ማክሰኞ 30 ዲሴምበር 2014

ስለ ገና በዓል እና ጾም አንዳንድ ጥያቄዎች

የገና እና የጥምቀት በዓላት ሲደርሱ በምእመናኑ ዘወትር የሚጠየቁ ጥያቄዎች አሉ፡፡ እነዚህን እና መሰል የሕዝቡን የዘወትር ጥያቄዎች መልስ የያዘ የማያዳግም ጥራዝ ማውጣት ከሊቃውንት ጉባኤ የሚጠበቅ ነው፡፡ አብዛኞቹ ጉዳዮች አበው ቀድመው ሥርዓት የሠሩባቸው እና ማብራርያ ብቻ የሚያስፈልጋቸው ናቸውና፡፡ ለዛሬ ሦስቱን ብቻ እንመልስ፡፡

ገና እና ጥምቀት ዓርብ እና ረቡዕ ቢውሉ ይበላባቸዋል ወይስ ይጾማሉ?

ፍትሐ ነገሥት፡ ዳግመኛ በየሳምንቱ ዓርብ እና ረቡዕን መጾም ነው፡፡ በዓለ ሃምሳ፣ የልደት እና የጥምቀት በዓል የተባበሩባቸው ጊዜ ካልሆነ በቀር /ዐንቀጽ 15፣ ቁ566/

የዓርብን እና የረቡዕን ጾም ግን ከልደት፣ከጥምቀት እና ከበዓለ ሃምሳ በቀር ዘወትር ይጹሙ /ዐንቀጽ 15፣ቁ 603/

የገና እና የጥምቀት ቅዳሴ ስንት ሰዓት ነው?

ፍትሐ ነገሥት፡ ስለ ልደት እና ጥምቀት ግን በዚያ ዘመን በኒቂያ የተሰበሰቡ ሊቃውንት ቅዳሴው በሌሊት ይሆን ዘንድ አዘዙ /ዐንቀጽ 15፣ ቁ 595/

ልደት ጋድ አለው?

ፍትሐ ነገሥት፡ የልደት እና የጥምቀት በዓላት ጋድ አላቸው /ዐንቀጽ 15፣ ቁ 566/

     ትንታኔ፡ የገና ጾም 44 ቀናትን ይይዛል፡፡

                   40 ጾመ ነቢያት

                     3 ጾመ አብርሃም ሶርያዊ

                    1 ጋድ

               ድምር 44

የገና ጋድ ከጾሙ ተያይዞ የተቀመጠ እንጂ ለብቻው የተቀመጠ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሰሙነ ሕማማት ለብቻው የሚቆጠር ጾም ነው፡፡ /ዐንቀጽ 15፣ቁ 565/ ነገር ግን አንድ ሰው ዐቢይ ጾምን ሳይጾም ከርሞ ሕማማትን ለብቻው መጾም አይችልም፡፡ የገናም ጋድ እንዲሁ ነው፡፡

ይህንን ጋድ የልደትን ጾም የማይጾሙ ሰዎች እንዲጾሙት የተሠራ ነውን?

መልስ፡ በቤተ ክርስቲያን ላልተጠመቁ፣ ለማይቆርቡ፣ ንስሐ ለማይገቡ፣ ለማያስቀድሱ፣ ለማይጾሙ ሰዎች ተብሎ የተሠራ ልዩ ሥርዓት የለም፡፡ በፍትሐ ነገሥት ዐንቀጽ 15፣ ቁ 565 እንደተገለጠው ሰባቱ አጽዋማት «ለክርስቲያን ሁሉ» የታዘዙ ናቸው፡፡ ስለዚህም የገናን ጾም ክርስቲያን ሁሉ ጾመው በበዓለ ልደት ሊገድፉ ይገባቸዋል፡፡ ፍትሐ ነገሥት ስለ ገና ጾም ሲገልጥ «መጀመርያው የኅዳር እኩሌታ ፋሲካው የልደት በዓል ነው» ይላል /ዐንቀጽ 15፣ ቁ 568/፡፡ ይህም ከገና ጾም ተሸርፎ የሚጾም ነገር እንደሌለው ያሳያል፡፡

