ሰኞ 24 ኖቬምበር 2014

ጾም - ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው (ክፍል ኹለት)



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ሐሙስ ኅዳር 11 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
ውድ የመቅረዝ አንባብያን፡፡ በትናንቱ ጕባኤ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ብዙ ነገር አሳስቦን ነበር፡፡ ጉባኤውን ለመታደም ወደ ቤተ ክርስቲያን ዓውደ ምሕረት ከመጣን አይቀር ከነበሽታችን ልንመለስ እንደማይገባ ይልቁንም መንፈሳዊ መድኃኒትን ውጠን ልንመለስ እንደሚገባን፣ የነፍስና የሥጋ መድኃኒት ከምትኾን ከጾም ጋር አብረው የማይሔዱ ነገሮች ምን ምን እንደኾኑ፣ ከእንግዲኽ ወዲኽ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና አውጥታ ጾም ነው ስላለችን ብቻ ሳይኾን በዓላማ ልንጾም እንደሚገባና ሌላ ብዙ ነፍስን የሚያለመልሙ ትምህርቶችን አስተምሮን ነበር፡፡ ምንም እንኳን የዛሬው ትምህርት ለእኛ ኹለተኛ ጕባኤ ቢኾንም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ግን ከትናንቱ ጋር በአንድ ቀን ጕባኤ ያስተማረው ነው፡፡ የመዠመሪያው ቀን ስብከቱም ዛሬ ላይ እንጨርሳለን፡፡ በነገራችን ላይ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቁመቱ አጭር ስለነበረ ምእመናኑ ባዘጋጁለት መድረክ ላይ ወጥቶ ነበር የሚያስተምረው፡፡ ዛሬ በየዓውደ ምሕረቱ የምንመለከተው አትሮንስም ከዚያን ጊዜ ዠምሮ አገልገሎት ላይ የዋለ ነው፡፡ መልካም ጕባኤ እንዲኾንልን በመመኘት ፊታችንና መላ ሰውነታችንን ሦስት ጊዜ በማማተብ ትምህርቱን በትጋት ኾነን እንድንማር በድጋሜ ጋበዝናችኁ፡፡
 

   በመንፈሳዊ ሕይወት ቸልተኛ መኾንና ለራስ ሕይወት ግድ አለመስጠት የብዙ ኃጢአቶች ምክንያት እንዲኹም ነጸብራቅ ነው፡፡ ልክ እንደዚኹ ጾምም የብዙ በረከት ምክንያት እንዲኹም ነጸብራቅ ነው፡፡ እንደምታስታውሱት አዳም በገነት በነበረ ጊዜ ለመንፈሳዊ ሕይወቱ ቸልተኛና ግድ የሌለው እንዳይኾን ብሎ ልዑል እግዚአብሔር አንድ ትእዛዝ ሰጥቶት ነበር፡፡ እንዲኽ በማለት፡- “ከገነት ዛፍ ኹሉ ትብላለኅ፤ ነገር ግን መልካሙንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ” /ዘፍ.2፡16-17/፡፡ እዚህ ጋር “ብላ፤ አትብላ” የሚለው የሚለው ትእዛዝ በምሳሌ ስለ ጾም ጥቅም የሚያስረዳ ነው፡፡  የሰው ልጅ ግን ይህቺን አንዲት ትእዛዝ ለመጠበቅ አልታዘዝ አለ፤ ትዕግሥት አጣ፤ ሞትንም በራሱ ላይ አመጣ፡፡ የሰው ልጆች ጠላትና ክፉ መንፈስ የኾነው ዲያብሎስም እንደምታስታውሱት አዳም በገነት የአታክልት ስፍራ ደስ ብሎት እንደ ሰማያውያን መላዕክት ኾኖ እየኖረ ስለነበረ ቀናበት፡፡ አምላክ ትኾናለህ ብሎም አታለለውና የነበረውን ቅድስና እንኳን አሳጣው፡፡ አያችኁ ልጆቼ! ያለንን ቅዱስ ነገር በአግባቡ ሳንይዝ ይልቁንም ሌላ ከዚኽ የበለጠ ነገር መመኘት መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰው “በዲያብሎስ ቅንኣት ምክንያት ሞት ወደ ዓለም ገባ” ያለንም እኮ ስለዚኹ ምክንያት ነው /ጥበብ 2፡24/፡፡ እንግዲኽ ሞት ወደ ሰው ልጆች እንዴት በስንፍና እንደመጣ እያስተዋላችኁ ነው ልጆቼ? በኋላ ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ ሲጻፍም በመንፈሳዊ ሕይወት መድከምን እንዴት እንደሚነቅፍ እንመልከት፡- “ሕዝቡም ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ” /ዘጸ.32፡6/፤ “ወፈረ፤ ደነደነ፤ ሰባ፤ የፈጠረውንም እግዚአብሔርን ተወ፤ የመድኃኒቱንም አምላክ ናቀ” /ዘዳ.32፡15/፡፡ የሰዶም ኗሪዎችም የዲን እሳት ዘንቦባቸው የጠፉት ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው እጅግ ቸልተኞች ስለነበሩና ለመብልና ለመጠጥ ሰፊ ቦታን ስለ ሰጡ ነው፡፡ ነቢዩ ሕዝቅኤል ስለዚኹ ጉዳይ ሲነግረን እንዲኽ ብሏል፡- “የሰዶም ኃጢአት ይኽ ነበረ፤ ትዕቢት እንጀራን መጥገብ መዝለልና ሥራ መፍታት” /ሕዝ.16፡49/፡፡ በአጭር አነጋገር አብዝቶ መብላትና መጠጣት፣ ጾምን ችላ ማለት የብዙ ኃጢአቶች ምክንያት ነው፡፡
 እንግዲኽ ራስን አለመግዛት እንዴት አደገኛ እንደኾነ አያችኁ? አኹን ደግሞ ጾም እንዴት በረከትን እንደሚያመጣ እንመልከት፡፡ ሙሴ 40 ቀን ስለጾመ የእግዚአብሔር ሕግ የተጻፈበትን ጽላት ተቀበለ /ዘጸ.24፡18/፡፡ ከተራራው ሲወርድ ግን የሕዝቡን ኃጢአት ተመለከተና ኃጢአተኛ ሕዝብ የእግዚአብሔርን ሕግ መቀበል አይችልም ሲል ብስንት መለማመጥ የተቀበለውን ጽላት ወርውሮ ሰበረው፡፡ ይኽ ታላቅ ነቢይ በተሰበረው ፋንታ ሌላ ጽላት ለመቀበል 40 ቀናት ነው የጾመው /ዘጸ.34፡28/፡፡ ታላቁ ነቢይ ኤልያስም ልክ እንደ ሙሴ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾሟል፡፡ እንዲኽ በመጾሙም በእሳት ሠረገላ ተነጥቆ ወደ ሰማይ ተወሰደ፤ እስከ አኹን ድረስም አልሞተም፡፡ እጅግ አስደናቂ የኾነው ሰው ነቢዩ ዳንኤልም እጅግ ብዙ ቀናትን ይጾም ስለነበረ ተንኰለኞች ወደ አንበሳ ጕድጓድ እንኳን ቢጥሉት አንበሶች ሊበሉት አልቻሉም፡፡ አንበሶቹ ለነቢዩ ዳንኤል እንደ በጐች ነበሩ፡፡ አንበሶቹ በግ የኾኑት ግን ተፈጥሯቸው ተለውጦ በግ በመኾን ሳይኾን ዳንኤልን ሳይበሉት ከነተናጣቂ ተፈጥሯቸው ሳሉ ነው፡፡ የነነዌ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቁጣ ያስቀሩት በመጾማቸው ነው፡፡ እንደዉም በነነዌ የጾሙት ሰዎች ብቻ አልነበሩም፤ እንስሳቱም ጭምር እንጂ፡፡ በዚኽም ምክንያት እግዚአብሔር ሊያደርገው ከተናገረው