2014 ኤፕሪል 1, ማክሰኞ

የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሰንበት ገብርሔር

Thursday, March 27, 20140 comments

የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሰንበት ገብር ሔር (ቸር አገልጋይ) የተሰኘው ሲሆን ይህንን ስያሜ ያገኘበትም ምክንያት ከዋዜማው ጀምሮ የሚዘመረው ጾመ ድጓ ‹‹ገብር ሔር ወገብር ምእመን ገብር ዘአስመሮ ለእግዚኡ፤ ጌታውን ያስደሰተው አገልጋይ ታማኝና ቸር አገልጋይ ነው፡፡  ገብርሔር በጎ አገልጋይ ማለት ሲሆን የስያሜውን መነሻ የምናገኘው በዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሚነበበው የወንጌል ክፍል ማቴ.25-14-30 ነው፡፡


ምስባክ     መዝ. 39÷8 
"ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ፡፡ 
ወሕግከኒ በማዕከለ ከርሥየ፡፡
 ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበር ዐቢይ፡፡"

ትርጉም፦ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ለማድረግ መከርሁ፥
 ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው።
 በታላቅ ጉባኤ ጽድቅህን አወራሁ።

ወንጌል
ማቴ. 25÷14-30 “መንገድ እንደሚሄድ÷ አገልጋዮቹንም ጠርቶ ሊያተርፉበት ገንዘቡን እንደ ሰጣቸው ሰው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው ለአንዱ አምስት÷ ለአንዱ ሁለት÷ ለአንዱም አንድ ሰጠና ወዲያውኑ ሄደ፡፡ ያ አምስት መክሊት የተቀበለውም ሄደ፤ ነግዶም ሌላ አምስት መክሊት አተረፈ፡፡ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ፡፡ አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታዉን ወርቅ ቀበረ፡፡ ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ ተመልሶ ተቈጣጠራቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና፡- አቤቱ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ አምስት አተረፍሁ ብሎ አምስት መክሊት አስረከበ፡፡ ጌታውም፡- መልካም÷ አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡ ሁለት መክሊት የተቀበለውም መጥቶ፡- አቤቱ÷ ሁለት መክሊትን ሰጥተኸኝ አልነበረምን? እነሆ ሌላ ሁለት መክሊትን አተረፈሁ አለ፡፡ ጌታውም፡- መልካም÷ አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ የታመንህ ስለ ሆንህ በብዙ አሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡ አንድ መክሊት የተቀበለውም መጣና እንዲህ አለ፡- አቤቱ÷ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ÷ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንህ አውቃለሁ፤ ስለ ፈራሁም ሄድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ፤ እንግዲህ እነሆ÷ መክሊትህ፡፡ ጌታውም መልሶ አለው፡- አንተ ክፉና ሰነፍ አገልጋይ÷ እኔ ካልዘራሁበት የማጭድ÷ ካልበተንሁበትም የምሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንሁ ታውቃለህን? ገንዘቤን ለለዋጮች መስጠት በተገባህ ነበር፤ እኔም ራሴ መጥቼ ገንዘቤን ከትርፉ ጋር በወሰድሁ ነበር፡፡
 ከዚያ የቆሙትንም እንዲህ አላቸው፤ ይህን መክሊት ከእርሱ ተቀብላችሁ ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት፡፡ ላለው ሁሉ ይሰጡታልና፤ ይጨምሩለታልም፤ ለሌለው ግን ያንኑ ያለውን ይወስዱበታል፡፡ ክፉውን አገልጋይ ግን÷ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወደ አለ ጨለማ አውጡት፡፡


ዲያቆን (ምንባብ) 
2ኛ ጢሞ.2÷1-15 ልጄ ሆይ÷ አንተም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ በርታ፡፡ በብዙ ምስክሮች ፊት ከእኔ የሰማኸውን ትምህርት ለሌሎች ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች እርሱን አስተምራቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚያገለግል በጎ አርበኛ ሆነህ መከራ ተቀበል፡፡ ወደ ሰልፍ የሚሄድ÷ አለቃውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ነው እንጂ የዚህን ዓለም ኑሮ አያስብምና፡፡ የሚታገልም ቢሆን እንደ ሕጉ ካልታገለ አክሊልን አያገኝም፡፡ የሚደክም አራሽም አስቀድሞ ፍሬውን ሊያገኝ ግድ ነው፡፡ ያልሁህን አስተውል፤ እግዚአብሔርም በሁሉ ነገር ጥበብን ይስጥህ፡፡
 በወንጌል እንደምሰብከው÷ ከሙታን ተለይቶ የተነሣውን ከዳዊት ዘር የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስበው፡፡ ስለ እርሱም እንደ ወንጀለኛ አስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም፡፡ ስለዚህ እነርሱ ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ሕይወትና የዘለዓለም ክብር በሰማያት ያገኙ ዘንድ÷ ስለ ተመረጡት ሰዎች በሁሉ ነገር እታገሣለሁ፡፡ ነገሩ እውነት ነው፤ ከእርሱ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን፡፡ ብንታገሥም ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን፤ ብንክደው ግን እርሱም ይክደናል፡፡ ባናምነውም እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን መካድ አይቻለውምና፡፡
እንግዲህ ይህን አሳስባቸው፤ በቃልም እንዳይጣሉ÷ በእግዚአብሔር ፊት ምከራቸው፤ ይህ ምንም የማይጠቅም÷ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነውና፡፡የእግዚአብሔርን ቃል በእውነት አቃንቶ ሲያስተምር እንደማያፍር ሰራተኛ ሆነህ ፣ራስህን የተመረጠ አድርገህ  ለእግዚአብሔር ታቀርብ ዘንድ ትጋ።  

ንፍቅ ዲያቆን (ምንባብ)

