2015 ኤፕሪል 22, ረቡዕ

እስመ በእንቲኣሁ ይቀትሉነ ኲሎ አሚረ፡፡ ወኮነ ከመ አባግዕ ዘይጠብሑ ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፤እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን:: መዝ.43፡22

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት የተሰጠ የሐዘን መግለጫአትምኢሜይል
              
                                                                                ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም.
         

ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በክርስቶስ ሞት እና ትንሣኤ ነው፡፡ ይህንንም ስንል ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ምንም በደል ሳይገኝበት በአይሁድ ተከስሶ በግፍ የሞት ፍርድም ተፈርዶበት በዕለተ ዓርብ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ ደሙን አፍስሶ የሰው ልጆችን ዕዳ በደል ደምስሶ ነጻ እንዳወጣንና ዘለዓለማዊ ሕይወትን እንዳደለን በማመን እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ በማለት በሰጠው አምላካዊ ትእዛዝ መሠረት ትመራለች ማለታችን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንም ይህንኑ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት አምነው በሥራ ሲገልጡ ኑረዋል፤ ዛሬም በዚሁ እውነታ ይገኛሉ፡፡

ስለእውነት መሥዋዕትነት መክፈል ለቤተ ክርስቲያን እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ በየዘመናቱ እግዚአብሔር ለዚህ ክብር ያደላቸው ቅዱሳን ሰዎች የጌታን ፈለግ ተከትለው ስለክርስትናቸው ወይም በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ በማመናቸውና ይህንንም በይፋ በመመስከራቸው ብቻ በክፉዎች ሰዎች እጅ በሥጋቸው መከራ እየደረሰባቸው ለሞት በመብቃታቸው ሰማዕት እየሆኑ አልፈዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችንም እነዚህን ለክርስቶስ ያላቸውን ፍቅር እሰከ ሞት ድረስ በመታመን የገለጹትን ልጆቿን በታላቅ መንፈሳዊ ክብር ታዘክራቸዋለች፤ ምእመናንም በእነርሱ የሕይወት ጎዳና እንዲማሩና በኑሮአቸውም እንዲጽናኑ እያደረገች ትገኛለች፡፡ በዚህ ሂደትም የክርስቲያኖችን ሕይወት የቀጠፉትን ዓላውያንን ድርጊታቸውን እያወገዘች አድራጊዎቹ ግን በክፉ መንፈስ የተመሩ ሰዎች በመሆናቸው ለእነርሱም ልቡና እንዲሰጣቸውና ምህረትን እንዲያገኙ ከእግዚአብሔር መለመንን አላቋረጠችም፡፡ ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ በመሰቀል ላይ ሳለ አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ቅር በላቸው በማለት የበደሉንን እንኳ ይቅርታ እንድናደርግላቸው ባስተማረን ትምህርት መሠረት ነው፡፡

የክርስትና ተግባር እንደየዘመኑ ሁኔታ የሚቀያየር ሳይሆን ከእግዚአብሔር አንድ ጊዜ የተሰጠና የጸና ዘላለማዊ እውነታ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ዛሬም በምእመናን ሁሉ ዘንድ ህልው ሆኖ ይኖራል፤ በሥራም ይገለጣል፡፡

