ቅዳሜ 2 ሜይ 2015

‹‹ምንም ብትሉ÷ ምንም ብትሉ የማይከፈል ሕዝብ ነው፤… መሸበር አያስፈልግም›› /የበዓለ ቅዱስ ጊዮርጊስ የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ውርስ/


Historical+account+of+His+Grace+Abune+Gregory+II-p2-3በረከታቸው ይደረብንና የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ (1932 – 1982 ዓ.ም.) ሚያዝያ 23 ቀን 1982 ዓ.ም. በሻሸመኔ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሰጡት ትምህርት
ጀግና በጦር ሜዳ ይወለዳል፤ በክፉ ቀን ከብዙ ፈሪዎች ከብዙም ጀግኖች መካከል ቅ/ጊዮርጊስ ተገኘ
የተወደዳችኹ ምእመናን፤ በዚኽች በበዓለ ኀምሳ ውስጥ፣ ዛሬ ተጨማሪ በዓል የምናከብረው የታላቁን ሰማዕት የቅዱስ ጊዮርጊስን የምስክርነት በዓል ነው፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ የተወለደው በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ነው፡፡ በእርግጥ ያ ዘመን ለክርስቲያኖች ጥሩ ዘመን አልነበረም፤ ያ ጊዜ ለክርስቲያኖች ጥሩ ጊዜ አልነበረም፡፡ ክርስቲያኖች የሚፈተኑበት ጊዜ ስለነበር ይኼ ታላቅ ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚያ ጊዜ ተገኘ፡፡ ጀግና በጦር ሜዳ ይወለዳል እንደሚባለው ኹሉ፤ ክፉ ቀን ያስተዛዝባል፤ ክፉ ቀን ደግሞ ብዙ ጀግኖች ይከሠቱበታል፤ ፈሪዎች የሚታወቁት ጀግኖችም የሚታወቁት በክፉ ጊዜ ነው፡፡ በደኅና ቀንማ ኹሉም ጀግና ነው፤ ኹሉም ልባም ነው፡፡ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚያ በክፉ ቀን ከብዙ ፈሪዎች መካከል ከብዙም ጀግኖች መካከል እርሱ ተገኘ፡፡
የሊቀ ሰማዕቱ የፈተና ንብርብር፣ የድል እና የጽድቅ አክሊል
St-George
ቅዱስ ጊዮርጊስን ይከራከሩት የነበሩት ሰዎች፣ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስቸግሩት የነበሩት ሰዎች ተራ ሰዎች አልነበሩም፡፡ የታናሽ እስያን በትረ መንግሥት የጨበጡ ንጉሣውያን ቤተ ሰዎች ነበሩ፤ የዳክዮስ ቤተ ሰዎች ነበሩ፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመሪያ የተፈተነው፣ ከንጉሡ ልጆች አንዲቱን ልዕልት እንዲያገባ ነበር፡፡ መልከ ቀና ስለነበር፣ ዘረ ጥሩ ስለነበር ተመርጦ ሃይማኖቱን እንዲክድ እና ለጣዖት እንዲሰግድ ወዲያውም ደግሞ የንጉሡን የመጀመሪያ ልጅ ልዕልቲቱን እንዲያገባ ነበር፡፡ በፍትወት ነበር የተፈተነው ማለት ነው፡፡ እንግዲኽ በዚኽ ፈተና ውስጥ ብዙ ብዙ ነገሮች አሉ÷ ፍትወት አለ፤ ገንዘብ አለ፤ ሥልጣን አለ፤ የፈተና ንብርብር ነው የደረሰበት ጊዮርጊስ፡፡ ነገር ግን ጊዮርጊስ÷ እንዳልኋችኹ ጀግና ሰው ስለነበር ለዳክዮስ እና ለቤተ መንግሥቱ አልተንበረከከም፤ አሸነፈ! እና በእግዚአብሔር ዘንድ በ፳፫ ዓመቱ÷ ዛሬ ወጣቶች ኃጢአት ለመሥራት ልምምድ በሚያደርጉበት ጊዜ እርሱ አሸንፎ የድል እና የጽድቅ አክሊል ተሸለመ፡፡ ይኼን ነው እንግዲኽ ዛሬ ክርስቲያኖች የሚያከብሩት፡፡ ክፉውን ነገር ኹሉ ያሸነፈ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሽልማት የሚያገኝበት ዕለት ነው፡፡ የሽልማት ቀን ማለት ነው ዛሬ፡፡
በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ አገሩ የት ነው? ቋንቋው ምንድን ነው? አይባልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምታገናኝ ናት፤ ሕዝብን እና ሕዝብን የምታዋሕድ አንድ የምታደርግ ናት፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ስለኾነች የትም ይወለድ የትም የእግዚአብሔር ሰው መኾኑን ተቀብላ ታከብራለች፤ ሌሎችም እንደዚኹ፡፡ ለምሳሌ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በትውልዳቸው ኢትዮጵያዊ ሲኾኑ በግብጽ ብትሔዱ ዛሬ በእስክንድርያ በካይሮ በሌሎችም ቦታዎች የተክለ ሃይማኖት መቅደስ የሌለበት፣ የተክለ ሃይማኖት ሥዕል የሌለበት አታገኙም፡፡ በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ አገሩ የት ነው? ቋንቋው ምንድን ነው? አይባልም፡፡ የእግዚአብሔር ሰው መኾኑ ብቻ ነው የሚታየው፡፡ ይኼ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ኹሉ የተወረሰ ሐዋርያዊ ውርስ ነው፡፡
ሐዋርያትም መጀመሪያ ብዙ የታገሉት እስራኤልን እና አሕዛብን ለማገናኘት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምታገናኝ ናት፤ ሕዝብን እና ሕዝብን የምታዋሕድ አንድ የምታደርግ ናት፡፡ ስለዚኽ ነው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳንን ማክበር ብቻ ሳይኾን የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድ ሕዝብ ያደረገችው፡፡ ምሥራቅ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን፣ ደቡብ ሳትለይ፤ አኹን በዛሬው ቀን ከቀይ ባሕር እስከ ጋምቤላ ከዚያም እስከ ዘይላ ድረስ ብትሔዱ÷ የጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ባለበት ኹሉ በዓሉ ይከበራል፡፡ አዎ! ጦርነትም ይኹን ረኀብም ይኹን ይከበራል፤ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ናትና፡፡ ጸሎታችንም መሥዋዕታችንም÷ በዚኽም ያለነው በዚያም ያለነው አብሮ ወደ እግዚአብሔር ይሔዳል፡፡
ለሐዋርያት ትምህርት ምልክቱ መለያያ ምክንያት እየፈጠሩ ሰውን እንዲጠፋ አለማድረግ ነው
ዛሬ ግን የሚመጡ እምነቶች ሰውን እና ሰውን የሚለያዩ ናቸው፡፡ ዛሬ እምነቶች ነን ብለው የሚመጡት እናትን እና ልጅን፣ አባትን እና ልጅን÷ ጎጥን፣ ጎሳን፣ ጎራን የሚለዩ ናቸው፡፡ ስለዚኽ ነው እኛ፣ እነዚኽ እንደ ሰኔ ሰርዶ ራሳቸውን ብቅ ብቅ ያደረጉትን ኹሉ የማንቀበላቸው የሐዋርያትን ትምህርት ስለማያስተምሩ ነው፡፡ ለሐዋርያት ትምህርት ምልክቱ ምንድን ነው? ሕዝብን እና ሕዝብን አንድ ማድረግ ነው፤ የተለያዩትን አንድ ማድረግ ነው፤ መለያያ ምክንያት እየፈጠሩ ሰውን እንዲጠፋ አለማድረግ ነው፡፡
ምንም ብትሉ÷ ምንም ብትሉ የማይከፈል ሕዝብ ነው፤… መሸበር አያስፈልግም
አኹን የኢትዮጵያ ሕዝብ በምንም በምን ሳንለያይ ባለፈው የፋሲካን በዓል አክበረናል፡፡ የትም ቦታ ብትሔዱ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለችበት ቦታ፤ እዚኽ ቤተ ክርስቲያን ያሉ ሰዎች ዘራቸው ምንድን ነው? ቋንቋቸው ምንድን ነው? ሳይባል ከአሜሪካ ጀምሮ እስከዚኽ ድረስ ባለው በአንድ ቀን ይከበራል፡፡ በሎንዶን የሚኖሩ እንዲያውም የሎንዶን ዜጎች የኾኑ የእኛ እምነት ተከታዮች የስቅለት ዕለት እኛ ጋራ ሊሰግዱ መጡ፤ ከሎንዶን ድረስ፡፡ ከስቅለት ቀደም ብለው መጡ፤ መንበረ ፓትርያርኩ ማረፊያ ተሰጣቸው፤ እዚያ ቆይተው ከእኛ ጋራ ጾሙንም ስግደቱንም አክፍሎቱንም አይተው ተሳትፈው ትንሣኤውን አክብረው በሳምንቱ ወደ አገራቸው ሔዱ፡፡ እና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ከኹሉ በፊት የምትጥረው አንድ ሕዝብ ለማድረግ ነው፡፡ አኹን የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ ሕዝብ ነው፤ አንድ ሕዝብ ነው፤ ምንም ብትሉ÷ ምንም ብትሉ የማይከፈል ሕዝብ ነው፡፡ ደኅና አድርጋ መሥርታዋለች ቤተ ክርስቲያኒቱ፡፡ የአባቶቻችንን ነፍስ ይማርና ደኅና አድርገው መሥርተውት አንድ ኾኗል፡፡ ይኼን እንዳታፈርሱ ነው ቤተ ክርስቲያን አኹን የምታስተምረው፤ በየጊዜው የምትሰበሰበው ይኽን ለማስተማር ነው፡፡
