቲያኗን በማይጠቅም ሁኔታ በማይመለከታቸው ጉዳይ ሲማስኑ እንደነበረ ተመልክተናል፡፡ በቆራጥነት ዛሬ ስላለው አስተዳደራዊ ችግር በግልጽ ሲነገር፣ መፍትሔም ያስፈልጋል ሲባል ጩኸት እንደሚበዛ፣ የሌለ አጀንዳ ፈጥሮ የሁሉም ትኩረት ከዋናው አጀንዳ እንዲያፈነግጥ ማድረግ ሁልጊዜ የሚታይ መሆኑን ከተደረገው ውይይት መረዳት ይቻላል፡፡ ይህንን ተረድቶ ወደፊት በተመሳሳይ ጉዳዮች የሚደረጉ ውይይቶች ጥናትን መሠረት ያደረጉና ሊያመጡት የሚገባ ውጤትም ቀድሞ የተቀመጠ ሊሆን ይገባል፡፡

በአስተዳደር ረገድ የተነሣው ሌላው ጉዳይ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ዘመኑን የዋጀ አለመኾኑን ነው፡፡ እንደ ቅዱስ ፓትርያርኩ ገለጻ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር አሁን ዘመኑ ከሚጠይቀው አንጻር ወደ ኋላ የቀረ ነው፡፡ እውነት ነው ለሀገር የአስተዳደር ሥርዓትን እያስተማረች ሕዝብን እያዘመነች ዛሬ የደረሰች ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ዘመን ካመጣው አስተዳደራዊ ስልት እንኳን መማር አቅቷት የሁሉም መሳለቂያ ሆና እናያለን፡፡ ቅዱስነታቸው እንዳሉት የቤተ ክርስቲያኗን አስተዳደራዊ አሠራር ማዘመን ደግሞ ከመሪዎች የሚጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ቤተ ክርስቲያኗ በዘመናዊ አሠራር የታገዘ ሰማያዊ አገልግሎት እንድትሰጥ የሚመኙትን ሁሉ ያስደሰተ እንቅስቃሴ ተሰምቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ዘመናዊው አሠራር ሲመጣ ጥቅማችን ይቀርብናል ባሉ አካላት ጩኸት የጥረቱ ውጤት የት እንደደረሰ ሳንሰማ፤ በአንጻሩ እንቅስቃሴው አንዱ የማኅበረ ቅዱሳን መወንጀያ ሲኾን እናያለን፡፡

ትምህርት፡-
ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን በጉያዋ አቅፋ በሙቀቷ ከምትይዝባቸው መንገዶች አንዱ ትምህርት ነው፡፡ የሰፋውና የጠለቀው ዕውቀቷ በተጉ ልጆቿ አማካይነት እየተቀዳ ለምእመናን ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በትምህርት የጠገቡ ልጆቿም እናታቸውን አቅፈው በእናታቸውም ታቅፈው ኖረዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ የተረከብናት ቤተ ክርስቲያናችን ከገጠሟት ችግሮች አንዱ ትምህርተ ሃይማኖቷ፣ ሥርዓተ እምነቷ፣ ታሪኳና ትውፊቷ ሁሉ በአግባቡ ከምንጩ ተቀድቶ ያለመሰጠቱ ችግር ነው፡፡ ነገር ግን ዛሬ ይህ ትምህርትን በአግባቡ የማዳረስ ችግር፤ እሱንም ተከትሎ የምእመናን መራቅ የተከሰተው ሊቃውንት ጠፍተው አይደለም፡፡ ቅዱስነታቸው በንግግሮቻቸው እንዳሉት ሊቃውንቱን የሚከባከብና የሚያሰማራ አስተዳደር በመጥፋቱ ነው፡፡ የአስተዳደራዊ ብልሽት መገለጫዎች ከሆኑት አንዱ በቤተ ክርስቲያኗ ለዕውቀትና ለዐዋቂዎች የሚሰጠው ቦታ እየቀነሰ መምጣቱ ነው፡፡

በየጉባኤ ቤቱ ደክመው ዕውቀትን በጠዋት የሰነቁ ሊቃውንት የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ አጥተው፣ ቃለ እግዚአብሔርን ምግብና ልብስ አድርገው በሥጋ የሚሠቃዩ በርካታ ሊቃውንት ያሏት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በአንጻሩ ዕውቀቱን አይደለም ደጃፉን የማያውቁ ዘመድ ወይም ምላስ ስላላቸው የቤተ ክርስቲያኗ ሙዳይ በሰፊው የተከፈተላቸው ግለሰቦች በርካታ ናቸው፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ በሰጡት አቅጣጫ መሠረት ይህ አሳዛኝ ጉዳይ ካልተስተካከለ እንደተባለው ምእመናን መሸሻቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ውሸቱንም ምኑንም ተናግረው የሚያሳምኑበት አንደበትና ንዋይ ስለሌላቸው ተገፍተው የሚኖሩት ዕውቀት ጠገብ ሊቃውንት ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ዐውደ ምሕረት መምጣት አለባቸው፡፡ ሊቃውንቱ ዝም ስላሉ ወይም እንዲሉ ስለተደረጉ ዐውደ ምሕረቱ ዕውቀት ርቦታል፡፡ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር በየዐውደ ምሕረቱ ስለሚሰጠው ትምህርት ይዘትና አሰጣጥ ስልት እንዲሁም የሰባክያኑ ማንነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ የማስተካከያ እርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡

ሕይወት፡-
ምእመናን ቤተ ክርስቲያናቸውን ወደው የሕይወት መሥዋ ትነት ጭምር እየከፈሉ በዕቅፏ የቆዩት በመሪነት ከተቀመጡት አበው ሕይወት በመማር ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ችግር ላይ ስትወድቅ፣ ሊቃውንቱ ሲሰደዱ ምእመናን እኛ እንቅደም እያሉ መሥዋእትነት እየከፈሉ ቆይተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ከምንም የመጣ አይደለም፡፡ በወቅቱ ምእመናንን ይመሩ ዘንድ በልዩ ልዩ ደረጃ የተሾሙት አባቶችና እናቶች የሕይወት መዐዛቸው የሚስብ፣ ለልጆቻቸው የነበራቸው ፍቅር የሚይዝ ስለነበረ ነው፡፡ ዛሬ ያ ትላንት ምእመናንን እንደ መግነጢስ ዕለት ዕለት ወደ ቤተ ክርስቲያን ይስብ የነበረ የአበው የቅድስና ሕይወትና ፍቅር በብዛት አደጋ ላይ ወድቆ እናያለን፡፡ በዚህ የተነሣ ለምን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደሚመጡ ዕውቀቱ ያነሳቸው ምእመናን ወደ ቤቱ መጥተው የሚስባቸው ሕይወትና ፍቅር ሲያጡ ይሸሻሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያን ሕይወታቸው የማሰነባቸውን ሰዎች አሽቀንጥራ ሳትጥል በዕቅፏ እንዲቆዩ የምታደርግባቸው ልዩ ልዩ ሥርዓት ያላት ስንዱ እመቤት ናት፡፡ ነገር ግን አንዳንድ አገልጋዮች የሕይወታቸው ድቀት ከእነሱ አልፎ በሌላውም እስኪታይ ደርሶ በማይገባቸው ወንበር ላይ ተቀምጠው ሲታዩ ምእመናን ይታወካሉ፡፡ ሲታወኩ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን ይሸሻሉ፡፡ ስለዚህ ቅዱስነታቸው አጠንክረው እንደገለጹት በቤተ ክርስቲያን መሪነት ያሉ ሰዎች ከምንም በላይ ሊመሯት የተሾሙባት ቤተ ክርስቲያን በየዘመኑ የመጡባትን ነፋሳት አልፋ እዚህ የደረሰችው በመሪዎቿ የሕይወት ቅድስናና መልካም አርአያነት መኾኑን ተረድተው ወደ ውስጣቸው ሊያዩ ይገባል፡፡