በሰሞኑ ራሱን እስላማዊ መንግሥት (IS) እያለ በሚጠራው ዓለም አቀፋዊው አሸባሪ ድርጅት በተለያየ ምክንያት ወደ ሊቢያ የገቡ ክርስቲያን ወንድሞቻችንን እና እኅቶቻችንን ይዞ በማሰር በውስጣቸውም 30 የሚያህሉትን ወንድሞቻችንን በሁለት የተለያዩ ቦታዎች በአሰቃቂ ሁኔታ እንደገደላቸው በይፋ በኢንተርኔት ባሰራጨው የቪዲዮ መረጃ አሳውቋል፡፡ በዚሁ መረጃው ላይም የተገደሉት ወንድሞቻችን የተገኘባቸው አበሳ ወይም ወንጀል ክርስቲያን ሁነው መገኘታቸው (በተለይም እነርሱ ጠላታችን ያሏት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አባል መሆናቸው) እና ሃማኖታቸውንም አንቀይርም ማለታቸው እንደሆነ በግልጽ አሳውቋል፡፡ ይህም ሳይበቃው የገደለበትን አሰቃቂ መንገድ በቪዲዮ ቀርጾ በማስፈራሪያ ቃላት በማጀብ ለዓለም ሁሉ አስራጭቶታል፡፡ ይህ ሁኔታ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ዋጋ የከፈለለትን የሰው ልጅ አንገቱን በካራ ቀልቶ ደሙን ማፍሰስ እና ሕይወቱን ማጥፋት እጅግ የሚዘገንን ሰይጣናዊ ተግባር ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያናችንም ቅዱስ ሲኖዶስ ይህ አሳዛኝ ዜና እንደተሰማ ድርጊቱን አውግዞ በቤተ ክርስቲያኒቱ ደረጃ የጸሎት ጊዜ ማወጁና ምእመናን ሁሉ በየአሉበት አካባቢ ሁነው እንዲሳተፉ ጥሪ ማሳለፉ ይታወቃል፡፡ ስለዚህም ምእመናን ሁላችንም በዚህ የአንድነት መገለጫ በሆነው መንፈሳዊ ተግባር ላይ ልንሳተፍ ያስፈልጋል፡፡

እነዚህ በበረኻው ላይ ደማቸው የፈሰሰው ወንድሞቻችን ለሃይማኖታቸው ያሳዩት ጥብዓት ለሁላችንም ትልቅ ትምህርት የሚሆንና አክብሮት የሚገባው ተግባር ነው፡፡ እነርሱ ወደጠራቸው ወደ እግዚአብሔር በክብር ተጉዘዋል፡፡ በወንጌል ለእናንተም ለወዳጆቼ እላችኋለሁ ሥጋን የሚገድሉትን በኋላም አንድ ስንኳ የሚበልጥ ሊያደርጉ የማይችሉትን አትፍሩâ€Ãƒ‚ºÃƒÃ‚¢€Ãƒ‚º በማለት የተጻፈውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል በሥራ በመተርጎም ምስክር ሁነዋል፡፡ ሉቃ.12.4 የተማሩትን የክርስትና ትምህርት በትክክል በሥራ በማሳየታቸው እጅግ የሚያኮራ ተግባር ፈጽመዋልና ሁላችንም እንኰራባቸዋለን፡፡

በርግጥ በሥጋ ስለተለዩን እንደ ሰውነታችን ልናዝንና ልናለቅስ እንችላለን፡፡ በተለይም ቤተሰዎቻቸው እና የቅርብ ወዳጆቻቸው የደረሰባቸው ኀዘንና ጉዳት ከፍትኛ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ ስለዚህም የልብ ስብራትን የሚጠግነው እግዚአብሔር አምላካችን መጽናናትን እንዲሰጣቸው እንጸልያለን፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ወንድሞቻችን የተጓዙት ሁላችን ወደምንናፍቀው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመሆኑ ልናዝን አይገባም፤ በእግዚአብሔር መንግሥት ምስክር ያገኙ በመሆናቸው ደስ ሊለን እንጂ፡፡ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ ባለው አምላካዊ ቃል መሠረት በክፉዎች ሰዎች ፊት ያለፍርሃትና ያለኀፍረት ስለርሱ መስክረው በዐደባባይ መከራ ተቀብለዋል፡፡ ማቴ.10.32፡፡ እንዲሁም ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጎናጸፋል፣ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፤ በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ በማለት እንደተናገረው ቃሉ የታመነ የሆነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋጋቸውን እንደሚከፍላቸው ፍጹም እምነታችን ነውና በዚህ ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ራእ.ዮሐ.3.5፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ጸጋና ክብር አግኝተው ወደ አምላካቸው ለሔዱት የሃይማኖት ጀግኖች የክብር አሸኛኘት ማድረግና አኩሪ ተግባራቸውን ማዘከር ግን ያስፈልገናል፡፡ በዚህ ዘመን ላለነው ክርስቲያኖች ሁሉ ለሃይማኖታቸው ሕይወታቸውን አሳልፎ እስከመስጠት ድረስ መሥዋዕት በመሆን አብነት ሁነውናልና፡፡

