‹‹ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዝንጉርጉርነቱን ሊለውጥ ይችላልን? ልጆቻችን የምንኮራባቸው መጻሕፍቶቻችን፣ የምንማርባቸው ዩኒቨርስቲዎቻችን ናቸው፤ አስተምረውናል፤ አኩርተውናል፤ አስከብረውናል››
የልጆቻን የኃይለ ሚካኤል(ኢያሱ ይኵኖ አምላክ) እና የኃይለ ኢየሱስን(ባልቻ በለጠ) ነፍስ ይማርልን፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን የሐዘን ዳርቻ ያድርግልን፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን የቤተሰቡን ሕይወት፣ የቤተሰቡን ሐዘን በመልካም ነገር፣ በፍቅር ነገር ይለውጥልን፡፡ ቤተሰቡን ያለምልምልን፡፡ ቤተሰቡን ያጽናልን፡፡ ደግ ያልኾኑ ሰዎችን ወደ ደግነት፣ ወደ ምሕረት፣ ወደ ቸርነት ይመልስልን፡፡ ለዓለሙ ኹሉ ሰላም መረጋጋትን ያድልልን፡፡ አገራችን ኢትዮጵያን በክብር በረድኤት ይጠብቅልን፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤
የውድ ልጆቻችን የሰማዕታቱ፣ የታማኝ ልጆቻችን፣ የጀግኖች ልጆቻችን፣ በኢትዮጵያዊ ባህላቸው፣ በኢትዮጵያዊ ትውፊታቸው፣ በእምነታቸው፣ በሥርዐታቸው፣ በወጋቸው ጸንተው፣ ለማንም ሳይበገሩ እና ለማንም ሳይደለሉ፣ ለሌላ እጃቸውን ሳይሰጡ፣ ሳይቀለበሱ ጀግንነትን ያስተማሩ ልጆቻችን፣ መጻሕፍት የኾኑ ልጆቻችን ወላጆች እና እዚኽ የተሰበሰባችኹ ውድ ወገኖቼ፤
ከክርስቶስ ልደት በፊት ሰባት መቶ ዓመታት ቀድሞ የነበረው ነቢዩ ኤርሚያስ፣ በዚያን ጊዜዋ ባቢሎን በዛሬዋ ኢራቅ፤ በዚያን ጊዜዋ ፋርስ በዛሬዋ ኢራን እየዘዋወረ ባስተማረበት ዘመን ስለ ኢትዮጵያውን አድናቆት፣ ክብር፣ ጀግንነት፣ አይበገሬነት በትንቢቱ ምዕራፍ 13 ቁጥር 23 ላይ እንዲኽ ብሏል፡- ‹‹ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዝንጉርጉርነቱን ሊለውጥ ይችላልን?››
ኢትዮጵያዊ ባህሉን፣ ኢትዮጵያዊ እምነቱን፣ ኢትዮጵያዊ አንድነቱን፣ ኢትዮጵያዊ ጀግንነቱን፣ ኢትዮጵያዊ ትውፊቱን በሌላ ሊቀይር ይችላልን? አይቀየርም፡፡ ነቢዩ ሠቆቃው ኤርሚያስ በተባለ መጽሐፉም ይህን በስፋት እየገለጸ ይናገራል፡፡
ውድ ወገኖቼ፤ ልጆቻችን እኮ ጀግኖች ናቸው፤ ልጆቻችን እኮ እጃቸውን አልሰጡም፤ ልጆቻችን እኮ አልተንበረከኩም፤ ልጆቻችን እኮ መጻሕፍቶቻችን ናቸው፤ ልጆቻችን እኮ አርበኞቻችን ናቸው፤ አልተማረኩም፤ የጀግና እናት አታለቅስም እንደተባለው ኹሉ፣ እናንተም የጀግኖች እናቶች ናችኹ፤ ልትኮሩ ይገባችኋል፤ ስማቸውን ለውጠው፣ ሃይማኖታቸውን ለውጠው፣ ሥርዐታቸውን ለውጠው፣ ተማርከው ቢኾን ኖሮ ነበር ማልቀስ የሚገባን፡፡
ውድ ወገኖቼ፤ የጀግኖች ወላጆች ናችኹና ልትኮሩ፣ ልትጽናኑ ይገባችኋል፡፡ እሰይ ልጄ፤ ተባረክ ልጄ፤ ለመንግሥተ ሰማያት ያብቃኽ ብላችኹ ልትመርቁ፣ ልትጸልዩ፣ ልትጽናኑ ይገባል፡፡ የመጽናኛ ዕለት ነው፤ ልጆቻችን አስተምረውናል፤ ልጆቻችን አኩርተውናል፤ ልጆቻችን አስከብረውናል፤ አስወድደውናል፤ በዓለም ደረጃ አገራችንን አስተዋውቀዋል፡፡