በአጠቃላይ የዚህ ጽሑፍ መነሻ ቅዱስነታቸው የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች ቁጥር ቀንሷል፤ አሁንም እየቀነሰ ነው፤ ፈጣን የመፍትሔ እርምጃ ካልተወሰደ ወደፊትም ተባብሶ ይቀጥላል በማለት በግልጽ መናገራቸው ነው፡፡ በጽሑፉ እንደተገለጠው እዚህ ድምዳሜ ላይ ደርሶ በግልጽ ለመናገር ጥናት ይጠይቃል፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬ በተለይ በከተማ ባለችው ቤተ ክርሰቲያን ከሚታየውና ከሚሰማው ዘርፈ ብዙ ችግር በመነሣት በርካታ ምእመናን ምንም እንኳን ከቤተ ክርሰቲያን መራቃቸው ትክክል ነው ባይባልም፤ ላለባቸው ፈተና በምክንያትነት እያቀረቡት እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

መራቃቸው ምናልባት ሙሉ በሙሉ እምነታቸውን ትተው ወደ ሌላው ሔዶ በመቀላቀል አይደለም፡፡ ከላይ እንደተገለጠውና በብዛት እንደሚታየው ቀድሞ ከነበሩበት የአገልግሎት ሕይወት በመራቅ ወይም የዕለት ከዕለት ምልልሳቸውን በማቆም በቤታቸው መወሰን ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥ የሚያዩትና የሚሰሙት ነገር ከእምነት ውጭ ያደረጋቸው ወይም እምነታቸውን እንዲቀይሩ ያደረጋቸው አይጠፉም፡፡ ቅዱስነታቸውም እንዳሉት ዛሬ በቤተ ክርሰቲያን ተንሰራፍቶ ያለው ችግር ካልተወገደ ነገ አገልግሎት እርሜ ብሎ የሚቀመጠውና ጠዋት ማታ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚገሠግሠው ምእመን ቁጥር ይቀንሣል፡፡ ከዚህ ጋር ከአምላኩ ጋር ያለውን ግንኙነት አቁሞ እምነት አልባ የሚሆነውና ቤተ ክርስቲያኑን ትቶ ወደ ሌላው የሚነጉደው ምእመን ቁጥር ይጨምራል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ይህንን ከትምህርቷ፣ ከሥርዓቷና ካለፈ ታሪኳ ጋር የማይሔድ ድርጊት ማስቆም አለባት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስንል በየደረጃው በመሪነት ከተቀመጡት አበው ጀምሮ እስከ ምእመኑ ድረስ ማለታችን ነው፡፡ በመሪዎቹና ተመሪዎቹ፣ በአገልጋዮቹና ተገልጋዮቹ አንድነትና መፈቃቀር ዘመናትን አልፋ እዚህ የደረሰች ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በሁሉም ላይ በሚታየው ድካም መፈተን የለባትም፡፡ በቅድሚያ ችግሩን ለመፍታት በራስ ላይ ያለን ችግር መርምሮ በማወቅ ከማስተካከል ጀምሮ በሌላውም ያለው ጉድፍ እንዲወገድ የሚከፈለውን መሥዋዕትነት ሁሉ መክፈል የግድ ይላል፡፡

ስለ ችግር እያወሩ እና መንጋውን በበረቱ እንዳይገባ የሚያደርግ፣ የገባውንም በሰላም እንዳይተኛ የሚያደርግ ባዕድ ጠረን ተፈጥሮ እየጨመረ መምጣቱን እያዩና እየሰሙ ለዓመታት መቀመጥ የቤተ ክርስቲያን ባሕል አይደለም፡፡ አስቀድሞ የምእመናንን ሕይወት የሚበድል፣ የቤተ ክርስቲያንን ሰማያዊ አገልግሎት የሚገዳደር ችግር እንዳይኖር የተግባርና የእውነት ሰው ሆኖ በጸሎትም በምክክርም መታገል ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ ሁሉም በይፋ እያወራቸው ያሉትን ችግሮች መፍታት ከሚመለከተን ሁሉ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ ምእመናን የችግሩ ሁሉ ተሸካሚ እንደመሆናቸው በሰበካ ጉባኤዎቻቸውና በልዩ ልዩ ስብስቦቻቸው በየአካባቢያቸው ያሉትን አስተዳደራዊና ግለሰባዊ ችግሮች ለመፍታት ጥረት ማድረግ አለባቸው፡፡

ከቅዱስነታቸው ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኗን ይመሩ ዘንድ የተቀመጡት አበውም ስለችግሩ ከመናገር አልፈው ውጤት ያለው ሥራ መፈጸሙን በባለቤትነት መምራትና መከታተል ያስፈልጋል፡፡ ለምድራዊ ሀብታቸውና የግል ክብራቸው በመጓጓት በማን አለብኝነት ቤተ ክርስቲያኗን የሚበድሉትና የሚገዳደሩት ዕለት ዕለት በቤተ ክርስቲያን አማካይነት ሕዝቡን የሚባርከውን እግዚአብሔርን መሆኑን ተረድተው ልብ ሊገዙ ይገባቸዋል፡፡

ዓለምን የፈጠረና የሚገዛ አምላክ ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን፤ አሜን፡፡ 

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ከኅዳር 1-15 ቀን 2007 ዓ.ም.

ቅዳሜ 29 ኖቬምበር 2014

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ታቦተ ጽዮን


አትም ኢሜይል
 ኅዳር 19 ቀን 2007 ዓ.ም.
tsion mariam 01እግዚአብሔር አምላክ ሕዝበ እስራኤልንከግብጽ ባርነት ካወጣቸው በኋላ የአምልኮ ሥርዐታትን ይፈጽሙበት ዘንድ የምስክሩን ድንኳን፣ የቃል ኪዳኗ ታቦትንና ለአምልኮ ሥርዐቱ ማከናወኛ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳትን እንዲሠሩ በሙሴ በኩል ታዘው ነበር፡፡ ከቃል ኪዳኗ ታቦት ውስጥም በእግዚአብሔር ጣት ዐሥርቱ ትእዛዛት የተጻፉበት የሕጉ ጽላት፣ አርባ ዓመት ሙሉ እስራኤላውያን በሲና ምድረ በዳ የተመገቡትን መና የያዘች መሶበ-ወርቅ፣ አሮን ለክህነት አገልግሎት ስለ መመረጡ ምስክር የሆነችው ለምልማና ፍሬ አፍርታ የተገኘችው የአሮን በትር ይገኙባታል፡፡(ዕብ.9፡4)

ታቦተ ጽዮን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትመሰላለች፡፡ ይህን ለመረዳት ግን ስለ ታቦተ ጽዮን አሠራርና መንፈሳዊ ትርጉም አስቀድመን ልንረዳ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ታቦተ ጽዮንን እንዲሠራ ብልሃትን፣ ጥበብን፣ ማስተዋልን፣ ዕውቀትን ይለይ ዘንድ መንፈሱን ያሳደረበትን ከይሁዳ ወገን የሆነውን ባስልኤልን መረጠ ፡፡(ዘፀ.25፡9) እርሱም እግዚአብሔር በሰጠው ማስተዋል ከማይነቅዝ እንጨት ርዝመቷ ሁለት ክንድ ተኩል፤ ወርዱዋም አንድ ክንድ ተኩል፣ ቁመቷም አንድ ክንድ ተኩል እንዲኖራት አድርጎ ታቦቷን ሠራት፡፡