ክፉ ነገር ተጸጽቶ አላደረገውም /ዮናስ 3፡10/፡፡ ከብሉይና ከሐዲስ ኪዳን እንዲኽ በመጾማቸው የተጠቀሙ ብዙ ሰዎችን መጥቀስ እንችላለን፡፡ ነገር ግን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያደረገው ነገር ኹላችንንም የሚያስተምር ነውና እሱን ብንመለከት፡፡ ኹላችኁም እንደምታውቁት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾሟል /ማቴ.4/፡፡ ሲጾምም ዲያብሎስን ድል አድርጎ አሳይቶናል፡፡ ጌታችን ይኽን ያደረገበት ምክንያት ዲያብሎስን ለማሸነፍ እኛም የጾምን ትጥቅ መታጠቅ እንዳለብን ሲያስተምረን ነው፡፡
እዚኽ ጋር ምናልባት ከእናንተ መካከል፡- “አባታችን! ቅድም እንደነገርከን እነ ሙሴ፣ እነ ኤልያስ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾመዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልክ እንደ ሙሴና እንደ ኤልያስ አንዲት ቀን እንኳን ሳይጨምር መጾሙ ለምንድነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይኽን ያደረገው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ጌታችን እንዲኽ የጾመው እኛን በጣም ስለሚወደን ነው፡፡ ምክንያቱም ሲዠምርም የእኛን ሥጋ ሳይዋሐድ መምጣት ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን በጣም ስለሚወደን ሥጋችንን ተዋሐደ፤ ከእኛ ከሰዎች ያልራቀ መኾኑን ሲያስረዳንም ጾመ፡፡
 እንግዲኽ ከላይ ለማየት እንደቻልነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሌሎችም ቅዱሳንም በመጾማቸው ምክንያት ዲያብሎስን አሸንፈውታል፡፡ በተለይ ቅዱሳኑ በመጾማቸው ምክንያት ለሥጋቸውም ለነፍሳቸውም ብዙ ጥቅምን አግኝተዉበታል፡፡
 ስለዚኽ እጅግ የምወዳችኁ ልጆቼ! የጾም ጥቅም እንዴት ትልቅ እንደኾነ እየተማርንና እየተመለከትን ሳለ የጾም ወራት ሲቃረብ ደስ ብሎን ልንቀበለውና ንቁዎች ኾነን እጅግ ብዙ ጥቅምን ልናገኝበት ይገባናል ብዬ እማልዳችኋለኹ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳን የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል” ብሎ እንዳስተማረን /2ኛ ቆሮ.4፡16/ ጾም ሲገባ እጅግ ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ከዚኽ የሐዋርያው ቃል እንደምንረዳው ጾም ማለት ነፍሳችን የበለጠ የምትወፍርበት መንገድ ነው ማለት ነው፡፡ እንጀራ ሥጋችን እንዲወፍር እንደሚያደርገው ኹሉ ጾም ደግሞ ነፍሳችን እንድትወፍር ያደርጋታል፡፡ ጾምን የምታዘወትር ነፍስ ከእግዚአብሔር ጋር ያላት ቀረቤታ እጅግ ስለሚጨምር ገና በዚኽ ምድር ሳለች ቅድስና በቅድስና እየጨመረች፣ ምሥጢራተ እግዚአብሔርን