ውድ ወገኖቼ፤ እንዲኽ ላሉት ነው እንዴ የሚለቀሰው? አገር አጥፍቶ ለሔደ፣ በሙስና ተዘፍቆ ለሔደ፣ ሰክሮ ለሔደ፣ አመንዝሮ ለሔደ፣ ቀምቶ ለሔደ÷ ‹‹በምድር ኑሮው ተበላሽቶ፣ በሰማይ እንዴት ይኾን ከቶ›› ተብሎ የሚለቀስለት ለዚኽ ነው፡፡ ብዙ ልጆቻችን በየመልኩ ኸሉም አርበኛ ነው፡፡ አካሉን፣ ሕይወቱን፣ ወላጁን፣ ልጁን፣ ዘመኑን፣ ንብረቱን የሰጠ ስንት አለ? ውድ ወገኖቼ፤ እንዴ፣ እነዚኽማ ልጆቻችን የምንኮራባቸው መጻሕፍቶቻችን ናቸው!! የምንማርባቸው ዩኒቨርስቲዎቻችን ናቸው ልጆቻችን!! ብርሃናችን ናቸው ልጆቻችን!! ማዕተቤን አልበጥስም፤ ወደ ሌላ አንለወጥም፤ አንበገርም አሉ፤ ይኼ ነው ወይ የሚያስለቅሰው? የሚለቀስበትን ነገር እንወቅ እንጂ!
ውድ ወገኖቼ፤ ስለዚኽ ልጆቻችንን በሰማዕትነታቸው፣ በጀግንነታቸው ልናከብራቸው፣ ልንማርባቸው፣ ምሳሌአቸውን ልንወስድ፣ ልናወድሳቸው ይገባል፡፡ ስለዚኽ ይኼ የመረጋጋት፣ የሰላም‹ የፍቅር ቦታ ነው፡፡ ልጆቻችን የአገር ፍቅር፣ የአገር ሰላም፣ የአገር አንድነት አስተምረውናል፡፡ በልጆቻችን ተምረናል፤ ጠግበናል፤ ረክተናል፤ ኮርተናል፡፡
የልጆቻችንን ነፍስ በገነት በመንግሥተ ሰማያት ያሳርፍልን፤ ይማርልን፤ ወላጆቻቸውን ይጠብቅልን፤ ከክፉ ነገር ይሰውረን፤ መልካሙን ነገር ያምጣልን፤ ልጆቻችንና ወገኖቻችንን በሰላም ወደ ቤታቸው ይመልስልን፡፡ ኹላችንም ተጽናንተን የሚያኮራ ሥራ እንድንሠራ ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡ ነፍሰ ገብሩ ኃይለ ኢየሱስ፣ ኃይለ ሚካኤል ሀገረ ሕይወትን መንግሥተ ሰማያትን ያውርስልን፡፡
* * *
‹‹ወገኖቻችን ሰማዕታት፣ ታሪክ አትርፈው ስለሔዱ ለዘላለም ስማቸውና ሥራቸው ሲወሳ ይኖራል››
(ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፤ የወላይታ ኮንታ እና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ)

አኹንም እነዚኽ ወንድሞቻችን፣ ወገኖቻችን ሰማዕታት የታሪክ ባለቤቶች ስለኾኑ፣ ታሪክ አትርፈው ስለሔዱ ከእነርሱ በፊት እንደነበሩት ኹሉ ለዘላለም ስማቸው፣ ሥራቸው ሲወሳ ይኖራል፡፡ ሐዘን ኹልጊዜ ሲያነሡት ልብ ይሠቀጥጣል፡፡ ይኼን እያነሡ መናገር በጣም ይከብዳል፡፡ ጭንቅላት ሊሸከመው አይችልም፡፡ እናም እዚኽ ያሉትን እያጽናናችኹ፣ እዚያ የቀሩት ደግሞ በሰላም እንዲወጡ ምሕላ እያደረግን ልንጸልይ ይገባል፡፡ እኛ እዚኽ ፀሐይ እየሞቅን፣ እየተነጋገርን እናዝለን፤ እዚያ እነርሱ ከወጡበት ሰውነታቸው አልቆ ነፍሳቸው የምትጨነቅ አለችና በሰላም እንዲያወጣቸው ላለፉት ብቻ ሳይኾን ለቀሩትም ጸሎት እያደረጋችኹ በዚኽ እንድትጽናኑ ነው አደራ የምንለው፡፡
ወላጆች ወለዱ እንጂ የኹላችን ልጆች ናቸው፤ ሐዘኑ የኢትዮጵያ ነው፤ እግዚአብሔር ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጽናቱን ይስጥልን፡፡ እዚያ የቀሩትንም በሰላም ያውጣልን፡፡

ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