በመቀጠል በውስጥም በውጪም በጥሩ ወርቅ ለበጣት፣ ከታቦቷም ዙሪያ የወርቅ አክሊልን አደረገላት፡፡ ካህናት ታቦተ ጽዮንን ለመሸከም እንዲረዳቸውም በአራቱም መዓዘናት በወርቅ የተሠሩ ቀለበቶችንና በእነርሱም ውስጥ የሚገቡ ሁለት መሎጊያዎችን ሠራ፡፡ ከጥሩ ወርቅም የስርየት መክደኛውን በቃል ኪዳን ታቦቷ ላይ በርዝመቷና በወርደዋ ልክ ሠራ፡፡ የስርየት መክደኛውን እንዲጋርዱት አድርጎም ጥሩ ከሆነ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ኪሩቤልን ሠራ፤ በስርየት መክደኛው ግራና ቀኝም አደረጋቸው፡፡ እነዚህ በጥሩ ወርቅ የተሠሩት ሁለቱ ኪሩቤል ፊታቸው ወደ ስርየት መክደኛው ሆኖ እርስ በእርሳቸው የሚተያዩ ተደርገው የተሠሩ ናቸው ፡፡ በዚህ በስርየት መክደኛው በሁለቱ ኪሩቤል መካከል እግዚአብሔር ለሙሴ በመገለጥ ሰው ከባልንጀራው እንደሚነጋገር ያነጋግረው ነበር፤ ለሕዝቡ በደመና አምድ ይታያቸው ነበር፡፡(ዘፀ.25፡22፤33፡8-11)

ወደ ትርጓሜው ስንመጣ ታቦተ ጽዮን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ስትሆን፣ በውስጡዋ የያዘችው የሕጉ ጽላት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ታቦቷ ከማይነቅዝ እንጨት መሠራቷ የጌታን እናት ንጽሕናን የሚያመለክት ሲሆን በውጪም በውስጧም በጥሩ ወርቅ መለበጡዋ የቅድስናዋና ድንግል በሕሊና ወድንግል በሥጋ መሆኗን የሚያስረዳን ነው፡፡

ታቦቷን አራት ሌዋውያን ካህናት ይሸከሟት ዘንድ በግራና በቀን በተዘጋጁ አራት ከወርቅ የተሠሩ ቀለበቶች ሲኖሩአት፤ በነዚያ የወርቅ ቀለበቶች ውስጥ ሁለት መሎጊያዎች ይገቡባቸዋል፡፡ ታቦተ ጽዮንን ለማንቀሳቀስ ሲፈለግ አራት ካህናት በመሎጊያዎቹ ይሸከሟታል፡፡ ይህ ሥርዐት በሰማያትም የሚታይ እውነታ ነው፡፡ የጌታን መንበር ገጸ ንሥር፣ ገጸ ሰብእ፣ ገጸ ላህም፣ ገጸ አንበሳ ያላቸው አርባዕቱ እንስሳት ይሸከሙታል፡፡(ኢሳ.6፡1-5፤ ሕዝ.1፡1-16) እንዲሁም ለአማናዊቷ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያም “የምስራች የሚናገሩ፣ ሰላምንም የሚያወሩ፣ የመልካምንም ወሬ፣ መድኃኒትንም የሚያወሩ፣ ጽዮንንም አምላክሽ ነግሦአል የሚሉ እግሮቻቸው በተራሮች ላይ እጅግ ያማሩ ናቸው” የተባለላቸው የእርሱዋንና የጌታችን ስም ተሸክመው የሚሰብኩ ወንጌላውያን አሏት፡፡(ኢሳ.52፡7)

የስርየት መክደኛው ታቹ መቀመጫው ንጹሐን አንስት ላዩ መክደኛው የንጹሐን አበው ግራና ቀኙ የወላጆቹዋ የሐናና የኢያቄም ምሳሌ ነው፡፡ እርሱን በክንፎቻቸው የጋረዱት ኪሩቤል የጠባቂ መልአክ ቅዱስ ሚካኤልና የአብሣሪው መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ምሳሌዎች ናቸው፡፡

የስርየት መክደኛው ስርየቱ የሚፈጸምበት ስፍራ ነው፡፡ ነገር ግን እውነታውን ስንመለከት በዚህ ቦታ ምንም ዓይነት መሥዋዕት ሲቀርብ እንዳልነበር እንረዳለን፡፡ ይህም በጊዜው አማናዊው መሥዋዕት ገና እንዳልተሠዋ ያስገነዝበናል፡፡ ይህ ስፍራ እግዚአብሔር ለሙሴ የሚገለጥበት ቦታ ነው፤ ከእርሱ ውጪ ሌላ ነገር በእዚያ ላይ ማረፍ የለበትም፡፡ ይህ በራሱ የሚሰጠን አንድ ማስተዋል አለ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን ሊፈጽም ሰው በሆነ ጊዜ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብበት ልዩ ስፍራ እንዳለ ያመላክተናል፡፡ ስለዚህም ይህ ስፍራ ለዚህ እንደተጠበቀ ወይም በዚህ ምሳሌ አማናዊ መሥዋዕት የሚቀርብበት ሥፍራ እንደሚያስፈልግ የሚያሳስብ ነው፡፡ ይህ እንደሆነ ለማመልከት ሲባል ለኃጢአት የቀረበው መሥዋዕት ከታረደ በኋላ ካህኑ ደሙን በጣቱ በመንከር ሰባት ጊዜ በስርየት መክደኛው አንጻር በመገናኛ ድንኳን ውስጥ ይረጨው ነበር፡፡(ዘሌዋ.4፡6) ነገር ግን ይህ ደም ከዚያ ስርየት መክደኛው ላይ አያርፍም ነበር ምክንያቱም በዚህ ስፍራ መቅረብ ያለበት መሥዋዕት መለኮት የተዋሐደው ነፍስ ግን የተለየው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ሥጋውና ቅዱስ ደሙ ነውና፡፡

ይህ የስርየት መክደኛ ሌላም ለእኛ የሚያስተላለፈው መልእክት አለው፡፡ መልእክቱም አማናዊው መሥዋዕት መቅረቡ እንደማይቀርና፣ መሥዋዕቱ የሚቀርብበት ስፍራ በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ሆኖ እግዚአብሔር በምህረት በሚገለጥበት በጸጋ ዙፋኑ በጽላቱ ላይ መሆን እንዳለበት ነው፡፡(ዕብ.4፡16) በዚህም እግዚአብሔር አምላክ በነቢዩ ሚልክያስ “ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና በየስፍራውም ስለስሜ ዕጣንን ያጥናሉ ንጹሕም ቁርባን ያቀርባሉ”(ሚል.1፡11) እንዳለው የስርየት መክደኛው በዓለም ዙሪያ ላለችው አንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምሥጢረ ቁርባንን ለምትፈጽምበት ጽላት ወይም ታቦት ምሳሌ መሆኑን ያሳየናል፡፡ በሐዲስ ኪዳን ጽላቱ(ታቦቱ) የሚያርፍበት ስፍራ መንበር ተብሎ ሲጠራ የእግዚአብሔር ስም የተጻፈበትና ቅዱስ ሥጋው ክቡር ደሙ የሚፈተትበት ደግሞ ጽላት ወይም ታቦት ወይም መሠዊያ ተብሎ ይጠራል፡፡

የስርየት መክደኛው በታቦቱ አናት ላይ መሆኑም ቅዱስ ኤፍሬም “የእኛን ሥጋ ለነሣኸውና ፣ መልሰህ ለእኛ ለሰጠኸን ፣ ለአንተ ክብር ምስጋና ይሁን፡፡ ከእኛ በሆነው ሥጋህ በኩል እጅግ የበዛውን የአንተን ስጦታ ተቀበልን፡፡” ብሎ እንዳመሰገነ፤ እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረቡን ያሳየናል፡፡ የስርየት መክደኛውን የሚጋርዱት በጥሩ ወርቅ የተሠሩት የኪሩቤል ምስሎችም አማናዊው መሥዋዕት በሚሠዋበት ጊዜ በዙሪያው ረበው የሚገኙ የመላእክት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ይህን ለማስገንዘብ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን በመንበረ ታቦቱ ላይ ምስለ ፍቁር ወልዳ እንዲቀመጥ ታዝዛለች፡፡ ምስለ ፍቁር ወልዳን ላስተዋለ ሰው በትክክል የታቦተ ጽዮንን መንፈሳዊ ትርጉምን ይረዳል፡፡