እያስተዋለች፣ የመንግሥተ ሰማያትን ጣዕም እየቀመሰች ትሔዳለች፡፡ እጅግ ብዙ ጭነትን የተሸከመች መርከብ ባሕሩንና ወጀቡን ማለፍ እንደሚያቅታት ኹሉ መብልና መጠጥ የሚያበዛ ሰውም የዚኽን ዓለም ወጀብ ማለፍ አይችልም፡፡ ቀለል ያለና ተመጣጣኝ የኾነ ጭነትን የያዘች መርከብ ግን ብዙ ችግር ሳይገጥማት የታሰበላት ቦታ በታሰበላት ጊዜ  ትደርሳለች፡፡ መብልና መጠጥን ሳያበዛ ጾም የሚወድ ክርስቲያንም ንቃተ ኅሊናው ብሩህ ነው፡፡ በዚኽ ምድር በሚያጋጥሙት ችግሮችም በቀላሉ እጅ አይሰጥም፡፡ ዛሬ ላይ በዚኽ ምድር የሚያጋጥሙት ጊዜያዊ ችግሮች እንደ ጥላና ሕልም እንደሚያልፉ ይገነዘባል፡፡ እንዲኽ እንዳናስብና በዚኽ ምድር በሚያጋጥሙን ጥቃቅን ችግሮች እንድንጨናነቅ የሚያደርጉን በመንፈሳዊ ሕይወታችን እጅግ ቸልተኞች ስንኾን ነው፡፡ ምክንያቱም የዘወትር ሐሳባችን መብልና መጠጥ ላይ ከኾነ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ደካሞች ነው የምንኾነው፡፡ ሥጋችን ይወፍራል፡፡ የማሰብና የማመዛዘን ዓቅማችን ይቀንሳል፡፡ ለነፍሳችን ምንም በማይጠቅም እንተ ፈንቶ ነገርም ተጠምደን እንውላለን፡፡  
 ስለዚኽ እጅግ የምወዳችኁ ምእመናን ሆይ! በጊዜያዊ ነገር ብቻ እየተጠመድን በመንፈሳዊ ሕይወታችን ቸልተኞች አንኹን ብዬ እለምናችኋለኹ፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ቸልተኞች ስንኾን የምንጐዳው በሚመጣው ዓለም ብቻ አይደለም፡፡ በዚኽ ምድር ሳለንም በመብልና በመጠጥ ብዛት ምክንያት የሚመጡ ብዙ በሽታዎች ተጠቂዎች ነው የምንኾነው፡፡ እኛ በሐዲስ ኪዳን ያለን ክርስቲያኖች ነን፡፡ በዚያ በጨለማው የብሉይ ኪዳን የነበሩ ሰዎች እንኳን በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ቸልተኞች እንዳይኾኑ ይልቁንም ጾምን እንዲያዘወትሩ ይነገራቸው ነበርና እባካችኁ ቸልተኞች አንኹን ብዬ እለምናችኋለኹ፡፡ እስኪ አምላካችን እግዚአብሔር ምን እንደሚለን እናድምጥ፡- “ክፉውን ቀን ከእናንተ ለምታርቁ፣ የግፍንም ወንበር ለምታቀርቡ፣ ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ ለምትተኙ፣ በምንጣፋችኁም ላይ ተደላድላችኁ ለምትቀመጡ፣ ከበጐችም መንጋ ጠቦትን ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ለምትበሉ፣ በመሰንቆም ድምፅ ለምትንጫጩ፣ እንደ ዳዊትም የዜማን ዕቃ ለምታዘጋጁ፣ በፋጋ የወይን ጠጅ ለምትጠጡ፣ እጅግ ባማረ ሽቱም ለምትቀቡ፣ ስለዮሴፍ መከራ ግን ለማታዝኑ ለእናንተ ወዮላችኁ” /አሞጽ.6፡3-6/፡፡ ልጆቼ! እግዚአብሔር በነቢዩ አሞጽ አድሮ እስራኤላውያንን እንዴት አድርጐ እንደወቀሳቸው፣ መብልንና መጠጥን ሲያበዙ እንዴት አድርጐ እንደገሠፃቸው አያችኁን? እንደዉም በደንብ አስተውላችኁት ከኾነ አብዝተው መብላታቸውንና መጠጣታቸውን ብቻ አይደለም የወቀሳቸው፡፡ ጨምሮም እነዚኽ ሰዎች ከዚኽ በላይ ደስታ እንደሌላቸው፥ ደስታቸው ግን እንደ ጧት ጤዛ ብዙ እንደማይቆይ ነግሯቸዋል፡፡