 1ኛ ጴጥ.5÷1-11 እንግዲህ እኔ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ÷ የክርስቶስም መከራ ምስክር÷ ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግለዎችን እማልዳቸዋለሁ፡፡ በእናንተ ዘንድ ያሉትን የእግዚአብሔርን መንጋዎች ጠብቁ፤ ስትጠብቁአቸውም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ አይሁን፤ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘትም አይሁን፡፡ ለመንጋዉ ምሳሌ ሁኑ እንጂ ሕዝቡን በኀይል አትግዙ፡፡ የእረኞችም አለቃ በተገለጠ ጊዜ የማይጠፋውን የክብር አክሊል ትቀበላላችሁ፡፡ እንዲሁ እናንተ ጐልማሶች ሆይ÷ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም ትሕትናን ልበሷት፤ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ያዋርዳልና፤ ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉትን ግን ያከብራቸዋል፡፡
እንግዲህ በጐበኛችሁ ጊዜ ከፍ ከፍ ያደርጋችሁ ዘንድ ከጸናችው ከእግዚአብሔር ክንድ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፡፡ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት፡፡ እንግዲህ ዐዋቂዎች ሁኑ፤ ትጉም፤ ጠላታችሁ ጋኔን የሚውጠውን ፈልጎ÷ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና፡፡ እርሱንም በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት፤ እንዲህም ያለ መከራ በዓለም በአሉ ወንድሞቻችሁ ሁሉ እንደሚፈጸም ዕወቁ፤ ፍቅርንም አጽንታችሁ ያዙአት፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዘለዓለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ፍጹማን ያደርጋችኋል፤ ያጸናችኋል፤ ልባሞችም ያደርጋችኋል፡፡ለእርሱ ክብርና ኅይል እስከ ዘለአለም ይሁን፤አሜን።
ንፍቅ ቄስ (ምንባብ)
የሐዋ.1÷6-8 እነርሱም ተሰብስበው ሳሉ÷ "ጌታ ሆይ÷ በዚህ ወራት ለእስራኤል ልጆች መንግሥትን ትመልሳለህን?” ብለው ጠየቁት፡፡ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ቀኑንና ዘመኑን ልታውቁ አልተፈቀደላችሁም፡፡ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኅይልን ትቀበላላችሁ፤በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉ፣በሰማሪያና እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ምስክሮቸ ትሆኑኛላችሁ።"

ቅዳሴ
ዘባስልዮስ

የብፁዕ አቡነ ቶማስ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ


አትም ኢሜይል
 መጋቢት 17 ቀን 2006 ዓ.ም.

abuna tomas
የቀድሞ ስማቸው አባ መዘምር ተገኝ የአሁኑ ብፁዕ አቡነ ቶማስ ጥር 14 ቀን 1932 ዓ.ም ጎጃም ደጋ ዳሞት ዝቋላ አርባዕቱ እንስሳ ተወለዱ፡፡ መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርትን በሚገባ ከተማሩ በኋላ ጸዋትወ ዜማን ከመሪጌታ አንዱዓለምና መሪጌታ ካሣ ይልማ ፣ ቅኔ ከመሪጌታ ፈንቴ /ዋሸራ/፣ መጻሕፍተ ሐዲሳትን ከመሪጌታ ብርሃኑ ወልደ ሥላሴ ፣ መጻሕፍተ ሊቃውንትን ከመሪጌታ ቢረሳ ደስታ ተምረዋል፡፡ በዘመናዊ ትምህርትም እስከ 6ኛ ክፍል ፣ የእንግሊዝኛን ቋንቋ በግላቸው የተማሩና የመኪና ጽሕፈት /type writing/ የሚያውቁ ነበሩ፡፡ ብፁዕ አቡነ ቶማስ ዲቁና ከአቡነ ማርቆስ፣ ቅስና ከአቡነ ባልዮስ፣ ቁምስና ከብፁዕ አቡነ ተክለሃይማኖት ተቀብለዋል፡፡

abuna tomas 2በደብረ ሊባኖስ ገዳም መጻሕፍተ ሊቃውንትን ረዘም ላለ ጊዜ አስተምረዋል፡፡ በገዳሙ የሠራተኞች ቅርንጫፍ ማኅበር ሲቋቋምም የመጀመሪያው ሊቀ መንበር በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው በጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል በአስተዳዳሪነትና መጻሕፍተ ሓዲሳትንና ሊቃውንትን በማስተማር የሚጠበቅባቸውን ተልእኮ ተወጥተዋል፡፡ ጥር 14 ቀን 1972 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ አንብሮተ ዕድ ተሹመው ሰፊ አገልግሎት ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ በመመለስ የታእካ ነገሥት በዓታ ለማርያምና መንበረ መንግሥት ግቢ ገብርኤል ገዳም የበላይ ጠባቂ ሆነው አገልግለዋል፡፡

ብፁዕነታቸው ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ የምእራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተው፤ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው መጋቢት 16 ቀን 2006 ዓ.ም መንበረ ጵጵስናቸው በሚገኝበት በፍኖተ ሠላም ከተማ ዐርፈዋል፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸውም በዚያው በፍኖተ ሰላም እንደሚፈጸም ይጠበቃል፡፡

የአባታችንን ነፍስ በአብርሃምና በይስሐቅ እቅፍ ያኑረልን፡፡

2014 ማርች 27, ሐሙስ

የተዋሕዶው መዶሻ ጳጳስ አባ ቶማስ


 

