ከ120 ተጠቋሚ ኢትዮጵያውያን መካከል
በበጎ ሰው ዳኞች የተመረጡት ሰባት ኢትዮጵያውያን ‹በጎ ሰዎች› ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 2006 ዓም በኢሊሊ ሆቴል በተከናወነ
ሥነ ሥርዓት ተሸለሙ፡፡
የመንግሥት ባለ ሥልጣናት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ ከየትምህርት ቤቱ የተጋበዙ ወጣቶችና ሌሎችም በተገኙበት በተከናወነው የሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ በግብርና፣ ኢንዱስትሪና ኢንተርፕርነርሺፕ ዘርፍ ወ/ሮ ቤተ ልሔም ጥላሁን፣ በማኅበራዊ አገልግሎት ዘርፍ ብጹዕ አቡነ ዮናስ፣ በርዳታና ሰብአዊ ሥራ ዘርፍ ዶክተር በላይ አበጋዝ፣ መንግሥታዊ የሥራ ኃላፊነትን በመወጣት ዘርፍ አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ፣ በጥናትና ምርምር ዘርፍ አምባሳደር ዘውዴ ረታ፣ በቅርስ፣ ባሕልና ቱሪዝም ዘርፍ አብዱላሂ ሸሪፍ፣ በኪነ ጥበብ ዘርፍ ደግሞ አባባ ተስፋዬ ሣሕሉ ተሸልመዋል፡፡
ሽልማቶቹን የተለያዩ ታዋቂ
ኢትዮጵያውያን የሸለሙ ሲሆን ከተሸላሚዎቹ መካከል አምባሳደር ዘውዴ፣ አምባሳደር ቆንጂትና ወ/ሮ ቤተ ልሔም ጥላሁን
ለሥራ ከሀገር ውጭ በመሆናቸው በተወካዮቻቸው በኩል ተቀብለዋል፡፡
ለሀገር በጎ ሥራ መሥራትንና ያለውንም
በጎ ተጽዕኖ በተመለከተ ዶክተር እሌኒ(የ2005 የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚ) እና ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ጸጋየ ንግግር ያደረጉ ሲሆን
ገጣሚ አበባው መላኩና ገጣሚ ምንተስኖት ደግሞ ግጥሞችን አቅርበዋል፡፡
የመዝጊያ ንግግሩን ሲስተር ዘቢደር
ዘውዴ የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መሥራችና የ2006 የበጎ ሰው ሽልማት ዕጩ አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም የአምባሳደር ልብስ ስፌት
ባለቤት አቶ ሰይድ ለአባባ ተስፋየ አሥር ሺ ብርና ሙሉ ልብስ ሲሸልሙ የሊንከን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ለሜሪ ጆይ አሥር ሺ ብር
ለግሰዋል፡፡
ዳሽን ቢራ መርሐ ግብሩን በክብር
ስፖንሰር አድርጓል
ሸገር ሬዲዮ፣ ኢቢኤስ ቴሌቭዥን፣ ኢሊሊ
ሆቴል፣ ምርፋቅ ካፌና ሬስቶራንት አጋሮቻችን ሆነው ለሰጡን አገልግሎት እናመሰግናለን
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