የደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንድነት ገዳም ገዳማዊ
ሥርዓቱ እንደተጠበቀ ቢሆንም የጎርፍ አደጋ፤ የብዝኅ ሕይወት መመናመን፤ የሕገ ወጥ የመሬት ወረራና ሌሎችም ችግሮች
እየተፈታተኑት ይገኛል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በገዳሙና በማኅበረ ቅዱሳን ባለሙያዎች
ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ወደ ሥራ ተገብቷ
ፕሮጀክቶቹንም በተያዘላቸው እቅድ መሠረት ለማስፈጸም በጠቅላይ
ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ሠኔ 8 ቀን 2006 ዓ.ም. የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ላይ ፕሮጀክቶቹንና
ገዳሙን አስመልክቶ የተዘጋጀ መጽሔት ለምእመናን ተሰራጭቷል፡፡ ከመጽሔቱ ያገኘናቸውን ጥቂት መረጃዎች እናካፍላችሁ፡
የደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃማኖት አንድነት ገዳም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር- ጎጃም መውጫ በ104 ኪሎ ሜትር ርቀት፤ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ 4.5 ኪሎ ሜትር ተገንጥሎ የሚገኝ የአንድነት ገዳም ነው፡፡
ገዳሙ በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በ1296 ዓ.ም. የተቆረቆረ ሲሆን፤ 710 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በገዳሙ አስተዳደር ሥር ከአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በተጨማሪ የቅዱስ አማኑኤል እና የቅዱስ ፊልጶስ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡
በገዳሙ ውስጥ የሚጎበኙ የተለያዩ የነገሥታት ሥጦታዎች፤ ቅዱሳት መጻሕፍት፤ ንዋየ ቅድሳት፤ የቅዱሳን አጽም፤ ፈውስ የሚገኝባቸው የጸበል ቦታዎችም ይገኛሉ፡፡
የደብረ ሊባኖስ ገዳም አምስቱ ስያሜዎችን ስንመለከት፡-
ምድረ ግራሪያ፡-
ግራሪያ የሚለውን ስያሜ የሰጠችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ከወዳጇ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወደ ምድረ ግብጽ ስትሰደድ በኢትዮጵያ ውስጥ ከቆየችባቸው ቦታዎች አንዱ ይህ ቅዱስ ቦታ ነው፡፡ ለአንድ ሳምንት ቆይታ አድርጋ የቦታውን ስም ምድረ ግራሪያ ስትል ሰይማዋለች፡፡ ግራሪያ ማለት ኩሉ ይገርር ሎቱ፤ ሁሉ ይገዛላታል ማለት ነው፡፡ አንድም ግራር በቁሙ ለሁሉ ጥላ፤ መሰብሰቢያ እንደሆነ ደብረ ሊባኖስም የሁሉ ጥላ መሰብሰቢያ ነውና ምድረ ግራሪያ ተብሏል፡፡
ደብረ አስቦ፡-
ደብረ አስቦ ማለት የዋጋ ተራራ ማለት ሲሆን፤ የሰየመውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ አባታችን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዚህ ቅዱስ ሥፍራ ሃያ ዘጠኝ ዓመታት ከጸለዩ በኋላ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ ቦታውንም ደብረ አስቦ፤ የድካምህ ዋጋ፤ የስምህ መጠሪያ ይሁንልህ በማለት ሰይሞታል፡፡
ኤላም፡-
ኤላም ማለት የእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ማለት ነው፡፡ ይህ ቦታ የአባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት አጽም ለአርባ ዓመታት የቆየበት ቅዱስ ሥፍራ ነው፡፡ ስያሜውም የአቡነ ዮሐንስ ከማ ነው፡፡ ዮሐንስ ከማ የጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት የመንፈስ ልጅ ናቸው፡፡ ኤላም የበረከት ቦታ፤ የሰላም ሠፈር ነው፡፡ የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተሰውሮ ይገኝበታል፡፡
ደብረ ሊባኖስ፡-
ደብረ ሊባኖስ ማለት የሊባኖስ ተራራ ማለት ነው፡፡ ጻድቁ አቡነ ሊባኖስ የተባሉት ሮማዊ አባት ለአርባ ዓመታት የጸለዩበት፤ ብዙ ገቢረ ተአምራት ያደረጉበት፤ ከእግዚአብሔር ጋር የተገናኙበት ነው፡፡ “ትትሌአል ወትከብር እምነ ኲሎን አድባራት ወገዳማት እሞን ለአህጉር፤ ከአድባራትና ገዳማት ትከብራለች፤ ከፍ ከፍም ትላለች፤ ለሀገራትም እናት ትባላለች” ሲል፡፡
አባ ሊባኖስ በጌታ የተወደደውንና የቅዱሳን ከተማ ደብረ ሊባኖስን በጣም ይወዱት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ይህ ቦታ ከአንተ በኋላ ለሚመጣው ለተክለ ሃይማኖት ነውና አንተ ወደ ትግራይ ሀገር ሒድ፤ እድል ፈንታህ በዚያ ነው አላቸው፡፡ እርሳቸውም አርባ ዓመታት የደከምኩበት ለከንቱ ነውን? አሉት ቅዱሳን አጽንኦተ በዓት ይወዳሉና፡፡ መልአኩም ስለ ድካምህ ይህ ቦታ ደብረ ሊባኖስ ይባላል እንጂ ደብረ ተክለ ሃይማኖት አይባልም አላቸው፡፡ እሳቸውም ፈቃድህ ይሁን ብለው ወደ ትግራይ ሀገር ሔዱ፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ ደብረ ሊባኖስ እየተባለ ይጠራል፤ ስመ ተፋልሶም አላገኘውም፡፡
ዜጋዎ አመል፡-
ዜጋዎ አመል ማለት የአየር ንብረቱ የተመቸ፤ የሚያስደስት፤ ተስማሚና ለኑሮ የሚመች ማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ዜጋዎ አመል ተብሏል፡፡
ምንጭ፡- ልሳነ ደብረ ሊባኖስ፤ ቅጽ-1፤ ቁጥር-1፤ ሠኔ 2006 ዓ.ም.
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