ይህን ድንቅ የሆነ መንፈሳዊ ትርጉምን ይበልጥ ለመረዳት አንድ ምሳሌ የሚሆነንን እውነታ እንመልከት፡፡ ንጉሥ ዳዊት የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑ ታቦት ከአቢዳር ቤት ወደ ጽዮን ከተማ ባስመጣበት ጊዜ በታቦተ ጽዮን ፊት ለእግዚአብሔር በሙሉ ኃይሉ በደስታ እየዘለለ መንፈሳዊ መዝሙርን አቅርቦ ነበር፡፡(2ሳሙ.6፡12-17) ይህን ዓይነት ተመሳሳይ ድርጊት በሐዲስ ኪዳንም ተፈጽሞል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስት ኤልሳቤጥን በተሳለመቻት ጊዜ የስድስት ወር ፅንስ የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የጌታችንን እናት የሰላምታ ድምፅ በሰማ ጊዜ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ከእናቱ ማኅፀን ውስጥ ሳለ በደስታ ዘሎአል(ሰግዶአል)፡፡ (ሉቃ.1፡44) ቅዱስ ዳዊት በታቦተ ጽዮን ፊት እንዲያ ደስ መሰኘቱና ለአምላኩ የምስጋና ቅኔን መቀኘቱ ለሰው ልጆች ሁሉ የመዳናቸው ምክንያት የሆነችውን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጁዋን ኢየሱስ ክርስቶስን በታቦተ ጽዮን በኩል በማየቱ ነበር፡፡

ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን አባቶችም ይህንን እውነታ ይጋሩታል ፡፡ ለምሳሌ ቅዱስ ኤፍሬም፡- “ከአዳም ጎን በተገኘችው አንዲት አጥንት ምክንያት ሰይጣን ከአዳም ማስተዋልን አራቀ፡፡ ነገር ግን ከእርሱ አብራክ በተገኘችው በቅድስት ድንግል ማርያም ምክንያት በእርሱ ላይ ሠልጥኖ የነበረው ሰይጣን እንደ ዳጎን ተሰባብሮ ወደቀ፡፡ ታቦተ ጽዮን በተባለችው በቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ውስጥ ባደረው በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የድል አዋጅ ታወጀ፡፡ በቃል ኪዳኑዋ ታቦት ሥር ዳጎን ተሰባብሮ እንደተገኘ እንዲሁ ክፉው ሰይጣን በታመኑበት ፊት ድል ተነሳ፡፡

እግዚአብሔር በቃል ኪዳኗ ታቦት ኃይሉን በመግለጥ ዳጎንን ሰባብሮ እንደጣለው እንዲሁ እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለድ በኃጢአት ምክንያት በእኛ ላይ ሠልጥኖ የነበረውን ሰይጣንን ድል ነሳው፡፡” (1ሳሙ.5፤6) ሲል ቅዱስ ጀሮም ደግሞ “ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድስትና ንጽሕት ነበረች፡፡ በቃል ኪዳኗ ታቦት ውስጥ የሕጉ ጽላት ብቻ እንደነበር እንዲሁ እርሷም በሕሊናዋ ከእግዚአብሔር ሕግጋት ውጪ ሌላ ምንም ሃሳብ አልነበራትም፡፡
ቅድስት ድንግል ማርያም በውስጥም በውጪም ነውር የሌለባት ንጽሕት ናት፡፡ እንደ ቃል ኪዳኗ ታቦት በውጪም በውስጥም በቅድስና የተጌጠችና ሕጉንም ጠብቃ የተገኘች የክርስቶስ ሙሽራ ናት ፡፡ በቃል ኪዳን ታቦቱ ውስጥ ከሕጉ ፅላት ውጪ ሌላ ምንም ነገር እንደሌለ እንዲሁ አንቺም ቅድስት ሆይ በሕሊናሽ ምንም ነውር የሌለብሽ ቅድስት ነሽ፡፡” ብሎ ሲያመሰግናት፤ የእስክንድርያው ዲዮናስዮስ ደግሞ “ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካህን ይሆን ዘንድ በሰው እንዳልተመረጠ እንዲሁ ቅድስት ድንግል ማርያም የጌታ ማደሪያ ትሆን ዘንድ በእግዚአብሔር የተመረጠችና በመንፈስ ቅዱስ ለእርሱ ማደሪያነት የተዘጋጀች ናት፡፡ የመለኮት ማደሪያ ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር የከተመባት ከተማ ሆና ትኖር ዘንድ ለዘለዓለም በእግዚአብሔር ታትማለች” በማለት ስለእርሱዋ ይመሰክራል፡፡

አዳም ድኅነቱ ከሴት ወገን በሆነች በቅድስት ድንግል ማርያም በኩል እንደሆነ ተረድቶ ለሚስቱ “ሔዋን” ብሎ ስም እንደሰጣት እንዲሁ ንጉሥ ዳዊት በቅድስት ድንግል ማርያም በኩል እንደሚድን በመረዳቱ አምባዬና መጠጊያዬ ነሽ ሲላት “ጽዮን” ብሎ ለድንግል ስያሜን እንደሰጣት በመዝሙራቱ ማስተዋል እንችላለን፡፡ ጽዮን የንጉሥ ዳዊት ተራራማዋ ከተማ ስትሆን፣ የስሟ ትርጓሜ አምባ፣ መጠጊያ ማለት ነው፡፡ ይህን ይዘው ብዙዎች ነቢያት ስለ ድንግል ሲናገሩ ጽዮን የሚለውን ስም ተጠቅመዋል፡፡

ነቢያት ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ሲናገሩ ጽዮን የሚለውን ስም እንደሚጠቀሙ ወደ ብሉይ ኪዳን ሳንገባ በሐዲስ ኪዳን ብቻ ስለ ጽዮን የተጻፉትን በማንሣት ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ኢሳይያስ ከአይሁድ ወገን የሆኑ የራሳቸውን ሥርዐትና ሕግ ለማቆም ሲሉ በክርስቶስ ከማመን ስለተመለሱት ሲጽፍ፡- “እነሆ በጽዮን የእንቅፋት ድንጋይና የማሰናከያ አለት አኖራለሁ”(ኢሳ28፡16፣8፡14) አለ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ስለክርስቶስ የተነገረ ነው በማለት በሮሜ 9፡33 ላይ ጠቅሶት እናገኛለን፡፡ ስለዚህም ነቢዩ ኢሳይያስና ቅዱስ ጳውሎስ ጽዮን ያሏት ቅድስት ድንግል ማርያምን እንደሆነ በዚህ ኃይለ ቃል መረዳት እንችላለን፡፡ የማሰናከያ አለት የተባለው ክርስቶስ እንደሆነም “እነሆ የብዙዎች ልብ ሐሳብ ይገለጥ ዘንድ ይህ ለእስራኤል ላሉት ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፡፡”(ሉቃ.2፡34-35) ተብሎ ተጽፎአል፡፡ ስለዚህ የማሰናከያ አለት የተባለውን ክርስቶስን ፀንሳ የወለደችው ቅድስት ድንግል ማርያም ጽዮን መባሉዋን በእነዚህ ጥቅሶች ማረጋገጥ እንችላለን፡፡