መልካም በዓል

የትልቁ ዋርካ ትልቁ ቅርንጫፍ



ታኅሣሥ 19 ቀን 2007 ዓም በቤተ ክርስቲያን ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ከታወቁት ሊቃውንት መካከል አንዱን አጥተናል፡፡ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታየን፡፡ ስለ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በመቆርቆር፣ በማስተማርና በመጻፍ የምናውቃቸው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከጫፍ እስከ ጫፍ ያገለገሉ፤ በተለይም ለወጣቱ ትውልድ ጥያቄዎቹን በመመለስና አስረግጠውም በማስረዳት የምናደንቃቸው ነበሩ፡፡
ዜማ፣ አቋቋም፣ የአማርኛ ሰዋስው፣ ቅኔና የግእዝ አገባብ፣ ብሉይ፣ ሐዲስ፣ ነገረ መለኮት፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ በዘመናዊ ትምህርት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የተማሩ መሆናቸውን ስናይ፤ በአንባቢነታቸው ጥንታውያንና ዘመናውያን መጻሕፍትን የሚያገላብጡ ብቻ ሳይሆኑ በላዔ መጻሕፍት እንደነበሩ በሌሎቹ ሊቃውንት ሲመሰከርላቸው፤ በምሥራች ድምጽ ሬዲዮ ትምህርት በመስጠት፣ በታሪክና ድርሰት ክፍል ለዐሥር ዓመታት በማገልገል፤ የመዝሙር ክፍልን በመምራት፣ የዜና ቤተ ክርስቲያንን በምክትልና በዋና አዘጋጅነት  በማገልገል፣ እንዲያውም ጋዜጣውን የጋዜጣ መልክ በማስያዛቸው በ1962 ዓም መሸለማቸውን  እያዘከርን የተጓዙበትን የዕውቀት ጎዳና ስንመረምር ያጣነው አንድ ሰው ብቻ ባለመሆኑ፡-
አራት ሰው ሞተ ተቀበረ ዛሬ
ድጓ ጾመ ድጓ መዋሥዕት ዝማሬ
ተብሎ ለሊቁ የተገጠመው ሙሾ ለእርሳቸውም ይስማማቸዋል እንላለን፡፡ 

የየረርና ከረዩ አውራጃ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ዋና ጸሐፊ፣ የቀበና አቦ አስተዳዳሪ፣ የካህናት አስተዳደር መምሪያ ጸሐፊ፣ የኤርትራ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ፣ የከፋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ፣ የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ኃላፊ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ፣ የአስተዳደር መምሪያ ኃላፊ፣ የቁጥጥር አገልግሎት ኃላፊ፣ የበጀትና ንብረት መምሪያ ኃላፊ፣ የስብከተ ወንጌል መምሪያ ኃላፊ፣ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህት ቤት ምክትል ዲን፣ እየሆኑ ቤተ ክርስቲያኒቱን ማገልገላቸው ስንመለከት፡-
ቀባሪዎቹን
አፈር መልሱ እንጂ ድንጋይ ለምናችሁ
የቀለም ቀንድ ነው ትሰብሩታላችሁ
እንላቸዋለን፡፡
በ1977 በምዕራብ ጀርመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያሬዳዊ ዜማ ለማሳየት ከተጓዘው ልዑክ አንዱ ነበሩ፤ በ1995 የዓለም አብያተ ክርስቲያናት በእስክንድርያ ከተማ ባደረገው ጉባኤ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው ነበር፣ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ በአዲስ መልክ ሲዘጋጅ በብርቱ ካገለገሉት ሊቃውንት አንዱ ነበሩ፣ የመንና ጅቡቲ የሚገኙ ምእመናንን ለማስተማር በየዓመቱ ይጓዙ ነበረ፡፡ የሊቃውንት ጉባኤ አባል ሆነው ለብዙ ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ይህንን ስንመለከትም
እንግዲህ መቃብር ጠንክረህ ተማር
ዕውቀት ተሸክሞ መጣልህ መምር
እንለዋለን፡፡
ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታየ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በሚያዘጋጁት ጉባኤ ልጆችን ሳይንቁ፣ ክፍለ ሀገር በሚዘጋጅ ጉባኤ ለመንገዱ ሳይሰቀቁ በመጓዝ ያስተማሩ የዘመናችን ሐዋርያ ናቸው፡፡ ክህነትን፣ ትምህርትንና ጽሕፈትን አንድ አድርገው የያዙ፤ በተለይም ‹‹ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን›› እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ ሆኖ እንዲወጣ በብርቱ የደከሙ ሊቅ ናቸው፡፡ ድካማቸው ፍሬ አግኝቶ በየጊዜው ያዘጋጇቸው መጣጥፎችና መጻሕፍት ዛሬ ከኮሌጆች እስከ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ድረስ የማስተማርያ ዋና መሣሪያዎች ሆነዋል፡፤ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አንድ የትምህርት ዘርፍ ሆኖ እየተሰጠ ይገኛል፡፡
ሚያዝያ 19 ቀን 1929 ዓም  ይፋት ውስጥ  ደብረ ምሥራቅ ሾተል አምባ በኣታ አጥቢያ ተወልደው፣ በ1941 ዓም ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ዲቁና፣ በ1959 ዓም ቅስና ተቀብለው፤ አራት ወንዶችና አራት ሴቶች ወልደው፣ አሥር የልጅ ልጆች አይተው በ78 ዓመታቸው የተለዩን ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታየ በዕለተ ዕረፍታቸውና ቀብራቸው ብዙዎችን ያስደነቁ ሁለት ነገሮች ተከስተዋል፡፡ የመጀመሪያው ክንፈ ገብርኤል ተብለው ተጠርተው በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ በዓል(ታኅሣሥ 19 ቀን) ወደ ፈጣሪያቸው መጠራታቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ሲከናወን የሕይወት ታሪካቸው በሚነበብበት ጊዜ ከትልቅ ዋርካ ላይ ማንም ሳይነካው አንድ ትልቅ ቅርንጫፍ ተገንድሶ መውደቁ ነው፡፡
ቦታው የነበሩ፣ ይህንንም ነገር የተመለከቱ ሁሉ ታሪኩን በካሜራቸው ሲቀርጹና ከታላቋ ዋርካ ከቤተ ክርስቲያን ብዙዎችን የያዘው አንዱ ታላቅ ቅርንጫፍ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል ዛሬ መሰናቱን በኀዘን ሲተረጉሙ ነበር፡፡ የቅርንጫፉን ቅጠልም ብዙዎቹ ተሻምተው ወስደውታል