ብፁዕ አቡነ ቶማስየምዕራብ ጎጃም(ፍኖተ ሰላም) ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
Abayneh Kassie's photo.
ከዲ/ን አባይነህ ካሴ
                                                                                            የተዋሕዶው መዶሻ ጳጳስ አባ ቶማስ
ረዘም ላሉ ጊዜያት በቅርበት ከማውቃቸው ብጹዓን አበው መካከል ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቶማስ አንዱ ናቸው፡፡ ዜና ዕረፍታቸውን ስሰማ እጅግ አዘንሁ፡፡
- የተመሰከረላቸው ሊቅ
- ፊት ለፊት ዞሮ / ማማት የሌለባቸው/
- ጥቡዕ / በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሰተውን ርካሽ አስተዳደር በድፍረት የተቃወሙ እና የታገሉ/
- ቀናኢ
- ተሐድሶን ከቤተ ክርስቲያን ነቅሎ ለመጣል ያለ ማሰለስ የተጋደሉ ብርቱ
- እምነታቸውን በብርዕ ያደመቁ
- አባቶቻቸውን መስለው የኖሩ …ታላቅ አባት
አንድ ሊቅ ሲሞት አንድ ታላቅ ቤተ መጻሕፍት እንደተቃጠለ ይቆጠራል እንዲሉ እንዲህ እንዲህ እያሉ እየተሰናበቱን ሄዱ፡፡ እንኪያስ ምን ይበጀን ይሆን

በረከታቸው ይድረሰን እንጂ ሌላ ምን ይባላል፡፡
                 


የተዋሕዶው መዶሻ ጳጳስ አባ ቶማየተዋሕዶው መዶሻ ጳጳስ አባ ቶማስ
ረዘም ላሉ ጊዜያት በቅርበት ከማውቃቸው ብጹዓን አበው መካከል ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቶማስ አንዱ
የተዋሕዶው መዶሻ ጳጳስ አባ ቶማስ
ረዘም ላሉ ጊዜያት በቅርበት ከማውቃቸው ብጹዓን አበው መካከል ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቶማስ አንዱ ናቸው፡፡ ዜና ዕረፍታቸውን ስሰማ እጅግ አዘንሁ፡፡
- የተመሰከረላቸው ሊቅ
- ፊት ለፊት ዞሮ / ማማት የሌለባቸው/
- ጥቡዕ / በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሰተውን ርካሽ አስተዳደር በድፍረት የተቃወሙ እና የታገሉ/
- ቀናኢ
- ተሐድሶን ከቤተ ክርስቲያን ነቅሎ ለመጣል ያለ ማሰለስ የተጋደሉ ብርቱ
- እምነታቸውን በብርዕ ያደመቁ
- አባቶቻቸውን መስለው የኖሩ …ታላቅ አባት
አንድ ሊቅ ሲሞት አንድ ታላቅ ቤተ መጻሕፍት እንደተቃጠለ ይቆጠራል እንዲሉ እንዲህ እንዲህ እያሉ እየተሰናበቱን ሄዱ፡፡ እንኪያስ ምን ይበጀን ይሆን

በረከታቸው ይድረሰን እንጂ ሌላ ምን ይባላል፡፡
ናቸው፡፡ ዜና ዕረፍታቸውን ስሰማ እጅግ አዘንሁ፡፡
- የተመሰከረላቸው ሊቅ
- ፊት ለፊት ዞሮ / ማማት የሌለባቸው/
- ጥቡዕ / በቤተ ክርስቲያን
 

2014 ማርች 26, ረቡዕ

ሰበር ዜና – የምዕራብ ጎጃም ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቶማስ ዐረፉ


ብፁዕ አቡነ ቶማስ፤ የምዕራብ ጎጃም(ፍኖተ ሰላም) ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ብፁዕ አቡነ ቶማስ የምዕራብ ጎጃም – ፍኖተ ሰላም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
የምዕራብ ጎጃም – ፍኖተ ሰላም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቶማስ ትላንት መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ምሽት 2፡00 ገደማ ዐርፈዋል፡፡
ብፁዕነታቸው የስኳር ሕመምተኛ እንደነበሩና እስካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ድረስ በቡሬ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክሊኒክ ሕክምናቸውን ሲከታተሉ እንደቆዩ የሀገረ ስብከቱ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ለከፍተኛ ሕክምና ወደ አዲስ አበባ መጥተው በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል የደም ማጣራት(ዲያሊስስ) ሲደረግላቸው የሰነበቱ ቢኾንም ጤናቸው መሻሻል ባለማሳየቱ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ከሆስፒታሉ በአምቡላንስ ወጥተው በኦክስጂን እየተረዱ ወደ ሀ/ስብከታቸው ከተመለሱ በኋላ ትላንት ምሽት 2፡00 ላይ ማረፋቸው ታውቋል፡፡
በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ ሐምሌ ፲፯ ቀን ፲፱፻፸፭ ዓ.ም. ከተሾሙት ኤጲስ ቆጶሳት አንዱ የነበሩት ብፁዕነታቸው አኹን ካረፉበት ከምዕራብ ጎጃም – ፍኖተ ሰላም ሀ/ስብከት አስቀድሞ በሊቀ ጵጵስና ከመሯቸው አህጉረ ስብከት መካከል የድሬዳዋ እና የሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ አህጉረ ስብከት ይገኙበታል፡፡
በፊት ስማቸው መልአከ ሣህል መዘምር ተገኝ የሚባሉትና በመጻሕፍት ትርጓሜና በቅዳሴ መምህርነታቸው የሚታወቁት ብፁዕ አቡነ ቶማስ፣ የቅድስት ሥላሴ እና የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጆችን በዲንነት፣ የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያምንና የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳማትን በበላይ ሓላፊነት አስተዳድረዋል፡፡
ትምህርተ ሃይማኖትን የሚከበውን ቃለ ስብከታቸውንም ‹‹ፍኖተ እግዚአብሔር›› በሚል ርእስ በመጽሐፍ አሳትመዋል፤ በሀ/ስብከታቸውም በቅ/ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት በተለይም የመጽሐፍ ትርጓሜ ቤተ ጉባኤ ሊቃውንትን አግኝቶ ደቀ መዛሙርት አብዝቶ እንዲጠናከርና እንዲስፋፋ በብዙ ደክመዋል፡፡
የብፁዕነታቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ነገ፣ መጋቢት ፲፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. በዚያው በፍኖተ ሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከቀኑ በ9፡00 ሰዓት እንደሚከናወን ተገልጧል፡፡
አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር የብፁዕ አባታችንን ነፍስ ከማኅበረ ቅዱሳን ይደምርልን፡፡
 