tsion mariam 02ነቢዩ ዳዊትና ኢሳይያስ ጽዮን ከተሰኘች የሙሴ ፅላት ካህኑ በሚያቀርበው መሥዋዕት አማካኝነት አፋዊ ድኅነት እንደተደረገ፣ ከእመቤታችን ከተወለደው አማኑኤል አማናዊ ድኅነት እንዲፈጸምልን “መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል ከያዕቆብም ኃጢአተኝነትን ያስወግዳል”(መዝ.13፡10፤ኢሳ.59፡20) በማለት ስለክርስቶስ ትንቢትን ተናግረዋል፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ ለጌታችን ለመድኃኒታችን ሰጥቶ በሮሜ.11፡26 ላይ ተጠቅሞበታል፡፡ በዚህም ቦታ ጽዮን ያሏት ቅድስት ድንግል ማርያምን መሆኑን ማስተዋል እንችላለን፡፡ ምክንያቱም እርሱ ከእርሱዋ እንጂ ከሌላ አልተወለደምና፡፡ ነገር ግን “መድኃኒት” የተባለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመሆኑ “መልአኩም እንዲህ አላቸው፡- እነሆ ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁ በዳዊት ከተማ መድኅኒት እርሱ ክርስቶስ ተወለደ” (ሉቃ.2፡10) በማለት ገልጾልናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢየሱስ ማለት “መድኃኒት ማለት ነው (ማቴ.1፡21) የኢየሱስም እናት ደግሞ ቅድስት ድንግል ማርያም መሆኑዋን ማንም የማይክደው ሐቅ ነው፡፡ ስለዚህም ነቢያቱ “መድኃኒት ከጽዮን ይወጣል” ሲሉ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጽዮን ከተባለችው ከቅድስት ድንግል ማርያም ይወለዳል ማለታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡

ምንም እንኳ ቅዱስ ዳዊትና ሌሎች ነቢያት ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ለመናገር ሲሉ ጽዮን የሚለውን ስም አብዝተው ይጠቀሙ እንጂ አልፎ አልፎ ግን ጽዮን በማለት ስለ ከተማዋ ተናግረው እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ ሚክያስ “ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን ትታረሳለች”(ሚክ.3፡12)ይላል፡፡ ይህ በቀጥታ ስለጽዮን ከተማ የተነገረ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ጌታችን መናገር ሲፈልግ ስለእርሱ የሚናገሩትን ብቻ መርጦ እንደተጠቀመ እንመለከታለን፡፡ እኛም እንዲሁ ለቅድስት ድንግል ማርያም የተነገሩትን አስተውለን ልንለያቸው ይጠበቅብናል፡፡ ምክንያቱም አንዳንድ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ያልተጻፉ ነገር ግን ጽዮን የሚለውን ስም ይዘው የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት አሉና፡፡ ቢሆንም ስለታቦተ ጽዮን የተጻፉ ገቢረ ተአምራት ሁሉ እግዚአብሔር ቃል ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለዶ ለፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ምሳሌዎች ናቸው፡፡

በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በብሉይ ኪዳን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙትን ገቢረ ተአምራት ለድንግል ማርያምና ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በመስጠት ተርጉማ ለልጆቹዋ ታስተምራለች፡፡ በኅዳር 21 ቀንም በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙት ታላላቅ ተአምራት የሚታሰቡበት ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በታቦተ ጽዮን የተፈጸሙትን ታላላቅ ተአምራት እግዚአብሔር ቃል ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ በመወለድ ከፈጸማቸው ታላላቅ የድኅነት ሥራዎች ጋር በማነጻጸር በድኅነታችን ውስጥ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ድርሻ ምን እንደሆነ ትገልጻለች፡፡ ለምሳሌ ታቦተ ጽዮንን የተሸከሙ ካህናት እግራቸው የዮርዳኖስን ባሕር በመንካቱ ባሕሩ ለሁለት እንደተከፈለ እንዲሁ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ተወልዶ ጥምቀትን በራሱ ጥምቀት በመመሥረት ከሰይጣን ባርነት ወደ እግዚአብሔር ልጅነት እንዳሸጋገረን እናወሳበታለን(ኢያ.3፤ ማቴ.3፡13-17)፡፡ ፍልስጤማውያን ከእስራኤላውያን ጋር ውጊያ በገጠሙ ወቅት ታቦተ ጽዮንን ማርከዋት ዳጎን በሚባለው ቤተ ጣዖታቸው ውስጥ አኑረዋት ነበር፡፡ ነገር ግን ታቦቷ ዳጎኑን በፊቷ ሰባብራ እንደጣለችው እንዲሁ ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደው በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ ሠልጥኖ የነበረው ሰይጣን ድል መነሳቱን እናወሳበታለን፡፡ ((1ሳሙ.5፤6)

በዚህ መልክ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መንጎቿን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያምና ስለ ልጁዋ ስለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሁም በእርሱ ስለተሰጠን ሰማያዊ የአገልግሎት ሥርዐት፣ ስለ ታቦት ጥቅምና አገልግሎት፤ ታቦተ ጽዮንንና ቅድስት ድንግል ማርያምን በማነጻጸር በሰፊው እንደምታስተምር መረዳት እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤትና በረከት ያሳትፈን፡፡ የእግዚአብሔር አብ ጸጋ የእግዚአብሔር ወልድ ቸርነት የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት በእኛ ላይ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኑር አሜን

ረቡዕ 26 ኖቬምበር 2014

አባ ፊልጶስን ፍለጋ (የመጨረሻው ክፍል)

                                      

መኪናዋ ተገፍታ ለመጨረሻ ጊዜ ስትወጣ
የአካባቢው ገበሬዎችና አሣፍረናቸው የነበሩ ሌሎች ገበሬዎች ተባብረው መኪናዋን በዳገቱ መግፋት ጀመሩ፡፡ ድንበሩ አንዴ ገብቶ መሪ ይዞ ይነዳል፣ አንዴ ወርዶ ጎማውን በካልቾ ይማታል፡፡ ሙሉቀን በትጋትና ተስፋ ባለመቁረጥ መኪናዋን ከፖሊሶቹና ከገበሬዎቹ ጋር ይገፋል፡፡ ቀለመወርቅ መኪናዋን የሚመለከት የሕግ ዐንቀጽ የሚፈልግ ይመስል አንገቱን ደፍቶ አንዳች ነገር ያስሳል፡፡ ኤልያስ መነጽሩን ከፍ እያደረገ ለድንበሩ የመፍትሔ ሃሳብ ያቀርባል፡፡ ይህ ሁሉ ግን መኪናዋን ዳገት እንድትወጣ አላስቻላትም፡፡