በረከታቸው ይደርብን፡፡  

‹‹ከአንድ ሊቅ በሚጠበቅ መልኩ በተጠያቂነት ደረጃ ሙሉ አገልግሎት በመስጠት መላ ዘመናቸውን አሳልፈዋል›› – የሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ዜና ሕይወት እና


The Late Accomplished Scholar Lique Kahinat Kinfe Gabriel Altaye
(ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. – ታኅሣሥ ፲፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)
  • ከትምህርት ቤትና ከመጻሕፍት ያገኙት ዕውቀት አራት ዓይና ያደረጋቸው ሊቁ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ በተጠያቂነት ደረጃ የሚገኙና አገልግሎታቸውም ሙሉ ነበር፡- ቀዳሽና መዘምር፤ ጋዜጠኛና ሰባኬ ወንጌል፤ ጸሐፊና ተርጓሚ፤ አስተዳዳሪና መምህር፤ የአውራጃ አብያተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፤ ኤርትራን ጨምሮ የአህጉረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የስምንት መምሪያዎች ምክትልና ዋና ሓላፊ፡፡
  • ሊቁ በሓላፊነት በተመደቡባቸው ቦታዎች ኹሉ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጡት÷ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ለማስተማር፤ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት፤ ሰበካ ጉባኤያትንና ሰንበት ት/ቤቶችን ለማቋቋም፣ ለማደራጀትና ለማጠናከር፤ አገልጋዮች ካህናትን በትምህርትና ሥልጠና በማብቃት አስተዳደርን ለማሻሻልና ተጠቃሚ ለማድረግ፣ የቤተ ክርስቲያንን የውስጥ ድርጅት በንዋያተ ቅድሳትና በጽ/ቤት መገልገያዎች ለማሟላት እንደነበር ዜና ሕይወታቸው በስፋት አትቷል፡፡
  • የአብነት ት/ቤቶችን፣ የካህናት ማሠልጠኛዎችንና ኮሌጆችን በበላይነት በሚያስተባብረው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የትምህርትና ማሠልጠኛ መምሪያ ለሦስት ጊዜያት በዋና ሓላፊነት ተመድበው የላቁ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ ከእኒኽም በመንግሥት የተወረሱ 27 መንፈሳውያንና ዘመናውያን ት/ቤቶችን በተለይም የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲመለስ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሐሳብ በማቅረብና በቅ/ሲኖዶስ ከተወሰነም በኋላ የበኩላቸውን ክትትል በማድረግ መንፈሳዊ ኮሌጁ ለቤተ ክርስቲያናችን ተመልሷል፡፡
  • በመምሪያ ደረጃ የሊቃውንት ጉባኤ አባል ኾነው ከተመደቡበት ጥቅምት ወር ፲፱፻፹፰ ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው መዳረሻ ከሌሎች ሊቃውንት ጋራ በመኾን ካከናወኗቸው ተግባራት መካከል÷ ቤተ ክርስቲያናችን የራስዋ የተጣራ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲኖራት 81 ቅዱሳት መጻሕፍትን በግእዝ ቋንቋ መሠረትነት አርመውና አስተካክለው ለኅትመት አብቅተዋል፡፡ ለካህናትና ምእመናን በሴሚናር ሲያሰለጥኑበት የቆዩት የቃለ ዐዋዲ ደንብ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሻሻል የበኩላቸውን ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፣ ሥርዐተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት›› መጽሐፍ ከሊቃውንት ጉባኤ አባላት ጋራ በአንድነት አዘጋጅተው ለምእመናን እንዲዳረስ አድርገዋል፡፡ በርካታ የቅዱሳን ገድላትና የመላእክት ድርሳናት ከግእዝ ወደ አማርኛ ቋንቋ መልሰዋል፡፡
  • የቤተ ክህነት ሥነ ጽሕፈት ኮሚቴ አባል በመኾን በዐበይት የቤተ ክርስቲያን በዓላት በሚወጡ ኅትመቶችና በሚሠራጩ የሬዲዮ መግለጫዎች በቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃዎችና በምርምር የተደገፉ፤ አንባቢንና አድማጭን የሚያረኩ በርካታ ጽሑፎችን በማቅረብ በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፉ ታላቅ ምሁር ነበሩ፡፡ በግል አዘጋጅተው ካሳተሟቸው መጻሕፍት መካከል ‹‹ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን››፤ ‹‹ሳታዩት የምትወዱት›› በሚል ለትምህርትና ለተግሣጽ ባሰራጯቸው ሥራዎቻቸው ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና ለነገረ ሃይማኖት መጠበቅ ተከራክረዋል፤ ተሟግተዋል፡፡ በተለይም ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን በኮሌጅ ደረጃ እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ ራሱን ችሎ የቆመ የትምህርት ክፍል ኾኖ እንዲሰጥ ግንባር ቀደም አስተዋፅኦ አድርገዋል፤ መጽሐፉም በኮሌጆችና በካህናት ማሠልጠኛዎች ለመምህራንና ለተማሪዎች መመሪያና ማጣቀሻ ኾኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡
  • የሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አገልግሎት ዓለም አቀፋዊም ነበር፡፡ ከግንቦት ፲፬ – ፴ ቀን ፲፱፻፸፯ ዓ.ም. የያሬዳዊ ማሕሌትን ዐውደ ትርኢት በምዕራብ ጀርመን ለማሳየት ከተመረጡት ሊቃውንት አንዱ በመኾን የማሕሌታችንን ሥርዐት አሳይተው ተመልሰዋል፡፡ እ.አ.አ ከሐምሌ ፱ – ፲፭ ቀን ፲፱፻፶፭ ዓ.ም. ‹‹ክርስቶስን ዛሬ መስበክ›› በሚል ርእስ በእስክንድርያ በተደረገው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ የቤተ ክርስቲያናችን መልእክተኛ በመኾን ጥንታዊ እምነቷንና ሥርዐቷን በቃልም በጽሑፍም በመግለጥ ተሳትፈዋል፡፡ በየመንና በጅቡቲ ለሚኖሩ ምእመናን ለበርካታ ጊዜ እየተመላለሱ መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡፡
*           *           *
  • ከደግ ቤተሰብ ተገኝተው በመልካም አስተዳደግ የወጡት ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ በትዳራቸውም የጋብቻ ጽናት ምሳሌነታቸውን በተግባር ያረጋገጡ ናቸው፡፡ ጥር ፲፪ ቀን ፲፱፻፶፭ ዓ.ም. በተክሊልና በሥርዐተ ቁርባን ካገቧቸው የሕግ ባለቤታቸው ወ/ሮ ድጋፍ ወርቅ ፈቄ ጋራ የ፶ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ የጋብቻ በዓላቸውን ከኹለት ዓመት በፊት አክብረው ነበር፡፡ ስምንት ልጆችንና ዐሥር የልጅ ልጆችን አፍርተውም ለወግ ለማዕርግ አብቅተዋል፡፡
  • ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል በሢመተ ክህነት÷ በ፲፱፻፵፩ ዓ.ም. ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማዕርገ ዲቁና፤ ሰኔ ፲፩ ቀን ፲፱፻፶፱ ዓ.ም. ከብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ሢመተ ቅስና ተቀብለዋል፡፡ የትምህርት ዝግጅታቸው በዜማ፣ በአቋቋም፣ በቅኔና በነገረ ሃይማኖት ላይ ያተኮረ ኾኖ ትርጓሜ መጻሕፍትንና የቤተ ክርስቲያን ታሪክን ከተለያዩ ሊቃውንት በመማር ምስጢር አደላድለዋል፡፡ በ፲፱፻፶፫ ዓ.ም. ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በከፍተኛ የነገረ መለኰት ትምህርት የቴዎለጂ ዲፕሎማ ተቀብለዋል፡፡ በቅድስት ሥላሴ ት/ቤት እና በዳግማዊ ምኒልክ የአንደኛና የኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተምረው አጠናቀዋል፡፡
  • ‹‹በዕለተ ሰንበትና በዐበይት በዓላት እየቀደሱና እያወደሱ፣ በሥራ ቀናት በቢሮ እየሠሩ፣ ለምእመናን ወንጌል እየሰበኩ፣ በመንፈሳዊ ኮሌጆችና በካህናት ማሠልጠኛዎች እያስተማሩና እያሠለጠኑ ከአንድ ሊቅ በሚጠበቅ መልኩ በተጠያቂነት ደረጃ በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ ሙሉ አገልግሎት ሲያበረክቱ ኑረዋል፡፡
Lique Kahinat Kinfe Gabriel Funeral
ዕረፍቱ ለሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ (ሚያዝያ 19 ቀን 1929 – ታኅሣሥ 19 ቀን 2007 ዓ.ም.)
  • በቀድሞው የሸዋ ክፍለ ሀገር በይፋት አውራጃ በማፉድ ወረዳ በደብረ ምሥራቅ ሾተል ዓምባ በኣታ ለማርያም አጥቢያ ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ.ም. ተወለዱ፡፡ ስማቸው ክንፈ ገብርኤል፤ ያረፉትም የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ዋናው በዓል በሚከበርበት በታኅሣሥ ገብርኤል፤ ኹሉን ማድረግ የሚችል አምላክ ለነፍሳቸው ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን ያድልልን፤ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን ይስጥልን፤ በእርሳቸው እግር ምሁራንን እንዲተካልን ፈጣሪን በጸሎት እንለምነዋለን፡፡››
የሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬን ዜና ሕይወት ወዕረፍት ከዚኽ በታች ይመልከቱ፡፡

