ሰኞ 24 ኖቬምበር 2014

ጾም - ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው (ክፍል አንድ)



(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ረቡዕ ኅዳር 10 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
 ይኽን ጽሑፍ ወደ አማርኛ የመለስነው ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የኦሪት ዘልደትን መጽሐፍ ከተረጐመበት ከመዠመሪያው ድርሳኑ ላይ ነው፡፡ ስብከቱ ረዘም ስለሚልም አንዱን ድርሳን በክፍል በክፍል አድርገን አቅርበነዋል፡፡ ሊቁ ይኽን ስብከት የሰበከው ዐቢይ ጾም ሊገባ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት እንደኾነ ከስብከቱ መረዳት እንችላለን፡፡ ምንም እንኳን ከፊታችን የምንቀበለው ጾም ጾመ ነቢያት ቢኾንም የጾም ዓላማው አንድ ነውና ለዚኽም ጊዜ ይስማማል በማለት አኹን ልናቀርበው ወደናል፡፡ በመኾኑም ልክ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሚያስተምርበት ዓውደ ምሕረት እንዳለን ኾነን በማሰብ ፊታችንና መላ ሰውነታችንን በትእምርተ መስቀል ሦስት ጊዜ በማማተብ ቃሉን በትሕትና እንድንማር እንጋብዛችኋለን፡፡ መልካም ጉባኤ!!! 

ቤተ ክርስቲያን እንደዚኽ በልጆቿ ደምቃ ሳይ፥ እናንተም ጕባኤውን ለመታደም ደስ ብሏችኁ ስትመጡ ዐይታ ነፍሴ ሐሴት አደረገች፤ ደስም ተሰኘች፡፡ ጕባኤውን ለመታደም መጥታችኁ ፊታችኁ እንደምን በደስታ እንደተመላ ዐይቼ ጠቢቡ ሰው “ደስ ያለው ልብ ፊትን ያበራል” እንዳለው ልቤ በደስታ ፍንክንክ አለብኝ /ምሳ.15፡13/፡፡ ቀጣዩ ወራት የቁስለ ነፍሳችንን መድኃኒት የምናገኝበት ወርሓ ጾም ነውና ይኽን የምስራች እነግራችኍ ዘንድ ዛሬ ጧት ከወትሮው በተለየ ትጋት ነው የተነሣኹት፡፡ ደግ አባት ነውና ባለፉት ወራት የሠራነውን ኃጢአት ሥርየት እናገኝበት ዘንድ ሽቶ አምላካችን ፈውሰ ሥጋ ፈውሰ ነፍስ የሚኾን ቅዱስ ጾምን አዘጋጅቶልናል፡፡
ስለዚኽ ከእኛ መካከል አንድ ስንኳ ተስፋ የሚቈርጥ፣ በድብርትም የሚያዝ ከቶ አይገኝ፡፡ ይልቁንም ደስ የምንሰኝበትን፣ የሕመማችንን ፈውስ የምናገኝበትን መድኃኒት እረኛችን እግዚአብሔር አዘጋጅቶልናልና ወርሓ ጾም በመምጣቱ ደስ ልንሰኝ ይገባል፡፡ አሕዛብ ይኽን ወራት ደስ ተሰኝተን መቀበላችንን አይተው ይፈሩ፡፡ በእኛና በእነርሱ መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ አይተውም ይማሩ፡፡ በዓላቶቻቸው በዘፈንና በስካር፣ ይኽም በመሰለ ሌላ ርኵስ ግብር የተሞሉ ናቸውና፡፡
 ምእመናን ከዚኽ አሕዛባዊ ግብር ተለይተን በዓል ልናደርግ ይገባናል፡፡ በምግባር በትሩፋት ልናጌጥ ልናሸበርቅ ይገባናል፡፡ እውነተኛ ጾም ማለት ሰዎች የሚድኑበት፣ ሰላምና አንድነት የሚያገኙበት፣ ክፉ ግብርን ቈርጠው የሚጥሉበት፣ አርምሞን ገንዘብ የሚያደርጉበት፣ በመብልና በመጠጥ ከመንጋጋት የሚላቀቁበት ነው፡፡ በዚኽ በወርሓ ጾም ዕረፍተ ሥጋ ወነፍስ እንዲኹም አርምሞ፣ የነፍስ ወሥጋ ፍቅርና ደስታ፣ ራስን መግዛት፣ እንዲኹም ሌሎች እዚኽ መዘርዘር የማንችላቸው ብዙ የብዙ ብዙ ምግባር ትሩፋቶችን ገንዘብ የምናደርግበት ነው፡፡
