ሚያዝያ 15 ቀን 2007 ዓ.ም.
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሊቢያ ለተሰዉት ክርስቲያኖች ቀኖናው በሚፈቅደው መሠረት በቅርቡ የሰማእትነትን ክብር እንደምትሰጥ አሰታወቀች
ቅዱስ ጳትርያርኩ፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የግብጽ አምባሰደር፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የሰማእታቱ ቤተሰቦችና ምእመናን በተገኙበት ጸሎተ ፍትሐቱ ተከናውኗል፡፡
በጸሎተ ፍትሐቱ ላይ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የሰንበት ትምህርት ቤቶች መዘምራን ሰማእታቱን አስመልከቶ ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበዋል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ ያስተላለፉትን መልእክት ቀጥሎ እናቀርባለን፡፡ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን!
ዘሰ አምነኒ በቅድመ ሰብእ አነኒ አአምኖ በቅድመ አቡነ ዘበሰማያት
በሰው ፊት ያመነኝን ሰው እኔም በሰማያዊ አባቴ ፊት አምነዋለሁ
የቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል 10*32
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
የተከበራችሁ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አባላት ወጣቶች ምእመናንና ምእመናት
ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ መሥዋዕትነት አብሯት የኖረ ታሪክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም በልዩ ልዩ ዘመናት ልጆቿ በግፍ ተገድለው ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፡፡
በስድስተኛው ክፍለ ዘመን በናግራን፣ በዘጠነኛው ክፍለ ዘመን በዮዲት ጉዲት፣ በዐሥራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን በግራኝ አሕመድ፣ በዐሥራ ዘጠነኛውና ሃያኛው ክፍለ ዘመን በውጭ ወራሪ ኃይሎች በርካታ የሰማዕትነት ታሪኮች አልፈዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሁሉም ዘመን የተነሡባት አሳዳዶችና ገዳዮች ከነታሪካቸው ሲጠሩ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአምላኳ ጥበቃና በልጆቿ ጽናት ሰማዕታቷን አክብራ ለሰው ልጅ መንፈሳዊ ሀብትን እያደለች አሁንም አለች ወደፊትም ትኖራለች፡፡ ዛሬ እነዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች በጠባቡ በር ተጉዘው በደማቸው ማሕተም ወደ መንግሥተ ሰማያት የገቡ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የክርስትና እምነት ጽኑ ምስክሮች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስም ለእነዚህ ልጆቻችን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በሚፈቅደው መሠረት የሚገባውን የሰማዕትነት ቀኖና ሥነ ሥርዓት በቅርቡ በማከናወን ለመላው ዓለም ያሳውቃል፡፡ ስለዚህ የክርስቶስ ቤተሰቦች የሆናችሁ ክርስቲያኖች ሁሉ በዚህ አረመኔያዊ ወንጀል ሳትደናገጡ አሸባሪነትን በአንድነት ሆናችሁ በማውገዝና በመከላከል የተጀመረውን ተቃውሞ ትርጉም ባለውና አፋጣኝ በሆነ መንገድ ልንፈጽመው እንደሚገባ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን
አሸባሪነት ሃይማናት የለውም፣ በዕውቀትና በበሳል አእምሮ የሚከናወን ተግባርም አይደለም፣ የድርጊቱ ፈጻሚዎችም የተረጋጋ ሥነ ልቦና ያላቸው ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ብሶት ያለባቸው ሰዎች እንደሚያደርጉት ያለ የነፃነት ትግልም አይደለም፡፡
ነገር ግን በፍጹም ራስ ወዳድነትና ጭካኔ ላይ የተመሠረተ አስነዋሪ ወንጀል ነው፡፡ የአይ ኤስ አሸባሪዎች የፈጸሙት ወንጀል የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ትውልድ አስተሳሰብን የማይወክልና የሰውን ልጅ ተፈጥሮአዊ ባህርይ የጣሰ ተግባር ነው፡፡ ይህንን አስነዋሪ ግፍ ክርስቲያኖችና የሌላ እምነት ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ ሰው የሆነ ፍጡር ሁሉ ሊያወግዘውና ሊጸየፈው የሚገባ ተግባር ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የፈጸሙት ተግባር በራሳቸው ላይ ቢፈጸምና በጤናማ ሥነ ልቦና ቢያዩት ኖሮ በወጣቶቻችን ላይ በፈጸሙት ተግባር ልክ እንኳ ቢከፈላቸው እንደማይበቃ አድርገው በራሳቸው ላይ ይፈርዱ ነበር፡፡ ዛሬ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ለሚመስሉት ወገኖቹ ሕይወት፣ ምቾትና ሰላም ደፋ ቀና በሚልበት ዓለም ከሰው የተፈጠሩ የማይመስሉ አረመኔዎች ክቡር የሆነ የሰውን ልጅ ነፍስ ኢሰብኣዊ በሆነ መንገድ ሲቀጥፉ መታየት ምን የሚሉት እምነት ነው? ይህን አስነዋሪና ከሰው ተራ የሚያወጣቸውን ተግባርስ የወጣቶቹ ወላጆች ሳይቀሩ ዓለም ሁሉ በሚመለከተው ሚዲያ ማሳየት ምን የሚሉት ጭካኔ ነው? የሰውን ልጅ የቀድሞ ታሪክ አጥፈቶ አዲስ የግፍና የኢሰብኣዊነት ታሪክ ለመሥራት መጣጣርስ ምን የሚሉት አስተሳሰብ ነው? ስለዚህ አይ ኤስን ጨምሮ በሰብአዊ ፍጡር ሉዓላዊ ክብር ላይ የተቃጣ የአሸባሪነት ወንጀል ያልምንም ቅድመ ሁኔታ ከምድራችን ሊወገድ የሚገባው እኩይ ግብር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ራሳቸውን አይ ኤስ ብለው የሚጠሩት አሸባሪዎች ከዕውቀትና ከሃይማናት የወጡ፣ የልማትና የሰው ልጅ ሰላማዊ ሕይወት ሥጋቶች የሆኑ ቡድኖች በመሆናቸው ዓለም በአንድነት ተባብሮ ሊያቆማቸው ይገባል፣ ምናልባት ቡድኑን በገንዘብና በልዩ ልዩ መንገድ ድጋፍ የሚያደርጉ ግለሰቦችና ተቋማት ካሉም የጥፋት ተባባሪ ከመሆን ሊታቀቡ ይገባል፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ለፈጸሙት ወንጀል በነፍሳቸውና በኅሊናቸው ከሚመጣባቸው ዘለዓለማዊ ፍርድ ይድኑ ዘንድ ንሥሓ እንዲገቡ ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡ የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት
ቀደም ሲል እንደገለጽነው በመንፈሳዊ ሕይወት ከምናገኘው ዋጋ ሁሉ የሰማዕትነት ዋጋ ተወዳዳሪ የለውም፣
በፍትሕ መንፈሳዊ ወሰማእታትሰ እሉ እሙንቱ ዘይቤ ክርስቶስ በእንቲሆሙ ዘሰ አምነኒ በቅድመ ሰብእ አነኒ አእምኖ በቅድመ አቡነ ዘበሰማያት፣ ወለእመተሳተፍክምዎሙ በጊዜ ኅዘናቲሆሙ ይከውን ለክሙ ስምዕ በእንተ ጻሕቀ ኅሊናክሙ፡፡ ሰማዕታት ማለት እኔን በሰው ፊት ያመነኝን ሰው እኔም በሰማያዊ አባቴ ፊት አምነዋለሁ ብሎ ክርስቶስ ስለእነርሱ የተናገረላቸው ናቸው፡፡ እነዚህን በመከራቸው ጊዜ ብትመስሏቸው ስለ ቁርጥ ሓሳባችሁ ሰማዕትነት ይቆጠርላችኋል፡፡ የተባለላቸው ናቸው፤ ሰማዕታት ለሃይማኖታቸው ታማኞች ለመድኅኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ደማቅ ምስክሮች ናቸው፤ ሰማዕታት በቅዱሳት መጻሕፍት ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቁንስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ፤(ማቴ 10*28) የሚለውን ቃል ተቀብለው ምርጫቸው እግዚአብሔር መሆኑን በአደባባይ ያሳዩ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ሰማዕታት የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው በተባለው መሠረት የመንግሥተ ሰማያትን የክብር አክሊል በጥበብ ጀምረው በደማቸው ምስክርነት የተቀዳጁ ናቸው፡፡ ክብራቸውም አቡቀለምሲስ ዮሐንስ በራእዩ ምዕ 20 ቁጥር 4 ዙፋኖችንም አየሁ፤ በእርሱ ላይ ለተቀመጡትም ዳኝነት ተሰጣቸው፣ ስለኢየሱስም ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቆረጡባቸውን ሰዎችአየሁ ብሎ እንደተናገረው በእግዚአብሔር መንግሥት የማያልፍ አክሊልና የፍርድ ዙፋን የተዘጋጀላቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ የእነዚህ ወጣቶች ልጆቻችን ቤተሰቦች የሰማዕታት ቤተሰቦች በመሆናችሁ ልትጽናኑ ይገባል፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም በደሙ የመሠረታት ወልደ እግዚአብሔር የልጆቿን ነፍስ በክብር እንዲቀበል ትጸልያለች፡፡
ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን የልጆቻችንን ነፍስ በክብር ያሳርፍልን፣ ለመላው ዓለም ሰላምና መረጋጋትን ለቤተ ክርስቲያንና ለሰማዕታቱ ቤተሰቦች መጽናናትና ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን የልጆቻችንን ነፍስ በክብር ያሳርፍልን፣ ለመላው ዓለም ሰላምንና መረጋጋትን ለቤተ ክርስቲያንና ለሰማዕታቱ ቤተሰቦች መጽናናትና ብርታትን ይስጥልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ሚያዝያ 15 ቀን 2007 ዓ.ም አዲስ አበባ - ኢትዮጵያ |
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት የሚቀርቡ መንፈሳዊ ትምህርቶች ፤መረጃዎች እና የመሳሰሉት የሚስተናገዱበት ገጽ ነው
ሐሙስ 23 ኤፕሪል 2015
ለሰማእታቱ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎተ ፍትሐት ተካሔደ፡፡
ደንበኛ ይሁኑ ለ፡
አስተያየቶች ለጥፍ (Atom)
በአውሮጳ የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ የተውጣጡ ካህናት፡” የ...
-
June 1, 2015 ከሐራ ዘተዋሕዶ በሐዋርያዊት፣ ጥንታዊት እና ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያናችን ህልውና እና ዕድገት ፊት ከተጋረጡትና አፋጣኝ እልባት ከ...
-
‹‹…ወንድማችንን እናውቃቸዋለን፤ በእውነቱ ለፌ ወለፌ የማይሉ ደረቅ ሊቅ ናቸው፤ በሃይማኖቱ ዘርፍ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንዲቱም ነጥብ እንዳትዛባ...
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