ሰበር ዜና – የሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ተጠያቂው ሊቅና ኹለገቡ ባለሞያ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ዐረፉ

Lique Kahinat Kinfe Gabriel Altaye
የሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን (Liturgical Theology) ተጠያቂው ሊቅ÷ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ
ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንንና አገራችን ኢትዮጵያን በክህነት፣ በሊቅነት፣ በመምህርነት፣ በአስተዳደር እና በጸሐፊነት ሞያቸው በብቃትና በትጋት ሲያገለግሉ የኖሩት ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ዐረፉ፡፡
የሊቁ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል ሞተ ዕረፍት የተሰማው÷ ዛሬ፣ እሑድ ታኅሣሥ ፲፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በአዲስ አበባ ቀበና መካነ ሕይወት ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ከሚገኘው መኖርያ ቤታቸው ነው፡፡
በመኖርያ ቤታቸው÷ በቤተ ሰዎቻቸውና በወዳጆቻቸው መካከል ያረፉት ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል፣ ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ በበርካታ ዘርፎችና በተለያዩ የሓላፊነት ደረጃዎች ሲሠሩ ከኖሩበት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ከነበረባቸው ከፍተኛ የደም ግፊትና የነርቭ ሕመም ጋራ በተያያዘ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በጡረታ የተገለሉ ቢኾንም በመምሪያ ደረጃ የሊቃውንት ጉባኤ አባልነታቸው አገልግሎታቸውን ቀጥለው ቆይተዋል፡፡
ከዘመናችን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መካከል ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል በልዩነት የሚታወቁትና የሚታወሱት÷ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን (Liturgical Theology) ራሱን ችሎ የቆመ የትምህርት ዘርፍ (discipline) ኾኖ ጎልቶ እንዲወጣና በሥርዐተ ትምህርትም መርሐ ትምህርት ተቀርፆለት እንዲታወቅ÷ በምሁራን አነጋገር የራሱ ጉባኤ እና ወንበር እንዲኖረው÷ ባደረጉበት ጥረታቸውና ድካማቸው ነው፡፡
ለዚኽም በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በተለያዩ መጻሕፍት የሚገኙትን የአምልኮ መፈጸሚያ ሥርዓታት በተመጠኑ ገጾች በማስተጋባት ለጥናት እንዲመች አድርገው ያዘጋጁበት ‹‹ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን›› የተሰኘው ዝነኛው መጽሐፋቸው በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡
ባለፉት ዐሥርት ዓመታት፣ በቴዎሎጂ ኮሌጆቻችን፣ በካህናት ማሠልጠኛዎቻችንና በሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን ጸሎተ ቅዳሴውንና ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ጨምሮ ተግባራዊውን ትምህርተ መለኰት (Practical Theology) ለማስተማር በመመሪያነትና ማጣቀሻነት እያገለገለ የሚገኘው ይኸው የሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል ‹‹ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን›› መጽሐፍ ዛሬም በተደጋጋሚ የመታተም ዕድል ማግኘቱም ከፍተኛ ጠቀሜታውን ያሳያል፡፡
ሊቁ መጽሐፉን ከማዘጋጀት ባሻገር በመንፈሳዊ ኮሌጆቻችን (በቅድስት ሥላሴ፣ በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ) በከፍተኛ ደረጃ እንዲኹም በበርካታ መድረኮች ብዙ ሺሕ ምእመናንን ለዓመታት አስተምረውበታል፤ ሳይፋልስ ተጠብቆ እንዲኖርም ሳያሰልሱ መክረውበታል፡፡ በዚኹ መጽሐፍና ከሌሎች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ጋራ በየጊዜው ባዘጋጇቸው በርካታ ጽሑፎቻቸው ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ለመበረዝ በኅቡእም በገሐድም የሚያሤሩ አላውያንና መናፍቃንን ሞግተውበታል፤ ገሥጸውበታል፡፡
የቤተ ክርስቲያናችንን አስተዳደር የሚመራው ጠቅላይ ቤተ ክህነት እንደ ተቋም መደራጀት በጀመረባቸው ዓመታት አገልግሎታቸውን የወጠኑት ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል÷ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶችን ‹‹በእሑድ ትምህርት ቤት›› በየአጥቢያው አሰባስቦ በማስተማር ሰንበት ት/ቤቶች አኹን በሚገኙበት መልክ እንዲቋቋሙ የማድረጉን ጅምር ከወሰዱት፣ ስብከተ ወንጌልን በተለያዩ የብዙኃን መገናኛዎች (በጽሕፈትም በቃለ ስብከትም) በማስፋፋት ከሚታወቁት መምህራን ተርታ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም የዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ የቀሳውስትና የመምህራን ማሠልጠኛ በተለይም በቅኔ፣ በአቋቋም እና በመጻሕፍተ ሊቃውንት በጉባኤ ያካበቱትን ሞያቸውን በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በጀመሩት አገልግሎታቸው በብዙ አትርፈውበታል፡፡ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅን በምክትል ዲንነት መርተዋል፤ በጠቅላይ ቤተ ክህነት በሰው ኃይል አስተዳደርና የአስተዳደር መምሪያ በሓላፊነት ተመድበው በምስጉንነት ሠርተዋል፡፡
በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ተጠያቂነታቸውና ጠበቃነታቸው እንደ ዓምድ የሚታዩት ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል፣ በመድረክ ትምህርትና በቢሮ ሓላፊነት ብቻ ሳይወሰኑ በቤተ መቅደሱና በቅኔ ማሕሌቱ ክህነታዊ አገልግሎት ሕመማቸውን ታግሠው ጭምር እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው የጸኑ ብርቱ አባት ነበሩ፡፡
ይህ ዜና በሚጠናቀርበት ሰዓት የሚወጡት መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ የሊቁ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ የቀብር ሥነ ሥርዐት ነገ፣ ታኅሣሥ ፳ ከቀኑ በ9፡00 ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ሰባክያነ ወንጌል እና በአባትነት ትጋት ሲያገለግሏቸው የኖሩት ምእመናን ልጆቻቸውና ወዳጆቻቸው በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ተገልጦአል፡፡
የቅዱሳን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር የአባታችንን ነፍስ ያሳርፍልን፤ ከማኅበረ ቅዱሳን ይደምርልን፡፡