 

 

ብፁዕ አቡነ ቶማስየምዕራብ ጎጃም(ፍኖተ ሰላም) ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ኦ አባ ንበር በማዕከሌነ
በወርኃ መጋቢት በአዝመራው ወቅት ተጠራ
ለዘመናት ወንጌል ዘርቶ የብዙኃንን ልብ ያበራ
እውነትም ብፁዕ ቶማስ ትጉህ የፍቅር አርበኛ
የመተሳስብ የሰላም የአንድነት አባት ዳኛ
የቀለም ራስ መምህር የመጻሕፍት ቌት ጠንቃቂ
ጎባጣውን የሚያቀና የተጣመመውን ሐራቂ
እንደሰው መጠን ቢፈጠር አዳማዊ ቢኾን ፍጥረቱ
ፍጹም አስደንጋጭ ኾነብን አራደን የቶማስ ሞቱ
ዲያቆን ዘፍጽምና ካህን መናኝ መነኩሴ
መምህር ወጳጳስ ኀሩይ በኀበ ሥላሴ
የቅዳሴው አበጋዝ መራሒ ወንጌል አንደበቱ
እንደምን ድካም ያዛቸው እንደምንስ ተረቱ
የተዋሕዶን ክብር ዝና በዓለም መደረክ ያገዘፈ
በመክሊቱ የሠራበት እልፍ አእላፋትን ያተረፈ
ንዋየ ኀሩይ ቶማስ የታላቅነት ማሳያ
ብርሃን ለምግባር ሠናይ የመልካምነት ገበያ
በመንፈሳዊ ጥበብ የጠለቀ በያሬዳዊ ዜማ የናኝ
እምነትና ፍልስፍናን በዕውቀት ቀንበር ያቆራኘ
ኦ አባ ትጉህ ለጸሎት ኃያል ጽኑ ለተጋድሎ
ያስመሰከረ ማንነቱን በጉባኤ ቤት አውድማ ውሎ
እጨጌ ለመንበረ ፍኖተ ሰላም አቡነ
ሊቀ ጳጳስ ዘጎጃም በታቦተ ጽዮን እምነ
ሥዩመ እግዚአብሔር ወሰብ የፍኖተ ሰላም መሪ
እንደ ፀሐይ ደማቅ እንደ ኮኮብም አብሪ
መዋቲ ሥጋ የለበሰ ሞት ዕጣው ቢኾንም ቅሉ
የአባት ሞት ግን መሪር ነው የማይታመን ለኹሉ
በወርኃ ፍጹም ሱባኤ መጋቢት ሐተታ
እምድኽ ፈለሰ ቶማስ ወደ ላይኛው ቦታ
መከራው ይበልጥ በረታ የሐዘን እንባ ዘነበ
አቡነ መምህር ቶማስ ውስተ መቃብር ሰከበ
ጆሯችንን ጭው ያደረገ ፍጹም ለማመን የከበደ
አባ ሞትኽን ሰማን ልባችን በሐዘን ራደ
እግዚአብሔር ያጽናሽ ቤተ ክርስቲያን
ቅኔ፣ ጾመ ድጓ፣ መዋስዕት ምዕራፉን
ጠንቅቆ ያወቀ ዝማሬ ድጓውን
የአበውን ትውፊት በደንብ የቀሰመ ልጅሽን ሞት የነጠቀሽ
ሌት እና ቀን ለመምሰል ሳይኾን በመኾን ያቆመሽ
ስምኽ ከመቃብር በላይ ያበራል ጸንቶ እንደፋና
የወንጌል አርበኛው ቶማስ የሔድክ በጽድቅ ጎዳና
የወንጌል ብርሃን ባልበራበት ከአጽናፍ አጽናፍ ዞሮ
ምንኩስና ጵጵስናን በሕይወቱ በእውነት ኖሮ
ነዳያንን በፍቅር ስቦ ምስኪናን በችሮታ
ሰብስቦ ያኖረው ክንድኽ ዛሬስ እንደምን ተረታ
ጸዐዳው የሕይወት መምህር የቀለም ገበሬ
የኹለት ዓለሙን ምሁር ሞት እጁን ያዘው ዛሬ
የአብርሃም እቅፍ ለአንተ የገነት በር ይከፈት
በገድል ትጋት የኖረችው ነፍስም ታግኝ ዕረፍት
ተዋናይ በመንፈስ አባ ንበር በማዕከሌነ
ሳህል ወጸልይ ምሕረት ሀበ ማርያም እምነ
ሊቀ ጳጳሳት ዘሀገረ አባ ኢትዮጵያ
ከአትሮንሱ ላይ ተነሣ ታጠፈ የዕውቀት ገበያ
በትረ ሙሴ ይዞ ሕዝቡን በጥበብ የመራ
ይኽው ወር ተራ ደርሶት እርሱም በመጋቢት ተጠራ
ሕይወታቸው ያለው አይታበልምና ቃሉ
ብፁዕ አቡነ ቶማስ ያክብርህ ከሃሌ ኵሉ፡፡
ከመምህር ሳሙኤል አያልነህ
መታሰቢያነቱ መጋቢት 16 ቀን 2006 ዓ.ም.
በመሞት ለተለዩን ለብፅዕ አቡነ ቶማስ ሊቀ ጳጳስ
About these ads