እኛም የወጣችውን መኪና በእግር ስንከተል
ቀለመወርቅ ‹ድንጋዩን አንሡ› የሚለው ጥቅስ ትዝ ብሎት ነው መሰል መኪና መንገዱ ውስጥ ገብቶ ጭንቅላት ጭንቅላት የሚያህሉ ድንጋዮችን ማንሣት ጀመረ፡፡ መኪናዋም ጥረቱን አደነቀችለት መሰል ወደላይ የመውጣት ተስፋ ሰጠች፡፡ ገበሬዎቹም ያለ የሌለ ኃይላቸውን ተጠቅመው ወደ ላይ ገፏት፡፡ ‹ተመስገን› ዋናውን ዳገት እያቃሰተች ወጣችና አፋፍ ላይ ቆመች፡፡ የሁሉም ፊት ከኀዘን ወደ ደስታ፣ ከቀቢጸ ተስፋ ወደ ተስፋ ተቀየረ፡፡
‹‹አይዟችሁ ከዚህ በኋላ ሌላ ዳገት የለም›› አለን አብሮ የነበረው ቆፍጣናና ጉልበታም ገበሬ፡፡ መኪና የገፋበትን ክንዱን እየወዘወዘ፡፡ እውነትም እንዳለው ቀሪው መንገዳችን ሜዳ ነበረ፡፡ ከውስጥ እኛ፤ ከውጭ ገበሬዎቹ ተሣፈርንና ያለፈ ነገራችንን እያነሣን ወደ መዳረሻችን ጉዞ ቀጠልን፡፡ 
መኪናዋ በዳገቱ መጨረሻ ላይ
እነሆ የኳሳ ደረስን፡፡ በመኪና ልንሄድበት የምንችለው የመጨረሻው ቦታ የኳሳ ከተማ ናት፡፡ ሊቀ ካህናቱ የምንሄድበትን በረሃ በሩቁ አመለከቱን፡፡ ‹ልብ የሌላትን መኪና ገፍቶ እዚህ ያደረሰ አምላክ ልብ የሰጠንን እኛን እዚያ ማድረስ አያቅተውም› ብለን አመንን፡፡ የከተማው ፖሊስ ጣቢያ መኪናችንን አቆምን፡፡ ሁለቱ ፖሊሶች፣ የወረዳው ሊቀ ካህናት፣ ከወረዳው ቤተ ክህነት የመጡ አንድ ሌላ ዳዊት ደጋሚ ካህን እና እኛ አራታችን በእግር ለመገስገስ ተዘጋጀን፡፡ እኒህ ዳዊት ደጋሚ ካህን የሚገርም ተሰጥዖ አላቸው፡፡ እኛ እንሂድ አንሂድ ስንጨነቅ፣ ሰው ሁሉ የመሰለውን እየሰነዘረ ሲከራከር፣ መኪና ስትሄድ፣ መኪና ስትቆም እርሳቸው ዳዊት መድገማቸውን አያቆሙም፡፡ ባይሆን እንደ መሐል ከተማ ሰው ዲፕሎማሲ ባለመቻላቸው ድንበሩ ተቀይሟቸው ነበር፡፡ ‹ምን ያህል መንገድ ይቀረናል?> ሲላቸው መልሳቸው ‹ገና ምኑ ተነካ› ነው፡፡ ‹ሞራል አይሰጡም፤ ተስፋ ያስቆርጣሉ› አለ ድንበሩ፡፡ እርሳቸው እንደሆነ ቁርጥ ያለ የዘመድ ዋጋ ነው የሚያውቁት፡፡
ዳገቱ አለቀ
ከየኳሳ ከተማ ሁለተኛው ምእራፍ ተጀመረ፡፡ በሩቁ የምናቋርጠው በረሃ ተዘርግቷል፡፡ መንገድ ላይ የደብረ ዕንቁ አገልጋይ የሆኑ መሪጌታ ይጠብቁናል፡፡ ለአንድ ሰዓት ያህል ከተጓዝን በኋላ ኤልያስ ማንከስ ጀመረ፡፡ ከዚህ ጉዞ ላለመቅረት ብሎ እንጂ እግሩን ኦፕራስዮን አድርጎ ነበር፡፡ ያደረገው ጫማ ሸበጥ ነገር ነው፡፡ 
የወንዝ ዳር ረፍት
ድንበሩና አንደኛው ፖሊስ ከፊት፣ ካህናቱና ሙሉ ቀን ከመካከል፣ ከእነርሱ ቀጥሎ ቀለመወርቅ፣ እኔና ኤልያስ በስተመጨረሻ ‹አዴም ነዲያቸው› እያልን  እንጓዝ ነበር፡፡ የኤልያስ እግር መቁሰል ጀምሯል፡፡
በበረሃው መግቢያ በር
መንደሮችንና እርሻዎችን እያቋረጥን ነበር የምንጓዘው፡፡ አሥር ዓመት የማይሞላቸው ሴትና ወንድ እረኞች እጃቸውን አፋቸው ላይ አድርገው በግርምት ያዩናል፡፡ 
አዲስ ጠረን የሸተታቸው ከብቶች በአጠገባቸው ስናልፍ ቀንዳቸውን ሊፈትሹብን ይፈልጋሉ፡፡ ሰላምታ የማይጓደልባቸው የስማዳ ገበሬዎች ከዐጨዳቸው ላይ ብዲግ እያሉ፣ በሽክና ጠላቸውን ይዘው በመጋበዝ በሰላምታ ያሳልፉናል፡፡ 
የቸሩ የስማዳ ገበሬ ግብዣ
አሁን የመሪጌታ ጥዑመ ልሳን እርሻና መንደር ጋ ደረስን፡፡ እኒህ መሪጌታ ‹በከንቱ የተቀበላችሁትን በከንቱ ስጡ› የሚለውን ቃል አክብረው፣ ከተማውን ትተው እዚህ ገጠር ተቀምጠው ደቀ መዛሙርት የሚያፈሩ መሪጌታ ናቸው፡፡ ምርግትናውን ከክህነት፣ ክህነቱንም ከግብርና አስተባብረው እያረሱ ያስተምራሉ፣ እያስተማሩም ያርሳሉ፡፡ ደቀ መዝሙሮቻቸው በአንድ በኩል ለመምህራቸው የጉልበት አገልግሎት ይሰጣሉ፤ በሌላ በኩል ከመምህሩ ዕውቀት ይሸምታሉ፡፡ ተማሪዎቻቸውን በመደዳ ያስቀምጡና በሬያቸውን ይጠምዳሉ፡፡ ወዲያ ሲሄዱ ለአንዱ ቀለም ይነግራሉ፣ ወዲህ ሲመጡም ለሌላው ቀለም ይነግራሉ፡፡ እርሻውም የታደለ ነው፤ ቃለ እግዚአብሔር እየፈሰሰበት ይታረሳል፣ ይዘራል፣ ይታጨዳል፣ ይወቃል፡፡ ይህንን የመሰሉ ሰዎች ያመረቱት እህል እየተቀላቀለበት ሳይሆን አይቀርም ሞሰባችን ረድኤት የነበረው፡፡
እረፍት በመሪጌታ እርሻ አጠገብ
በመሪጌታው እርሻ ጎን ዕረፍት አደረግን፡፡ እግረ መንገዳችንንም እርሳቸውን እንጠብቅ ዘንድ፡፡ የመምህሩ ቤት ከመንገዳችን በስተ ቀኝ ከዛፎቹ ሥር ነው፡፡ ዙርያውን በተማሪዎቻቸው ጎጆዎች ተከብቧል፡፡ አሁን የአጨዳ ጊዜ በመሆኑ ተማሪዎቻቸውን አስተባብረው ወደ አጨዳ ሄደዋል፡፡ አውድማቸው የተቀመጥንበት አካባቢ ነውና እህሉን ወደዚህ ያመጣሉ፡፡ ከባለቤታቸው ጋር እያወጋን ጠበቅናቸው፡፡ እግረ መንገዳቸውን አብረውን ያሉት ካህን ስለ ጌርጌስ ያወጉን ጀመር፡፡ 
አባ ፊልጶስ ከጌርጌስ ወደ ሐቃሊት የመጣበት በረሃ
‹ጌርጌስ ማለት ያ ከማዶ የምታዩት ሜዳማ ተራራ ነው፡፡ በደብረ ዕንቁ እና በጌርጌስ መካከል ታላቅ በረሃ አለ፡፡ ጌርጌስ አጠገብ የጃምባ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ያለበት ጋሼና የሚባል ቦታ አለ፡፡› ‹በዜና መዋዕሉ ከጋሼና እስከ ዐንቆ የሚለው ይህንን ነው ማለት ነው› አልኩ፡፡ አቡነ ፊልጶስ ወደ ሐቃሊት ሲመጣ ከአቡነ ሰላማ መተርጉም ጋር የተገናኘው በጌርጌስ መሆኑን ገድሉ ይነግረናል፡፡ ይህቺ ቦታ ከጥንት ጀምሮ የጳጳሳት መቀመጫ ነበረች፡፡ አሁን በትክክልም የአቡነ ፊልጶስን የመጨረሻ ቦታ እያገኘነው ነው ማለት ነው፡፡
የመሪጌታ ተማሪዎች ጎጆ
አንቆስ ማናት? ደብረ ዕንቁ ትሆን? ይህንን እያሰብኩ እያለ፡፡ ያን ጊዜ አንደኛውን ፖሊስ ዝም ብለን ክንቀመጥ ብዬ ‹እንዴው ስለ ሀገሩ ምን ይዘፈናል?› አልኩት፡፡ እርሱም እንዲህ አለኝ
ላሊበላን መሳም በከንቱ ድካም ነው
ከየኳሳ በታች ዐንቆ መጨምጨም ነው
እጅግ የሚገርም ሰምና ወርቅ ቅኔ፡፡ የኳሳ መኪናችንን ያቆምንባት ከተማ ናት፡፡ ‹ከየኳሳ በታች ዐንቆ መጨምጨም ነው› አለ፡፡ ‹ዐንቆ ማናት?› አልኩት፡፡ ‹ዐንቆ ማለት ደብረ ዕንቁ ናት› አለኝ፡፡ እፎይ አልኩ፡፡ ‹ከዐንቆ እስከ ጋሼና› የሚለው ተፈታ ማለት ነው፡፡ ‹ሐቃሊት የተባለችውኮ ደብረ ዕንቁ ናት፤ ሐቃሊት ማለት በበረሃ ያለች ቦታ ማለት ነው› አሉና ካህኑ ይዘረዝሩት ጀመር፡፡ ገርሞኝ ነበር በደስታ የማያቸው፡፡ ‹ሐቃሊት የታለች?› አልኳቸው፡፡ ሐቃሊትን ትንሽ ከሄድን በኋላ ታያታለህ፤ ጌርጌስ ያውልህ፡፡ አቡነ ፊልጶስ የታመመው እዚያ ነው፡፡ ወደ ሐቃሊት የመጣው ታቹን በበረሃው አድርጎ ነው፡፡ በበረሃው ከመጣ በኋላ እዚህ ዳገቱ ላይ ሲደርስ ዐረፈ፡፡ ያረፈበት ቦታ ይኼውልህ፤ አሁን የታቦት ማርገጃ አድርገነዋል›› አሉና አሳዩኝ፡፡ ቦታውን ወድቄ ተሳለምኩት፡፡ ዙርያውን ታጥሮ አንዲት ዛፍ በቅላበታለች፡፡ አካባቢው ለጥ ያለ ሜዳ ነው፡፡ 
የመሪጌታ ተማሪ ነዶ ተሸክሞ