ረቡዕ 24 ዲሴምበር 2014

የገና ዛፍ የነጮች የባዕድ አምልኮ መገለጫ መሆኑን ያውቃሉ? የገና ዛፍ ታሪክና አመጣጡ




የገናን ዛፍ የት መጣውን /ምንጩን/ ስናጤነው ቅዱሳት መጻሕፍት እንዲህ ይነግሩናል። በዞራስተርን የሁለት አማልክት ዕምነት የሚያምኑት ምዕራባውያን አዲሱን ዓመታቸውን /2015/ ለመቀበል ዝግጀት ላይ ይገኛሉ። በዞራስተርን የሁለት አማልክት ዕምነት መሠረት ክፉውና ደጉ የተባሉ ሁለት አማልክቶች አሉ። እንደ ዕምነቱ አስተሳሰብ ከሆነ እዚህ ምድር ላይ የሆነው እየሆነው ያለውና የሚሆነውም ማንኛውም ነገር በሙሉ የሚከናወነው በእነዚህ በሁለቱ አማልክቶች ፉክክር ነው። ክፉው አምላክ ከሰለጠነ /የበላይ ከሆነ/ በምድር ላይ ክፉ የሆኑ ብዙ ነገሮች ይከሰታሉ። በተቃራኒው ደግሞ ደጉ አምላክ ከሰለጠነ በጎ ነገሮች ይከሰታሉ ማለት ነው። ምዕራባውያኑ ታዲያ ደጉን አምላካቸውን ማለትም ጣዖታቸውን ሳተርን ብለው ይጠሩታል።
በምዕራቡ ዓለም የክረምቱ ወቅት በጣም አስቸጋሪ ነው። ዛፎች ሁሉ ቅጠሎቻቸው ይረግፋሉ። ልምላሜ አይታይባቸውም። ፅድ ግን በተፈጥሮው ይህን አስቸጋሪ ወቅት ተቋቁሞ የማለፍ ኃይል አለው። በመሆኑም ፅድ ክፉውን ዘመን /ክረምቱን/ ተቋቁሞ መልካሙ ዘመናቸው እስኪመጣላቸው ድረስ በልምላሜ ይቆይላቸዋል። ይህም ሳተርን /ደጉ አምላካቸው/ ከክፉው አምላክ ለመሸሸግ በፅድ ውስጥ ተደብቆ ይኖራል ብለው ያመናሉ ምዕራባውያኑ። እናም ብራ ሲሆን /በእኛ መስከረም ጠባ እንደምንለው ነው/ የደጉን አምላክ ‹‹የእንኳን ደህና መጣህ›› በዓልን በድምቀት ያከብራሉ።
ምስጋና ለፅዱ ይሁንና ደጉ አምላካቸውን ደብቆ ስላቆየላቸው ባለውለታ ስለሆነ የደጉን አምላክ የእንኳን ደህና መጣህ በዓል ሲያከብሩ ታዲያ ፅድን ለበዓላቸው ማድመቂያነት ይጠቀሙበት ነበር። ይኸው ትውፊታቸው ዛሬም ድረስ አለ። በአጭሩ ከጥንት ጀምሮ እነርሱ ይኽን በዓል የሚያከብሩት ሳተርን ለተባለው ጣዖት /ደጉ አምላክ/ ያደርጉት የነበረው ሥርዓት ነው። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ክርስትናን በአዋጅ ካስፋፋበት ጊዜ ጀምሮ በውጭው ዓለም ጥንት የነበሩ ብዙ ጣዖታዊ በዓላት ክርስቲያናዊ በዓል ሆነው አሁንም ድረስ በብዙ ሀገራት እየተከበሩ ይገኛሉ። /ነገር ግን ልደትንና ትንሣኤን ጨምሮ ሌሎችም በዓላት ቢሆኑ ሥርዓታቸውን በጠበቁ መልኩ የሚከበርባቸው አንዳንድ ሀገራት እንዳሉ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ለማስገንዘብ ይወዳል።/
በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ይኸው እስከዛሬ እኛም ይኽንኑ የባዕድና የጣኦት አምልኮ በዓላቸውን በእነሱው ልማድ መሠረት የፅድ የገና ዛፍ እየሠራን ስናከብርላቸው ኖረናል። አሁንም ትንሽ ቀን ብቻ የቀረውን የገናን በዓል በእንዲሁ ዓይነት ሁኔታ ለማክበር ሽር ጉድ እያልን ነው። አባቶቻችን ሲናገሩ ‹‹እግዚአብሔር ዓለሙን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ሰው ሆኖ ዓለሙን ያዳነበት ጥበቡ እጅግ ረቂቅና ጥልቅ ነው›› ይላሉ። እንዴት ደስ የሚል አገላለፅ ነው!!! ታዲያ ምን ዋጋ አለው? አለመታደል ሆኖ ይሁን አሊያም አለማወቃችን ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋን ይግባውና እጅግ ድንቅ የሆነውን የጌታችንን የአምላካችንን የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ከእንደዚህ ዓይነቱ ምዕራባዊ የጣዖት በዓል ጋር ቀላቅለን እናከብራለን። ይህ እጅግ አሳዘኝ ነገር ነው በእውነት!
በአንድ ወቅት በምዕራባውያን የገና በዓል ሰሞን ‹‹BBC channel 4›› ላይ የበዓል መርሀ ግብር /program/ ቀርቦ ነበር። በመርሀ ግብሩ ላይ የተለያዩ የዕምነት ድርጅቶች የበዓል አከባበር፣ የጸሎትና የመዝሙር ሥርዓትና ሌሎችንም ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ከቀረቡ በኋላ የመርሀ ግብሩ መሪ በመጨረሻ እንዲህ ነው ያለው፡- “now let us see the real Christianity” ማለትምአሁን እውነተኛውን የክርስትና ሃይማኖት እንመልከትበሚል መሸጋገሪያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን የበዓል አከባበር ስነ-ሥርዓት ማስተላለፍ ጀመረ። ካህናት አባቶች ወረብ ሲያቀርቡ፣ የቅዳሴውን ሥርዓት፣ መዝሙሩ ሲዘመር፤ ጧፉ እየበራ ወንጌሉ ሲነበብ፣ እጣኑ እየጤሰ ስብሐተ እግዚአብሔር ሲቀርብ...... ሁሉንም በየተራ ማቅረብ ጀመረ። እናም እነርሱ ማለት ምዕራባውያን ስለ ዕምነት ጉዳይ እውነት የሆነውን ነገር ፍለጋ ፊታቸውን ወደ እኛ ባዞሩበት ወቅት እኛ ደግሞ እውነተናውን ማንነታችንን ባንጥልና የአጉል ባህል ተገዢዎች ባንሆን ብሎም በአምልኮ ጣኦታቸው ተሳታፊዎች ባንሆን መልካም ነው። መልካም ነው ብቻም ሳይሆን መንፈሳዊና ሞራላዊ ግዴታዎችም አሉብን። በእርግጥ እኛ የዚህ ዘመን ትውልዶች የግሎባላይዜሽን ጎርፍ ጠራርጎ የወሰደን ስለሆንንና ‹‹በጣም ስልጡኖችና ዘመናውያንም›› ስለሆንን ይህ ምን ማለት እንደሆነ ላይገባን ይችላል፤ እንዲገባንም አንፈልግም፡፡ 