ደብረ ዘይት- የምጽአት መታሰቢያ የዐቢይ ጾም 5ኛ ሳምንት


የደብረ ዘይት ተራራ የዛሬ ገጽታ 
ደብረ ዘይት ማለት ቃሉ “ደብር” ሲል ተራራ ሲሆን “ዘይት” ሲል የወይራ ዛፍን ያመለከታል። ባጠቃላይ ደብረ ዘይት የወይራ ዛፍ (የዘይት ዛፍ) የበዛበት ተራራ ማለት ነው። ቦታው የሚገኘው በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም ከጎለጎታ (ቀራንዮ) ተራራ በስተምስራቅ በግምት ፪ ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ታላቅ ተራራ ነው። በሁለቱ ተራሮች መካከል ጌቴሴማኒ የሚባለው ለምለም ስፍራ ይኸውም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የመቃብር ስፍራ ይገኛል።
የደብረ ዘይት ተራራ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ የሚያድርበት፣ የሚያስተምርበት፣ ውሎ የሚያርፍበት ሥፍራ ነው። ሉቃ ፳፩፥ ፴፯፣ ሉቃ ፳፪፥ ፴፱፣ ዮሐ ፰፥ ፩ ከዚሁ ተራራ ላይ ነው ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያረገው። ኋላም በዳግም ምጽአት እዚሁ ተራራ ላይ ነው ለፍርድ የሚመጣው። /ሐዋ ፩፥፲፫/።
 በደብረ ዘይት ተራራ ወገብ ላይ በሰፊው ተንጣሎ የሚታይ አንድ ነገር አለ፤ ይኸውም የአይሁድ መቃብር ነው። ይህን ስፍራ ለመቃብርነት የመረጡበት ምክንያት ወደፊት መሢሑ መጥቶ እስራኤልን ነፃ አውጥቶ ወደ አባቱ ያርጋልና ኋላ ለፍርድ ሲመጣ በመጀመሪያ የሚፈርድበት ስፍራና ሙታንም የሚነሱበትና የሚሰበሰቡበት ስፍራ ይህ በመሆኑ እኛ መሢሐችንን ለማግኘትና ከሙታንም ለመነሳት የመጀመሪያዎቹ እንሆናለን ብለው በማመናቸው ነው። አይሁድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መሢሕ እርሱ ነው ብለው አያምኑም። መሢሕ ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ የተቀባ ማለት ሲሆን በግሪክ ቋንቋ ደግሞ ክርስቶስ ማለት ነው። እግዚአብሔር ሕዝበ እስራኤልን ለመጠበቅ ከመሃላቸው የሚመርጣቸውን ሰዎች በቅዱሳን ነቢያቱ አማካኝነት በተቀደሰ ዘይት (በቅብዓ ቅዱስ) እየቀባቸው ካህናትንና ነገሥታትን ይሾምላቸው ስለነበር ሕዝቡም እግዚአብሔር ለቀባውና ለመረጠው እየታዘዙ ይኖሩ ነበር። በመሆኑም እስራኤል ወደፊት አንድ ታላቅ መሢሕ እግዚአብሔር እንደሚልክላቸው ባላቸው ተስፋ መሠረት ገና አሁንም ድረስ መሢሐችንን እንጠብቃለን ይላሉ። ይሁንና እግዚአብሔር እስራኤልን ብቻ ሳይሆን ዓለሙን ሁሉ እንዲያድን አንድ ልጁን ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ልኮልን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶልን በእርሱ ቁስል እኛ ተፈውሰናል፣ በእርሱ ሞት እኛ ሕይወትን አግኝተናል። /ኢሳ. ፶፫፥፬-፮/። ከዚህ በኃላ ሌላ መሢሕ ሌላ አዳኝ ፈጽሞ የለም። አይሁድ በዚህ በትልቁ ነገር ላይ ወደኋላ ቀርተው ተበድለዋል።
እንግዲህ በቤተክርስቲያናችን ሕግና ሥርዓት መሠረት የዓብይ ጾም እኩሌታ ደብረ ዘይት በመባል ተሰይሟል፤ ይኽውም በዚሁ ሰንበት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆኖ ለቅዱሳን ሐዋርያቱ ስለዓለም ጥፋትና ስለዳግም ምጽአቱ ምልክቱን ነግሯቸዋል። ይኸውም /ማቴ. ፳፬፥ ፫-ፍ/ እንደተገለጸው፤
• ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ
• ጦርነትን የጦርነትንም ወሬ ትሰማላችሁ
• ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣሉ
• በየሀገሩም ረኃብ፣ ቸነፈርም፣ የምድር መናወጥም በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል
• በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ ይገድሏችሁማል፤ ስለ ስሜም በሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ
• በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በእርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፣ እርስ በእርሳቸውም ይጣላሉ
• ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ
• ከዐመፅም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች
• የጥፋት ርኩሰት በተቀደሰችው ሥፍራ ቆሞ ታያላችሁ
• በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል ካለ በኋላ እስከመጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል በማለት ገልጾላቸዋል።
ክብር ምስጋና ይግባውና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ለልጆቹ ካለው ፍቅር የተነሳ ሁልጊዜም የምንድንበትን መንገድ ሳያሳውቀን ቀርቶ አያውቅም። አሁንም ከላይ የተዘረዘሩትን የመሰናከያ አይነቶችና የመከራ ብዛቶችን ብቻ ጠቅሶ አላለፈም። ይልቁንም ጭንቅ ሲመጣ ማቅለያውን፣ መከራ ሲገጥም መውጫውን፣ ፈተና ሲከብደን ማለፊያውን ጭምር አሳይቶናል፣ ነግሮናል። ይኸውም፦
«ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ» /ማቴ. ፳፬፥፬/
አዎ በየጊዜው ፍልስፍና የተጠናወታቸው፣ ኃይማኖት መኖሩን የሚያውቁ እንጂ ዕምነት የሌላቸው፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን «እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን የሚመስላቸው»። /፩ ጢሞ. ፮፥፭/ ሐሰተኛ መምህራንና ሐሰተኛ ነቢያቶች አሉ። አዎ ጥሩ ምዕመን መስሎ መታየትን፣ ጥሩ ዘማሪ፣ ጥሩ ሰባኪ፣ ጥሩ ካህን፣ ጥሩ አባት፣ መልካም መሪ፣ መስሎ መታየትን እንጂ ፈጽሞ ያልሆኑም አሉ።
ቅዱስ ጳውሎስ /በ፩ ቆሮ. ፯፥፳፫/ ላይ «የሰው ባሪያዎች አትሁኑ» እያለ ብዙዎች ግን የጥልና መለያየት ባሪያዎች፣ የክፋትና የኃጢአት እስረኞች ሆነው በተቀደሰው ሥፍራ በመቆም እነሆ የጥፋት ርኩሰቶችን፣ ቀኖና አፍራሾችን፣ ሥርዓት ገርሳሾችን፣ የጥፋት ኃይሎችን እያየናቸውና እየሰማናቸው እንገኛለንና እንግዲህ አንባቢ ያስተውል። ከእነዚህ በመራቅ እንዳይስት ይጠንቀቅ። ጌታችንም «ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ» ያለን ለዚህ ሲሆን እንዴት መጠንቀቅም እንዳለብን ቅዱስ ጳውሎስ በ፪ኛ ተሰ. ፫፥፮ ላይ «ወንድሞች ሆይ ከእኛ እንደተቀበለው ወግ ሳይሆን ያለሥርዓት ከሚሄድ ወንድም ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን» በማለት ግዝትም ትምህርትም አስተላልፎልናል። ይሁንና ሥርዓትም የሚያፈርሱ ግዝትም የሚጥሱ እያየን ነው። እንግዲህ ሥርዓት ሲል በጽሁፍ ቅድስት ቤተክርስቲያን የሰጠችንን፣ ወግ ሲል በትውፊት እየወረደ ዛሬ ድረስ የመጣልንን ሲሆን ሌላው ቀርቶ መልካሙ ኢትዮጵያዊ ባሕላችንንና ይሉኝታችንን ሁሉ ጠብቀን ብንይዘው መለያችን መሆኑን መዘንጋት የለብንም።
ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ አትደንግጡ /ማቴ. ፳፬፥፮/
በአሁኑ ወቅት በዓለማችን የተለያየ ክፍል እየተሰማና እየታየ ያለው የሰላም መጥፋት፣ የፍቅር መቀዝቀዝና የጦርነት ወሬ ነው። ሕዝብ በሕዝብ ላይ ወንድም በወንድም ላይ፣ ወገን በወገኑ ላይ፣ ልጆች በልጆች፣ ወላጆች በልጆች፣ ባል በሚስቱ፣ ሚስትም በባል፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ወዘተ ተነስቷል። ሌላው ቀርቶ ሰው ራሱን በራሱ ላይ የሚያነሳሳበት፣ የሚያምጽበት፣ የሚጣላበት ጊዜ በመሆኑ እነሆ በዓመጻ ብዛት ፍቅር የቀዘቀዘበት፣ ቢወጡ ቢወርዱ በረከት የራቀበት፣ ባገኘ ቁጥር ሰው የሚጎድልበት ፣በሰበሰበ ቁጥር የሚበተንበት፣ ቢበሉ የማይጠገብበት፣ ቢጠጡ የማይረካበት፣ ቢለብሱ ድምቀትና ሙቀት የማይገኝበት፣ ጤና ቢባል የጠፋበት፣ ሰላም ቢባል የታጣበት፣ እምነት ቢባል የማይገኝበት ዘመን ውስጥ አለን። ይሁንና ከዚህ ለመራቅና ለመጠበቅ እስከመጨረሻው የጸና እርሱ ይድናል ነው የተባልነው።
“እስከመጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” /ማቴ. ፳፬፥፲፫/
እስከመጨረሻውስ የምንጸናው በምንድን ነው? የመጀመሪያው በሃይማኖት ነው። ለዚሁም ቅዱስ ጳውሎሰ /በ፪ቆሮ. ፲፫፥፭/ ላይ «በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ» ብሎናል። በሃይማኖት መኖር ማለት ሃይማኖታችን የሚያዘንንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምትነግረንን ንስሐ በመግባት፣ ጾሙን በመጾም፣ ጸሎቱን በመጸለይ፣ ስግደቱን በመፈጸም፣ ምጽዋቱን፣ አስራቱን በማውጣት፣ ሥጋ ወደሙን በመቀበል እና የዕለት ሕይወታችን የዕለት እንጀራችን አድርገን በትህትና በመታዘዝ በመልካም አርዓያነት እስከ መጨረሻው ብንፀና ከመዓቱና ከመቅሰፍቱ እንድናለን ፡፡
 ስለዚህ ሃይማኖታችንን መጠበቅ የራሳችንን ሕልውና መጠበቅ በመሆኑ /ዕብ. ፫-፲፬/ «የመጀመሪያ እምነታችንን እስከመጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናል» ተብለናልና የመጀመሪያይቱን፣ የጥንቷን፣ ያልተበረዘችውን፣ ያልተከለሰችውን፣ በዘመን ብዛት ቄንጥና ጌጥ ያልወጣላትን የማይወጣላትን አባቶቻችንና እናቶቻችን የተጠቀሙባትን ኢትዮጵያ ሃገራችን በዓለም የታወቀችባትን እጆቿን ዘርግታ ከፈጣሪዋ በመቀበል ከእግዚአብሔር መገናኛችን ቋንቋ ሆና መግባቢያችን ዜማ ሆና መዝሙራችን መለያ ሆና ክብራችን ወኔ ሆና ብንርቅ የምንቀርብባት ዳር ድንበር አስጠባቂያችን ብንጣላ የምንታረቅባት ብናጣ የምናገኝባት ብንደኸይ የምንከብርባት ብንታመም የምንድንባት ብንሞትም በሕይወት የምንነሳባት የመጀመሪያይቱ የተዋሕዶ እምነታችን ናትና እስከመጨረሻው በእርሱ የጸና እርሱ ይድናል።
ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሳሉና /ማቴ. ፳፬፥፳፬/
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስሙ ከሚመጡ ሐሰተኞች መምህራንና ሐሳዊ መሢሕ እንድንጠነቀቅና እንድንጠበቅ ያስተማረናል:: እነዚህ ሐሳውያን በተዓምራትና በፈውስ ስም ሰውን የሚያምታቱ “ጌታ እኛጋ እየተሰበከ ነውና ኑ በመንፈስ ተሞሉ ጌታ በዚህ አለ ምድርን የሚከድኑ አገልጋዮች በኛ ዘንድ አሉ” በሚሉና የራሳቸውን የሥጋ ፈቃድና ፍላጎት የተመላ ከእግዚአብሔር ቃል ውጭ የሆነ ትምህርት የሚያስተምሩ ናቸው:: ኢሳ ፵፬፥ ፳፭ ሕዝ ፲፫፥፫ ኤር ፳፫፥፲፮
እውነተኞቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታን ሲከተሉ ሁሉን ትተን ተከተልንህ /ማር. ፲፩፥፳፮/ ቢሉት ኢየሱስም መልሶ እውነት እላችኋለሁ ስለ እኔና ስለወንጌል ቤቱን፣ ወንድሞቹን፣ እህቶቹን፣ አባት እናቱን፣ ሚስት ልጆቹን፣ እርሻ ሀብቱን የተወ መቶ እጥፍ የማይቀበልና በሚመጣውም ዓለም የዘለዓለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም ብሎ ከምድራዊ ክብር ይልቅ የሚያገኙትን ሰማያዊ ጸጋ ገልጾላቸዋል::
የዛሬዎቹ ሐሳውያን መምህራን የእግዚአብሔርን ቃል ማስተማርንና የመዝሙር አገልግሎት መነገጃ መንገድ በሀብትና በዝና መክበሪያ መሰላል ለማድረግ ሲሮጡ ይታያል:: ። የሐዋርያት ሕይወትና መንፈሳዊ ተጋድሎ የሚያስተምረን ብርና ወርቅን ለመሰብሰብ ሳይሆን እግዚአብሔርን በሚያከብር ሕይወት እንድንመላለስ ነው:: /ሐዋ. ፫፥፮/ ጌታም በቅዱስ ወንጌል “ ለሚጠፋ መብል አትሥሩ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ” ብሎናል ዮሐ ፮፥ ፳፯ ስለዚህ ሁላችን በማስተዋል እንድንጓዝና በእምነታችን ጽኑ እንድንሆን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ባሕል እንዳንወጣ ባዕድ ሥርዓት ባዕድ የአነጋገር ዘይቤ የመዝሙር ዝማሬ እንዳንቀላቅል የሰው ስሜት እየተከተልን እንዳንጎዳ ሳናውቀው በጥፋት ርኩሰት የድፍረትን ስሕተት በተቀደሰው ስፍራ ላይ እንዳናሰለጥን ነው የሚያስጠነቅቀን ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ!
በተለይ ምእመናንን ለመጠበቅ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ለማክበር እግዚአብሔር ፤ አደራ የጣለብን የምድር ጨው የተባልን ካህናት
Ä አልጫውን ዓለም ካላጣፈጥነው፣
Ä የዓለሙ ብርሃን ተብለን ጨለማ ኃጢአትን በንስሐ ትምህርት ካላበራን፣
Ä የእግዚአብሔር ዓይኖች ተብለን ሁሉን በእኩልና በርህራሄ ካልተመለከትን፣
Ä የቤተ ክርስቲያን መብራት ተብለን ሕጓ ሲጣስ ሥርዓቷ ሲፈርስ የጨለማ ኃይል ሲከባት ከእንቅብ በታች እያበራን ጭራሽ የምናቃጥላት ከሆነ፣
Ä የመላዕክት ምሳሌ እየተባልን እንደ ቅዱስ ገብርኤል «ንቁም በበሕላዌነ እስከንረክብ ለአምላክነ» ብለን ባለንበት በጥንቷ በቀደመችው ሃይማኖታችን ጸንተን እንጠብቅ የማንል ከሆነ ቅዱስ ጴጥሮስ /፩ ጴጥ. ፭፥፫/ ላይ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ ያለውን ቃል ለእርሱ የተሰጠችውን ክህነት ይዘን ቃሉን ግን የማንጠብቅ ከሆነ ለመሆኑ ከኃያሉ ከእግዚአብሔር ክንድ የሚያድነን ማነው? «መንጋውን ለሚተው ለምናምንቴ እረኛ ወዮለት!» ተብለናል።/ዘካ. ፲፩፥፲፯/።
ይልቁንስ እኛ በኑሮም በቃልም በርትተን ቤተ ክርስቲያናችንን ብንጠብቃት ስለ አንድነቷ ጸንተን ብንቆምላት ሕጓን አስከብረን ሥርዓቷን ብንፈጽምና ብናስፈጽምላት የምድራዊውን አስተሳሰብና የመናፍቃኑን ማዕበል በአንድነት ብንቋቋምላት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ያለሥርዓት የሚሄዱትን ገሥጿቸው” /፩ ተሰ. ፭፥፲፬/ እንዳለ ይህን በተግባር በየቦታው ብንፈጽምላት በዚህ የተነሳ መከራ ቢመጣ መቀበላችን ተቃውሞ ሲነሳ መቋቋማችን የሚገባን ክብራችን ይሆናል። ለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ /በፊሊ.፩፥፳፰/ ላይ «በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ ይህም ለነርሱ የጥፋት ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው ይህም ከእግዚአብሔር ነው ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቷችኋልና ስለእርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም» በማለት እንኳንስ ለኛ ለካህናቱ ምእመናንም እንኳ በዚህ በረከት እንዲጠቀሙ ገልጿል።
ስለዚህ ሁላችንም ስለ ቤተ ክርስቲያናችን፣ ስለተዋሕዶ ሃይማኖታችን፣ ስለወገናችን፣ ስለውዲቷ ሃገር ኢትዮጵያችን፣ ስለመልካሙ ኢትዮጵያዊ ባሕላችን ጭምር መጨነቅ፣ መጠበብ፣ መጸለይ፣ መበርታት ይጠበቅብናል ግዴታችንም ነው። ይህን በማስከበር ሂደት ውስጥ ምንም ዓይነት ፈተና ቢገጥመን ተዋጊው እግዚአብሔር ይሆናል። ዓለም አብሮ ተነባብሮ ቢገፋንም አንጨነቅም፣ ብናመነታም ተስፋ አንቆርም፣ ብንሰደድም አንጣልም፣ ብንወድቅም አንጠፋም። /፪ ቆሮ. ፬፥፱-፲/ ምክንያቱም በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ጌታችን ስለዓለም ምጽአት ከተናገረው የመከራ ምልክት ሁሉ መዳኛ መንገዱ «እስከመጨረሻው የሚጸና ግን እርሱ ይድናልና» /ማቴ. ፳፬፥፲፫/ ብሎናል። 
በአጠቃላይ የደብረ ዘይት በዓል የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም መምጣት የምናስብበት፣ የመምጫው ምልክት የሆኑትን ነገሮች እየመረመርን ራሳችንን በንስሐ ሕይወት የምናዘጋጅበትና ከዘላለም ፍርድ ኩነኔ ለመዳን እንደ ቃሉ መመላለስ እንዳለብን የምናስብበት ነው። ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁም ተብለናልና ሁልጊዜ ዝግጁና ስንዱ ሆነን እንደቃሉ ለመኖር እስከመጨረሻው ጸንተን ለመዳን እግዚአብሔር ይርዳን አሜን!

የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)
           እንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት ወይቤሎሙ ለአርዳኢሁ ዑቁኬ ኢያስሕቱክሙ ወንበሩ ድልዋኒክሙ ብዙኃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ ወዘአዝለፈ ትዕግሥቶ ውእቱ ይድኅን ወአመ ምጽአቱሰ ለወልደ እጓለ እመሕያው ይትከወስ ኲሉ ኃይለ ሰማያት ወምድር አሜሃ ይበክዩ ኲሎሙ ኃጥአነ ምድር፡፡ ወይወርድ እግዚእነ እምሰማይ ዲበ ምድር በትእዛዙ ወበቃሉ ወበ አዕላፍ መላእክቲሁ በንፍሐተ ቀርን ዘእም ኀበ እግዚአብሔር ይምሐረነ አብ በይእቲ ሰዓት እሞተ ኃጢአት እስመ ገባሬ ሕይወት ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት፡፡
         ትርጉም:- ጌታችን በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ለደቀ መዛሙርቱ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ተዘጋጅታችሁም ኑሩ፤ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ እስከ መጨረሻው የጸና እርሱ ይድናል፡፡ የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ የሰማያትና የምድር ኃይላት ሁሉ ይናወጣሉ።ያን ጊዜ በምድር ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ ያለቅሳሉ አላቸው፡፡ጌታችንም ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ በመለከት ድምፅ ከአእላፍ መላእክት ጋር በግርማ መለኮቱ ከሰማይ ወደ ምድር ይወርደል፡፡ በዚች ዕለትም ከሞተ ኃጢአት አብ ይማረን የሕይወት ባለቤት የሰንበትም ጌታ ነውና፡፡
ምንባባት መልዕክታት
(1ኛተሰ.4÷13-ፍጻ.) ወንድሞቻችን ሆይ÷ ስለ ሞቱ ሰዎች÷ ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች እንዳታዝኑ ልታውቁ እንወዳለን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ እንደ ተነሣ ካመንን እንዲሁ እግዚአብሔር ሙታንን በኢየሱስ ያስነሣቸዋል፤ ከእርሱም ጋር ያመጣቸዋል፡፡ .......
(2ኛ ጴጥ.3÷7-14) አሁንም ሰማይና ምድር በዚያ ቃል ለእሳት ተዘጋጅተዋል፤ ኃጥኣን ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀንም ተጠብቀዋል፡፡ነገር ግን ወንድሞቻችን ሆይ÷ ይህን አትርሱ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ አንዲት ቀን እንደ አንድ ሺህ ዓመት÷ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን ነውና፡፡ 