 አኹን በዚኽ ምድር ላይ የምንመለከታቸው ነገሮች ልክ እንደዚኽ የሚጠፉ ናቸው፡፡ ክብርም በሉት፣ ሥልጣንም በሉት፣ ሀብትና ንብረትም በሉት፣ የምናገኛቸው መልካም አጋጣሚዎችም በሉት፣ ኹሉም ጠፊዎች ናቸው፡፡ ከእነዚኽ አንዱ ስንኳ ዘለዓለማዊ የለም፡፡ ኹሉም እንደ ወራጅ ውኃ የሚያልፉ ናቸው፡፡ የሙጥኝ ብለን ልንይዛቸው ብንሞክር እንኳን ብዙ ልናቆያቸው አንችልም፡፡ የምንቀረው ባዶአችን ነው፡፡ መንፈሳዊ ነገሮቻችን ግን የእነዚኽ ተቃራኒ ናቸው፡፡ እንደ ጽኑ ዐለት አይንቀሳቀሱም፤ ትተዉን አይሔዱም፡፡ በጊዜ ብዛት አይበላሹም (Expire date የላቸውም)፡፡ እስኪ አኹን ልጠይቃችኁ ልጆቼ! የማይጠፋውን ሀብት በሚጠፋው ሀብት የምንቀይረው እንዴት ብንደነዝዝ ነው? ዘለዓለማዊውን ደስታችን በዘለዓለማዊ ለቅሶ፣ ዘለዓለማዊውን ሕይወት በጊዜያዊ ሕይወት፣ ዘለዓለማዊውን ሀብታችን በሚጠፋ ሀብት መቀየራችን ምን ዓይነት ስንፍና ቢይዘን ነው?
 ስለዚኽ በዚኽ ጕባኤ የታደማችኁ ኹላችኁም ምእመናን ሆይ! እለምናችኋለኹ፡፡ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ተገቢውን ትኵረት እንስጠው፡፡ ለምድራዊ ነገር ፈጣን ኾነን ሳለ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ሰነፎች አንኹን፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ጠንካሮች እንድንኾን የምታደርገንን ጾምንም እንውደዳት፡፡ ከርሷ ጋር ያሉት ሌሎች በጐ ምግባራትንም (ጸሎት፣ ስግደት፣ ምጽዋት፣ ወዘተ) እንውደዳቸው፡፡ ከዛሬ በኋላ አዲስ የአኗኗር ስልትን (Renewed Life style) እንዠምር፡፡ በየቀኑ መልካም ምግባራትን መሥራት የሚያስደስተን እንኹን፡፡ በዚኽ በምንቀበለው ጾም ብዙ መንፈሳዊ ተግባራትን እናድርግና ራሳችንን በሰማያዊ ክብር እናስጊጥ፡፡ እንዲኽ የምናደርግ ከኾነ ጾሙ ሲፈታ ወደ ቅዱስ ሥጋውና ወደ ክቡር ደሙ ሳናፍር መቅረብ ይቻለናል፡፡ በልቡናችን ውስጥ የነበረውን ቆሻሻ ኹሉ ስለምናስወግድ ንጹሓን ኾነን ከዚያ ሰማያዊ ማዕድ ተሳታፊዎች መኾን እንችላለን፡፡ ከዚያም በጐ ምግባራችን የማይጠፋና ኃይልን ስለሚያገኝ በመጨረሻው ቀን ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን የሚለውን የሕይወት ቃል መስማት እንችላለን፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ ስለማይለየን ሕይወታችን በጸሎትና በምልጃ የተሞላ ይኾናል፡፡ እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተን መኖር ይቻለናል፡፡ ይኽን እንድናደርግ ሰውን በመውደዱ ሰው የኾነው ክርስቶስ ይርዳን፡፡ አሜን!!!

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...