የእነርሱን ጥሩውንና መጥፎውን ነገር እንኳን ለይተን መውሰድ ስላልቻልንና ሁሉንም ነገር ከነ አሠስ ገሠሱ ስለምንቀበል ይህንን ደካማ ጎናችንን ያወቁ ‹‹ዘመናዊ ቅኝ ገዢዎቻችን›› ለሁሉም ነገር ምቹ ሆነንላቸው አግኝተውናል። የሴቶቻችን እርቃን መሄድ፣ አካሎቻቸውን መነቀስና መበሳት፣ የወንዶች አለባበስና ፀጉር አቆራረጥእነዚህና ሌሎቹም ነገሮች በዘመናዊነት ሰበብ የመጡብን የዘመናዊ ቅኝ ግዛት ውጤቶች ናቸው፡፡ በግል አዳኝ ‹‹ኢየሱሴ›› ስም ብዙኃኑን ሕዝባችንን ፈጣሪውን አስክደው አምላክ የለሽ አደረጉትና ለግሎባላይዜሽናቸው የተመቸ ዝርው ትውልድ ፈጠሩ፡፡ አሁንማ ጭራሽ ለይቶላቸው ‹‹church of Satan›› በማለትየሰይጣን ቤተክርስቲያንከፍተው አባሎቻቸው በሆኑ ‹‹ታዋቂ የሂፖፕ›› አቀንቃኞቻቸው አማካኝነት የአባላቶቻቸውን ቁጥር ለመጨመር እኛም ሀገር ብቅ ብለውልናል፡፡ ግብረ ሰዶማዊነት እንደግለሰብ ነፃነት አድርጋችሁ ካልተቀበላችሁ እርዳታ አንሰጣችሁምም ተባልን፡፡ እሺ እነዚህና ሌሎቹም አስከፊ ኃጢአቶቻቸውን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እንድንቀበል ቢያስገድዱንም ቢያንስ እኛ በራሳችን ጊዜ ለምን የራሳችንን ባሕል ድምጥማጡን በማጥፋት የእነርሱን ባሕል እንከተላለን? የዘመናዊነት መገለጫው የራስን ባሕልና እምነት በሌሎች መተካት ሆነ እንዴ? ድሮ ቅኝ ቅዛት ተገዝተን ቢሆን ኖሮ ምንድን ነበር የምናጣው? ቀላል ነው መልሱ፡- የራስ ማንነት፣ እምነት፣ ባሕል፣ ታሪክአይኖረንም ነበር፡፡ አሁን ታዲያ በዘመናዊው ቅኝ አገዛዝ ሥርዓት ምክንያት እነዚህን ነገሮች አላጣናቸውም ይሆን? እንዲያው በመድኃኔዓለም! እባካችሁ ከፊት ለፊታችን በታላቅ ጉጉትና ተስፋ የምንጠብቀውን ከድቅድቅ ጨለማ ወጥተን ብርሃን ያገኘንበትን የአማኑኤልን የልደት በዓል የገናን ዛፍ በመጠቀም ከነጮቹ ባዕድና ጣኦት አምልኮ ጋር አንቀላቅለው፡፡ ልደቱን ቅድስት ቤተክርስቲያን እንደሚገባው አድርጋ ታከብረዋለችና እኛም ልጆቿ እንደሚገባው መጠን ልደቱን እናክብር፡፡ የገና ዛፍ የባዕድ አምልኮ መገለጫ ነው፡፡ ማህቶተ ቤተክርስቲያን ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ምንድን ነበር ያለው! ‹‹ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? የእግዚአብሔርን ታቦት በጣዖት ቤት ውስጥ የሚያኖር ማነው? 2 ቆሮ 614-16፡፡
በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ” 2 ቆሮ 135፡፡ 
ተዘጋጀ በጀማል ሀሰን ዓሊ (ስመ ጥምቀቱ ገብረሥላሴ) 
የአባቶቻችን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር በሃይማኖታችንና በኦርቶዶክሳዊ ማንነታችን ያፅናን አሜን።
(
የጽሑፉ ምንጮች፡- አናቆጸ ሲኦል በብርሃኑ ጐበና፤ ሐመር 5 ዓመት 1 1989 .

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...