ይህ ጭካኔና ክፉ ድርጊት የፈጸሙት ፉከራቸውን በዐደባባይ የገለጹት ሰዎች ምናልባት ክርስቲያኖች በዚህ ፈርተውና ተሰቅቀው ከሃይማኖታቸው ፈቀቅ የሚሉ፣ ቤተ ክርስቲያንም የምትሸማቅቅ አድርገው ገምተው ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን ሰማዕትነት ክርስትናን የሚያለመልምና የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን ከታሪክ ሊማሩት ይገባል፡፡ የመጀመሪያውን ክርስቲያናዊ ቤተሰብ ለመበተንና ክርስትናን በእንጭጩ ለማጥፋት አስበው አይሁድ ቅዱስ እስጢፋኖስን በዐደባባይ በድንጋይ ይወግረው ማስፈራሪያ እንዲሆን ገድለውት ነበር፡፡ ቢሆንም ግን ይህ ድርጊት ክርስቲያኖችን ከኢየሩሳሌም ከተማ ወጥተው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እንዲሔዱና ክርስትናን የበለጠ እንዲያስፋፉት አደረጋቸው እንጂ ቤተክርስቲያንን ማሸማቀቅ አልቻለም፡፡

በሮማውያን የኃያልነት ዘመንም እንዲሁ ነገሥታቱ ክርስትናን ለማጥፋት ብዙ ደክመዋል፡፡ ቢሆንም የነርሱ የጭካኔ ተግባር ክርስትና የበለጠ በቤተ መንግሥታቸው ጭምር እንዲሰበክና እንዲስፋፋ፣ የቤተ መንግሥቱ አባላት የነበሩ ሰዎችም ክርስትናን እየተቀበሉ ሰማዕታት እንዲሆኑ አደረጋቸው እንጂ ክርስትናን አላጠፋውም፡፡ በርግጥ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ክርስቲያኖች ኑሮአቸውንም ሆነ መንፈሳዊ ተግባራቸውን በካታኮምብ ውስጥ እንዲያደርጉ አስገድዶ እንደነበር ግን አንዘነጋውም፡፡ አሁንም በአንዳንድ ቦታዎች በክፉ አሳብ በሚመሩ ሰዎች ምክንያት እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ቢያጋጥም ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተምረንና በእግዚአብሔር ኃይል ታምነን ፍጹም ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድና ልናሳልፈው፣ ድል ልንነሣውም ይገባል፡፡

እኛ በክርስቶስ የደም ዋጋ የተገዛንና ዋጋም የተከፈለልን መሆኑን ሳንዘነጋ በክርስትናችን ምክንያት ዋጋ የሚያስከፍል ነገር ሲመጣ እንደነዚህ ወንድሞቻችን በጥብዐት ልንቆም ያስፈልጋል፡፡ እነርሱ ሕይወታቸውን ሰጥተው ለሃይማኖታቸው እንደተጋደሉ መደለያ የሆነው ጊዜያዊ ኑሮም እንዳላታለላቸው ሁሉ እኛም ሃይማኖታችንን ከሥጋዊ ፍላጎታችን በላይ ልናስቀድም እንደሚገባን የተማርንበት ክስተት በመሆኑ ሁላችንም እንዲህ ዓይነት ነገር ሲያጋጥመን ልንከተለው የሚገባንን የክርስትና አቅጣጫ ግልጽ በሆነ መንገድ በማሳየት ረገድ ለዚህ ዘመን ትውልድ መልካም አርአያ ሆነውናልና በዚህም ዘወትር ልናዘክራቸውና ልናመሰግናቸው ይገባናል፡፡