እኒህ ዳዊት ደጋሚ ካህን ብርቱ ናቸው፡፡ መምህሩ እስኪመጡ ተማሪዎቻቸው ያመጡትን የጤፍ ነዶ በአውድማው ላይ ይከምሩላቸው ጀመር፡፡ የቄስና የሴት እንግዳ የለውም ማለት ይኼ ነው፡፡ መምህሩ ነዷቸውን ተሸክመው መጡ፡፡ የተሸከሙትን አወረዱና ሰላም አሉን፡፡ ከእርሳቸው ጋር ወደ ደብረ ዕንቁ ለመሄድ መምጣታችንን ስንነግራቸው በደስታ አብረውን ለመሄድ ተነሡ፡፡ ወደ ቤታቸው ደርሰው ልብሳቸውን ቀየሩና ከእኛ ጋር ተቀላቀሉ፡፡
መሪጌታ ነዶ ተሸክመው
እነሆ አሁን የበረሃውን መንገድ ለማግኘት አባ ፊልጶስ ከጌርጌስ ሲመጣ ባረፈበት ሜዳ በኩል አቋርጠን መንገድ ጀመርን፡፡ መሪጌታ በሁለት ነገር ጠቅመውኛል፡፡ በአንድ በኩል ታሪክና ጨዋታ ዐዋቂ ስለሆኑ መንገዱን ያለ ድካም እንድንጓዝ አድርገዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በእድሜ ጠገቡ ጃንጥላቸው የስማዳን ፀሐይ መክተውልኛል፡፡ 
ወደ በረሃው ጉዞ
አሁን ኤልያስ እያነከሰ፣ ድንበሩ መሐል መጥቶ ፣ ቀለመወርቅና ሙሉቀን ከካህናቱ ጋር አብሪ ሆነው ወደ ቆላው ልንገባ ነው፡፡ ቆላው ሁለት ተራሮችን ወጥቶ መውረድና ሦስተኛውን ተራራ መውጣት ይጠይቃል፡፡ መሪጌታ አቡነ ፊልጶስ ከጌርጌስ ወደ ሐቃሊት የመጣበትን በረሃ አሳዩን፡፡ ከጎንና ጎን ተራራ ያለበት ገደል ነው፡፡
ከመጀመርያው ተራራ ወርደን
 አሁን ደብረ ሐቃሊት ከሩቁ ትታያለች፡፡ ሲቀርቧት የምትርቅ ሞሰበ ወርቅ የመሰለች ተራራ ናት፡፡ ወደ እርሷ ለመድረስ ግን ሁለት ተራሮች እንደ መቅድም ሆነውላታል፡፡ ታምሯ እርሷ ናት፡፡
ኤልያስ፡- ከሁለት እግር ወደ ሦስት እግር
ወደ ሁለት ሰዓት የፈጀ የመውጣትና የመወረድ ጉዞ በማካሄድ ላይ ነን፡፡ ቆላው ውስጥ፡፡ አሁን የምንሄድበት መንገድ አንድ ሰው ብቻ የሚያሳልፍ የተፈጥሮ ድልድይ ነው፡፡ በግራና በቀኝ ገደል ነው፡፡ ‹ከዚህ የተንከባለለ ወይ በሽሎ ወይ ዓባይ ነው የሚገኘው› ብለውኛል መሪጌታ፡፡ እኛም ከሁለቱ በአንዱ ላለመገኘት በጥንቃቄ መሥመር ሠርተን በመጓዝ ላይ ነን፡፡ አንዱን ተራራ ይህንን በመሰለ እንደ ባሕረ እሳት መንገድ በቀጠነ መሷለኪያ አለፍነውና ሌላ ተራራ ከፊታችን ተገተረ፡፡
ከደብረ ዕንቁ ማዶ የሚገኘው ጌርጌስ ነው
እርሱ ደግሞ ዐለቶች ተሰባስበው በማኅበር የመሠረቱት ነው፡፡ ከዐለቱ በስተጀርባ ተዙሮ ወደ ፊቱ ለመምጣት ከቁጥቋጦና ስለታም ድንጋዮች ጋር ትግል ይጠይቃል፡፡ በዐለቱ ጫፍ ላይ ሆናችሁ የመጣችሁበትን መንገድ ወደታች ስታዩት እናንተ ከጠፈር ጥግ ያላችሁ ነው የሚመስላችሁ፡፡ ሁሉም ነገር የጣት ቁራጭ አክሎ ነው የሚታየው፡፡ ዐለታማውን ተራራ ተጠማዝዘን ወረድነውና ተራራውን ከደብረ ዕንቁ ጋር ወደሚያያይዘው ቀጭን መንገድ ገባን፡፡ ይህም በግራና ቀኝ ገደል ያጀበው፣ ከቅድሙ ሰርጥ ግን ሰፋ የሚል መንገድ ነው፡፡ 
ሁለተኛው ዐለታማ ተራራ
ከባዱ ዳገት ወደ ደብረ ዕንቁ የሚያስወጣው ነው፡፡ ተራራውን እንደ ዘንዶ መጠማዘዝን ይጠይቃል፡፡ ደግነቱ መንገዱ ደልደል ያለ ነው፡፡ ለሃያ ደቂቃ ያህል ከዞርነው በኋላ አንድ ቦታ አገኘን፡፡ ‹ይህ ቦታ ምዕራፈ ወለተ ጴጥሮስ ይባላል› አሉን መሪጌታ ጥዑመ ልሳን፡፡ ‹‹ወለተ ጴጥሮስ ይህንን ገዳም ውኃ በመቅዳት አገልግላለች፤ ውኃ ቀድታ ስትመጣ የምታርፍበት ቦታ ስለሆነ ምዕራፈ ወለተ ጴጥሮስ ተባለ›› አሉን፡፡ ይህ ታሪክ በወለተ ጴጥሮስ ገድል ላይ ተጽፏል፡፡ 
ምእራፈ ወለተ ጴጥሮስ
ምዕራፈ ወለተ ጴጥሮስን ካለፍን ከሃያ ደቂቃ በኋላ የገዳሙን በር አገኘነው፡፡ እነሆ ጉዟችን ወደ መጠናቀቂያው እየደረሰ ነው፡፡ የገዳሙን በር ከዘለቃችሁ በኋላ ሌላ መንገድም ይጠብቃችኋል፡፡ ያውም ተራራማ መንገድ፡፡ ደግነቱ ብዙም ሩቅ አይደለም፡፡ 
ከተራራው ሥር
ፊት ለፊታችን ደብረ ዕንቁ ማርያም ታየችን፡፡ አንቺን ፍለጋ ስንት ጊዜ ለፋን፣ ስንቱንስ ሀገር አቋረጥን፡፡ ስንቱን ተራራና ገደልስ ተሻገርን፡፡ መሪጌታ ቤተ ክርስቲያኑን አስከፈቱልን፤ እኛም ወደ ወስጥ ዘለቅን፡፡ ጸሎት ካደረስን በኋላ ‹ክህነት ያላችሁ ወደ ውስጥ ዝለቁ› አሉ መሪጌታ፡፡ እኛም ወደ ቅድስቱ ዘለቅን፡፡ አቡነ ፊልጶስ ተቀብሮበት የነበረውንም ቦታ ከመንበሩ ሥር አሳዩን፡፡ የአቡነ ፊልጶስ ዐፅም ለ140 ዓመታት የቆየው እዚህ ነበር፡፡ በዐፄ እስክንድር ዘመን (1471-1487 ዓም) በእጨጌ መርሐ ክርስቶስ ጊዜ በእጨጌ መርሐ ክርስቶስ ጥያቄና በንጉሡ ፈቃድ ከደብረ ሐቃሊት ፈልሶ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገባ፡፡ 
አባ ፊልጶስ ያረፈበት ቦታ
ገዳማውያኑ መልካም አቀባበል ነበር ያደረጉልን፤ ገድሉን እያነበቡ ታሪኩን በመንገር፤ ገዳማዊ የሆነውን ምግብ በማቅረብ፤ የበረከቱም ተካፋይ በማድረግ፡፡ ደብረ ዕንቁ በኢትዮጵያ ታሪክ ያልተጠና ብዙ ነገር አላት፡፡ የአቡነ ሰላማ መተርጉም መቀመጫ ነበረችና ምናልባት ጳጳሱ ከአሥራ አንድ በላይ የሚሆኑ መጻሕፍትን ከዐረብኛ ወደ ግእዝ የተረጎሙት እዚህ ቦታ ይሆን ይሆናል፡፡
ደብረ ሐቃሊት በር ደረስን
 እርሳቸው ለዐረብኛው እንጂ ለግእዙ አዲስ ናቸውና ታላቁን ሥራ የሠሩት በደብረ ዕንቁ የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ሊሆኑም ይችላሉ፡፡ ደብረ ዕንቁ በዐፄ ሱስንዮስ ዘመን የተዋሕዶዎች መሸሸጊያና መወያያ በመሆንም ታላቅ ታሪክ አላት፡፡ እነ ዐራት ዓይና ጎሹን የመሳሰሉ የቅርብ ዘመን ሊቃውንትም መፍለቂያ ናት፡፡ በደብረ ዕንቁና በዲማ ጊዮርጊስ ሊቃውንት መካከል የነበረው የዘመናት ግንኙነትም ሊጠና የሚገባው ነገር ነው፡፡
ብቻ እኛ እዚህ ደርሰናል፡፡ በጉዟችን የረዱንን የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከትን፣ የስማዳ ወረዳ ቤተ ክህነትን፣ የስማዳ ወረዳ መስተዳድርን፣ የደብረ ዕንቁ ገዳም አባቶችንና ሌሎችንም እግዚአብሔር ዋጋቸውን ይክፈል እንላለን፡፡ 
ደብረ ዕንቁ ማርያም
እንደነ አቡነ ፊልጶስ ያሉ በቤተ ክርስቲያን ዘላለም የሚያበራ፣ ለትውልዱም የሥነ ምግባርና የሞራል ስንቅ የሚሆን ታሪክ ያላቸው ሰማዕታት አባቶች እንደ አዲስ አበባ ባሉ ታላላቅ ከተሞች ቤተ ክርስቲያን ሊታነጽላቸውና ትውልዱ እንዲያውቃቸው ሊደረግ ይገባል፡፡ 
አባ ፊልጶስ ያረፈበት ቦታ፣ ከመንበሩ ሥር
በአንዳንድ ቅዱሳን ስም አምስትና ስድስት ቤተ ክርስቲያን በአንድ ከተማ ከመትከል ለእነ አቡነ ፊልጶስ አንድ ዕድል መስጠት በታሪክም በሰማይም የሚያስመሰግንና ዋጋ ያለው ተግባር ይሆናል፡፡ በማኅበር ተሰባስበው ክርስቲያናዊ ሥራ የሚሠሩ ወጣቶችም እንደ አቡነ ፊልጶስ  ባሉ አባቶች ስም በመጠራትና ታሪካቸውን ከፍ በማድረግ የበረከታቸው ተሳታፊ ይሆኑ ዘንድ ታሪክ ይጋብዛቸዋል፡፡
እረፍት በገዳሙ ግቢ
እነሆ እንደመጣነው ልንመለስ ነው፡፡ ያው ተራራና ገደል፣ ያችው መኪና ይጠብቁናል፡፡
የገዳሙ ግብዣ