 እንኪያስ እጅግ የምወዳችኁ ምእመናን ሆይ! አንዳች የሚረባንን ነገር ይዘንም ወደ ቤታችን እንመለስ ዘንድ ቃላችንን በታላቅ ትጋትና ጉጉት ኾናችኁ ተቀበሉት ብዬ እማልዳችኋለኹ፡፡  ኹላችንም ወደዚኽ ጉባኤ የመጣነው ሌላ ነገር ሽተን አይደለምና፡፡ ወሬ ለማውራት፣ የተባለውን ነገር ምንም ሳንሰማ ለማጨብጨብ፣ ከዚያም ምንም የሚረባ ነገርን ሳንይዝ ወደ ቤታችን ለመመለስ ወደዚኽ ጉባኤ አልመጣንምና ቃላችንን በማስተዋል ትከታተሉት ዘንድ እማልዳችኋለኹ፡፡ እግዚአብሔር በእኔ በባርያው አድሮ ለነፍሳችን ድኅነት የሚጠቅም ነገር ይናገራል፡፡ ስለዚኽ እጅግ ብዙ የሚጠቅም ነገር ሰንቀን ወደ ቤታችን እንመለስ ዘንድ እማልዳችኋለኹ፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ማለት ሐኪም ቤት ናት፡፡ ወደርሷ የሚመጡትም ተገቢውን መድኃኒት አግኝተው መሔድ አለባቸው፡፡ ቃሉን ብቻ አድምጠን ነገር ግን በሕይወታችን አንዳች ተግባራዊ የኾነ ለውጥ ከሌለን ወደ ጉባኤ መምጣታችን፣ ቃለ እግዚአብሔር መማራችን አንዳች ረብሕ የለውም፡፡ ብጹዕ ሐዋርያ ጳውሎስ እንዲኽ እንዳለ፡- “በእግዚአብሔር ፊት ሕግን የሚያደርጉት ይጸድቃሉ እንጂ ሕግን የሚሰሙ ጻድቃን አይደሉምና” /ሮሜ.2፡13/፡፡ ክብር ምስጋና ለስም አጠራሩ ይኹንና አምላካችን ክርስቶስም፡- “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ኹሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም” /ማቴ.7፡21/፡፡ ስለዚኽ እጅግ የምወዳችኁ ምእመናን ሆይ! ቃሉን በመስማታችን ብቻ አንዳች የምንጠቀመው ነገር ስለሌለ የሰማነውን የምናደርግ እንጂ የምንሰማ ብቻ አንኹን፡፡ እንዲኽ ከኾነም (ሰምተን የምንፈጽም ከኾነ) እምነታችን ሕይወት ያለው እምነት ይኾናል፡፡
 ስለዚኽ እግዚአብሔር ስለ ጾም የሚያስተምረንን ትምህርት ለማዳመጥ እዝነ ልቡናችንን እንክፈት፡፡ ጾም ሙሽሪትን ትመስላለች፡፡ ሙሽሪትን በሠርግ አዳራሽ ኾነው የሚቀበሏት ሰዎች ቤቱን ያስጌጡታል፤ ይሸልሙታል፡፡ ወደ ሠርጉ አዳራሽ የሚገባውን ሰው የሠርግ ልብስ ለብሶ እንደኾነ፣ የቆሸሸ እንዳልኾነ አይተው ያስገቡታል፡፡ እኛም እንዲኽ ልንኾን ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ልቡናችንን በማንጻት፣ ልል ዘሊል ከመኾን በመራቅ፣ የክፋት እርሾን በማስወገድ፣ ከጾም ጋር አብረው የሚመጡትን የሚያጅቧትን መልካም ምግባራትንም ለመቀበል የልቡናችንን ውሳጤ በመክፈት የምግባር እናት፣ የማስተዋል እንዲኹሉም ለሌሎች ምግባራት ኹሉ ንግሥት የምትኾን ጾምን ልንቀበላት ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ይኽን ያደረግን