ክርስቲያኖች በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ ብንኖርም ከእግዚአብሔር ጋር በደስታ እንኖራለን በሥጋ ብንሞትም ወደ እግዚአብሔር እንሔዳለንና ሁሌም የእግዚአብሔር ነን፡፡ በመጽሐፍ በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፣ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን፡፡ እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን እንደተባለው በማንኛውም ሁኔታ በእግዚአብሔር ደስ ይለናል እንጂ በምንከፍለው ዋጋ ልንሳቀቅ አይገባንም፡፡ ሮሜ.14.8፡፡

ክርስትና ራስን ለሌላው አሳልፎ መስጠት ነውና አንዱ ወገናችን ሲያዝን በሐዘኑ ልንካፈል ጭንቀቱንም ተጋርተን ብንችል ልናቃልልለት ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፣ ከሚያለቅሱት ጋር አልቅሱ ሮሜ.12.15፤ በማለት እንዳስተማረው በማኅበራዊ ሕይወታችን በፍቅር መንፈስ ልንረዳዳ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም በዚህ በመከራ ጊዜ ሐዘንተኞችን ማጽናናት፣ እንዲሁም ደግሞ ገና በየእስር ቤቱ በችግርና በሰቆቃ ያሉትን ወገኖቻችንን በምትለው ዐቅም ሁሉ ልንረዳቸውና ከጎናቸው ልንቆም ያስፈልገናል፡፡

ከዚህ አንጻር ካህናት አባቶቻችንም ሆኑ መምህራነ ወንጌል ድርሻቸው የጎላ ነውና የተለመደ መንፈሳዊ አገልገሎታቸውን ፍጹም በሆነ ሓላፊነት እንደሚወጡ አንጠራጠርም፡፡ በተለይ የችግሩ ሰለባ የሆኑትን በመርዳቱ ረገድ ሁሉም ሰው በአፋጣኝ የድርሻውን እንደሚወጣ እምነታችን ነው፡፡ እዚህ ላይ በተለያየ ምክንያት ከሀገራቸው የወጡ፣ በተለያየ ችግር ውስጥ ያሉና ያለፉ ሁሉ አንዳቸው ሌላውን ወገናቸውን በመርዳት መንፈሳዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ በዚህ አጋጣሚ ማሳሰቡ አስፈላጊ ነው፡፡

ከዚህ ክስተት የምንማረው ሰው በመልካም ትምህርት ከተቀረጸ ነፍሱን ለሌላው አሳልፎ እስከመስጠት ድረስ እንደሚታገስ ለሃይማኖቱም ፍጹም ዋጋ ሊከፍል የሚችል መሆኑን ነው፡፡ ስለዚህ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ምእመናኗን በትምህርተ ሃይማኖትና በሥነ ምግባር በመቅረጹ ረገድ የበለጠ በርትታ እንድትሠራበት የሚያመላክት ነው፡፡ እውነተኛው የክርስትና ትምህርት ሌላውን ወደማጥፋት ሳይሆን ወደ ርኅራኄና የራስን ሕይወት ወደመስጠት፣ በአጠቃላይም እንዲህ ወደ መልካም ጎዳና ይመራልና፡፡

በአንጻሩ ደግሞ ክፉ ትምህርት ሰውን ወደ አውሬነት ሊቀይር የሚችል መሆኑን ይህን ኢሰብአዊ ተግባር ያለምንም ርኅራኄ ሲፈጽሙ ከምናያቸው ሰዎች እንገነዘባለን፡፡ ስለዚህ ሰዎችን ከልጅነታቸው ጀምሮ በጥሩ መንገድ መምራት፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን መስበክ፣ በአጠቃላይም መልካም የሆነውን ትምህርት ማስተማር ለሀገርም ሆነ ለዓለም የሚበጅ መሆኑን ተረድተን ሁላችንም የበኩላችንን እና የሚመለከተንን መወጣት እንደሚያስፈልገን ትምህርት ወስደንበታል ብለን እናምናለን፡፡

ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ከተሰማ ጀምሮ የተለያዩ አካላት ድርጊቱን በማውገዝ ኃዘናቸውን በመግለጽ ረገድ የየራሳቸውን ድርሻ እየተወጡ ይገኛሉ፡፡ ይህ በራሱ የጋራ አንድነትንና መረዳዳትን የሚያመለክት በመሆኑ በእጅጉ የሚያስመሰግን ተግባር ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህ የጭካኔ ሥራ በአጭር ጊዜ የተቀነባበረና የአንድ ወቅት ክስተት ሳይሆን በተደጋጋሚ እየተፈጸመ የብዙ ንጹሐን ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ከማውገዝ ባለፈ ሥር ነቀል ለውጥ ሊያመጣና ችግሩን ሊፈታ የሚችል ሥራ በመተባበር ሊሠራ ይገባዋል ብለን እናምናለን፡፡ ለዚህም የተለያዩ የእምነት ድርጅቶችና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ግንባር ቀደም ድርሻ ሊኖራቸው ስለሚገባ ልዩነትን ከማጉላት ይልቅ ለሰው ልጅ ሕይወት የሚጠቅም ነገር በመሥራት ሓላፊነታቸውን ሊወጡ፤ መንግሥታትንም ሊያሳስቡ ይገባል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ልጆች የሆንን ሁላችን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት በሆነው ትምህርቱ እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፣ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፣ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፤ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና፡፡ ማቴ.5.44-45፡፡ በማለት እንዳስገነዘበን ክፉ አድራጊዎቹ ድርጊታቸው የሚወገዝና ማንም ሰው ቢሆን ሊጸየፈው የሚገባ ቢሆንም ይህን የፈጸሙት ሰዎችና የአስተሳሰባቸው ደጋፊዎች የሆኑ አካላት ግን ከክፉ መንገዳቸው እንዲመለሱ በማድረግ ረገድ እንደ ክርስትናችን ትልቅ ሓላፊነት አለብን፡፡ በክርስትና ጎዳና የተጓዙ አባቶቻችንና እናቶቻችን የጭካኔ ተግባር እየፈጸሙባቸው ያሉትን ሰዎች ሳይቀር ምሕረት እንዲያገኙ ወደ እግዚአብሔር ያመለክቱላቸው እንደነበር ከታሪካቸውና ከገድላቸው እንማራለን፡፡ ስለዚህ እኛም ለእነዚህ ክፉ አድራጊዎቹ ሰዎች ልንጸልይላቸው፣ እግዚአብሔር እንዲምራቸው ልቡናን እንዲሰጣቸው ልንለምንላቸው ይገባል፡፡ በውስጣቸው ያለው መንፈስ እጅግ ክፉ ነውና ጌታም በወንጌል ይህ ወገን በጸሎትና በጦም ካልሆነ በምንም ሊወጣ አይችልም ማር.9.29፡፡ በማለት እንዳስተማረው እንዲህ ዓይነቱ ክፉ መንፈስ ከሰዎች እንዲርቅ በጾምና በጸሎት ልንተጋ ይገባናል፡፡

በመጨረሻም ስለሃይማኖታቸው ሰማዕትነትን የተቀበሉትን ወንድሞቻችንን አምላካችን እግዚአብሔር ቅዱሳንን ባከበረበት ክብር እንዲያከብራቸው፣ ለቅዱሳን ሰማዕታት ያቀዳጃቸውን የክብር አክሊል እንዲያቀዳጃቸው በፍጹም እምነት እየጸለይን ቤተሰዎቻቸውንና ወዳጆቻቸውንም ቸሩ ፈጣሪያችን መጽናናትን እንዲያድላቸው እንመኛለን፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...