ከዚህ በኋላ የተፈጠረውን የአገልግሎት መንፈስ እና አንድነት ማንም አይበጥሰውም!!

የማኀበረ ቅዱሳን አስተዋጽኦ ሁለት መልክ አለው፡፡ አንደኛው የሚታየውን ነገር መስራቱ ነው፡፡ ለእኔ ግን ሁሌም የሚገርመኝና ማኀበረ ቅዱሳን ውስጥ እንዳገለግል ጉልበት የሚሆነኝ የማይታየው ነገር ነው፡፡ ይሔ ሁሉ ሰው፣ ይሔ ሁሉ ምእመን፣ ይሔ ሁሉ የግቢ ጉባኤ ተማሪ በአንድነት ስለ ቤተክርስቲያን እንዲመክር፣ እንዲያገለግል ያደረገው ማኀበሩ የፈጠረው የአገልግሎት ፍልስፍና ነው፡፡ ዘር፣ የትምህርት ደረጃ፣ ወንዝ፣ ከሀገር ውጭ፣ ከተማ፣ ገጠር ሳይል ሁሉም አኩል ለቤተክርስቲያን እንዲጨነቅ አድርጓል፡፡ ይህን አስብ ሁሌም ጉልበት ይሰጥሃል፡፡ አሁን የቤተክርስቲያን ጉዳይ የሁሉም ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉም ሰው እንደ ቤተክርስቲያን አባቶች እንዲያስብ ፣ እንዲጨነቅ፣ እንዲሟገት እንዲከራከር ፍልስፍናውን/አስተሳሰቡን የፈጠረው ማኀበረ ቅዱሳን ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የተፈጠረውን የአገልግሎት መንፈስና አንድነት ማንም አይበጥሰውም፡፡
(ዶክተር ዘርዓየሁ) ከመጽሔተ ተልዕኮ ዘማኀበረ ቅዱሳን ጋር ባደረገው ቆይታ የተናገረው፡፡

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...