ግብረ ሐዋርያት
(የሐዋ. 24÷1-21) በአምስተኛውም ቀን ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከመምህራኑና ጠርጠሉስ ከሚባል አንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ ጳውሎስንም በአገረ ገዢው ዘንድ ከሰሱት፡፡ ጳውሎስም በቀረበ ጊዜ ጠርጠሉስ እንዲህ እያለ ይከስሰው ጀመረ፤ክቡር ፊልክስ ሆይ÷ በዘመንህ ብዙ ሰላምን አግኝተናል፤ በጥበብህም በየጊዜው በየሀገሩ የሕዝቡ ኑሮ የተሻሻለ ሆኖአል፤ ሥርዐትህንም በሁሉ ዘንድ ስተመሰገን አግኝተናታል፡፡(ተጨማሪ ያንብቡ)
ምስባክ    
መዝ. 49÷2 እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይመጽእ፡፡ ወአምላክነሂ ኢያረምም፡፡ እሳት ይነድድ ቅድሜሁ፡፡
ትርጉም፦ እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል፡፡ አምላካችንም ዝም እይልም፤ እሳት በፊቱ ይነድዳል በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ፡፡
ወንጌል
(ማቴ. 24÷1-25) ጌታችን ኢየሱስም ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው የቤተ መቅደሱን የሕንጻ አሠራር አሳዩት፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም፡፡” (ተጨማሪ ያንብቡ)
ቅዳሴ: - ቅዳሴ ዘአትናቴዎስ 


በአጠቃላይ የደብረ ዘይት በዓል የጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም መምጣት የምናስብበት፣ የመምጫው ምልክት የሆኑትን ነገሮች እየመረመርን ራሳችንን በንስሐ ሕይወት የምናዘጋጅበትና ከዘላለም ፍርድ ኩነኔ ለመዳን እንደ ቃሉ መመላለስ እንዳለብን የምናስብበት ነው። ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁም ተብለናልና ሁልጊዜ ዝግጁና ስንዱ ሆነን እንደቃሉ ለመኖር እስከመጨረሻው ጸንተን ለመዳን እግዚአብሔር ይርዳን አሜን!

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...