እንደኾነ ታላቅ ሐሴት እናደርጋለን፤ ርሷም ቁስለ ነፍሳችንን ትፈውስልናለች፡፡ በሌላ አገላለጽ ብነግራችኁ ሐኪሞች በአንድ ታማሚ ሰውነት ውስጥ ያለውን ቆሻሻ፣ መርዘኛ ፈሳሽን ማስገድ ሲፈልጉ መዠመሪያ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር ታማሚው ምግብ ከመውሰድ እንዲቈጠብ ነው፡፡ ታማሚው ለጊዜው ምግብን ከመብላት ካልተከለከለ ሓኪሞቹ የሚሰጡት መድኃኒት እንደተፈለገው ውጤት አይሰጥም፡፡ እኛም ቁስለ ነፍስ ቁስለ ሥጋ የምትፈውሰውን ጾም ስንቀበላት ከዚኽ በላይ ልንኾን ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስን የምንሻ ከኾነ ልቡናችንን ንጹሕና ንቁ በማድረግ ልንወስዳት ይገባናል፡፡ እንዲኽ ካልኾነ ግን ከጥቅሟ ይልቅ ጉዳቷ ያመዝናል፡፡
 ዛሬ የምነግራችኁ ነገረ ለአንዳንዶቻችኁ እንዲኹ ተራ የልበ ወለድ ንግግር እንደሚኾንባችኁ አውቃለኹ፡፡ እኔ ግን በዓላማ (ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስን ለማግኘት) የምንጾም እንኹን እንጂ እንዲኹ የልማድ ባርያ አንኹን ብዬ እማልዳችኋለኹ፡፡ እስኪ ንገሩኝ! በየቀኑ ሆዳሞችና ሰካራሞች በመኾናችን የምናገኘው ጥቅም ምንድነው? አንዳች የምናገኘው ጥቅም የለም፡፡ ይልቁንም የከፋ ጉዳትን በራሳችን ላይ የምናመጣ ነን ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ከልክ በላይ ጠጥተን ስንሰክር የማስተዋል ልቡናችን ይጠፋል፤ የጾም ጥቅሟም አብሮ ይጠፋል፡፡ እስኪ ንገሩኝ! እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ብዙ መጠጥን ከሚጠጡ ሰዎች በላይ የሚያንገሸግሽ ምን አለ? ወይንን በመጠጣት በየመሸታ ቤቱ አድረው ፀሐይ ከምትወጣባቸው ሰዎች በላይ የሚያሳዝን ማን አለ? እነዚኽ በመጠጥ ብዛት የሚሰክሩ ሰዎች ከሚያገኙት ሰው ጋር ይጋጫሉ፤ ጠጪው ሰካራሙ ተብለው በማኅበረ ሰብኡ ይታወቃሉ፤ ቤታቸው የተናቀ ነው፤ የሚናገሩት ነገር ቁምነገር ስለሌለው ሕፃን ዐዋቂው ይሳለቅባቸዋል፡፡ ከዚኽም በላይ በጣም የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል እንደሚል “ሰካሮች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” /1ኛ ቆሮ.6፡10/፡፡ ወዮ! … ወዮ! … ወዮ! … እንደ ጧት ጤዛ ለሚጠፋ ርካታ የዘለዓለምን መንግሥት ማጣት እንደምን ያለ ጉስቁልና ነው?
 እዚኽ ጉባኤ የተሰበሰብን ምእመናን በእንደዚኽ ዓይነት ስንፍና ከመያዝ እግዚአብሔር ይጠብቀን! እያንዳንዷን ቀን በትዕግሥትና ራስን በመግዛት ኾነን በዙርያችን ከሚያንዣብበው የዲያብሎስ ወጀብም ተጠብቀን ወደ ነፍሳችን ወደብ ይኸውም ወደ እውነተኛ ጾም ከርሷ የሚገኘውን ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስም እናገኝ ዘንድ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...