ብዙ ሰዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ ያደረገችውንና የምታደርገውን አስተዋፅኦ እንደ ቀላል በመቁጠር፣ በቤተ ክርስቲያን መሰብሰባችንንም እንደ ሥራ ፈትነት በመቁጠር ብዙ ተችተውናል፡፡ አዎ÷ እንደማያልፍ የለም ትችቱም አልፏል፤ ይቀጥልም ይኾናል፡፡ ታዲያ መሸበር አያስፈልግም፡፡ የምንሠራውን እንደማናውቅ ኹሉ መሸበር እና በምንሠራው ሥራ መፍራትም አያስፈልግም፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ብቻ ሳይኾን በየሔደችበት በውጭ አገርም የምታስተምረው ሕዝብ እና ሕዝብ እንዲገናኝ፣ እንዲተባበር፣ እንዲተዛዘን፣ አንድ እንዲኾን፣ መለያያ ምልክት እንዲጠፋ ነው፡፡ የጌታችንም ትምህርት ይኼ ነበር÷ ሕዝብን እና አሕዛብን አንድ ለማድረግ፤ ኹሉም የብርሃን ልጅ እንዲኾን ነበር የጌታችን ትምህርቱ፡፡ እም ዕቶነ እሳት ዘይነድድ አንገፈነ ብርሃናተ ዘኢትሐጽፍ ተንሥኣ ለነ = ከዚያ ከሚያቃጥለው ከነዳጁ እሳት ያወጣን የብርሃናት ጌታ ብርሃናትን የሚለብስ እርሱ ሞትን በሞቱ ድል አድርጎ የተነሣልን እኛ አንድ እንድንኾን ነው፡፡ እርስ በርሳችን ብቻ ሳይኾን ደግሞ ከእርሱ ጋራም አንድ እንድንኾን ነው፡፡ ከመ ይኩኑ አሐደ ብነ ከማነ = እኛ እርስ በርሳችን ያለንን አንድነት እንድናጠናክር እና ከእግዚአብሔር ጋራ ደግሞ ያለንን ግንኙነት ደግሞ እንድናጠናክር ነው፡፡
ሰው ፍላጎቱን ካላሸነፈ የእግዚአብሔር ሰው ለመኾን አይችልም
ምናልባት እዚኽ መካከል ኢየሩሳሌም የሔዳችኹ ካላችኹ ልዳን አይታችኁት ይኾናል÷ የጊዮርጊስን መቃብር፤ እኔ ግን ሳይገባኝ ዕድል ገጥሞኝ እመቃብሩ ላይ ተንከባልዬበታለኹ፤ደስ ብሎኝ፤ የእግዚአብሔር ሰው ነው፤ ቅዱስ ነው፤ ቅድስናውም ደግሞ ለትውልድ ኹሉ ምሳሌ የሚኾን ነው፡፡ ማን ነው ወጣት ዛሬ ለክፉ ነገር የማይንበረከክ ማን ነው? ብዙ ሱሰኞች ነን እኛ÷ ብዙ ሱስ ያጠቃናል፡፡ ከጊዮርጊስ ጋራ እንደ ጊዮርጊስ የምናያቸው ብዙ ቅዱሳን አሉ÷ እነ ቂርቆስ አሉ፤ እነ ሠለስቱ ደቂቅ አሉ፤ ፍላጎታቸውን ያሸነፉ፡፡ ሰው ፍላጎቱን ካላሸነፈ የእግዚአብሔር ሰው ለመኾን አይችልም፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ለመኾን የሚችለው ፍላጎቱን ሲያሸንፍ ነው፡፡ ከወንድሙም ጋራ የሚያጣላው ከእግዚአብሔርም ጋራ የሚያጣላው የፍላጎቱ ክብደት ነው፡፡ ፍላጎቱ እየናረ ሲሔድ እየከበደ ሲሔድ የሰውን ያስመኘዋል፡፡ ያልተሰጠውን ይመኛል፡፡ ያ ነው እንግዲኽ ከጎረቤቱም ከእግዚአብሔርም የሚያጣላው፡፡
ትምህርት ሲባል…

ziway-abune-gorgorios1

እንግዲኽ በዚኽች ዕለት በእውነቱ ከእኔ ይልቅ ቀደም ብሎ ትምህርት ሰምታችኋል፤ መዝሙሮችንም ሰምታችኋል፡፡ አኹን እነዚኽ ልጆች እንዲኹ በቀላሉ የተገኙ አይደሉም፡፡ ታዲያ ከመዝሙሩ ጋራ ደግሞ ሃይማኖታቸውን ሥነ ምግባራቸውን እንዲማሩ ያስፈልጋል፡፡ ልጆቻችኹን ይዛችኹ ወደ ቤተ ክርስቲያን ኑ÷ ብቻችኹን አትምጡ፡፡ ብቻችኹን ከመጣችኹ ልጆቻችኹ ወደ ሌላ ይሔዳሉ፡፡ እናንተ እዚኽ መጥታችኹ የምትሠሩትን አያውቁም፤ ወራሾቻችኹም አይኾኑም፡፡ ስለዚኽ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስትመጡ ልጆቻችኹን ይዛችኹ ኑ፡፡ አሳዩአቸው÷ ሥዕሉን ይሳሙ፤ ቅዳሴ ጠበል ይጠጡ፤ በእምነቱ አሻሹአቸው፤ መስቀል እንዲስሙ አስተምሯቸው፤ ዕጣኑን ያሽትቱ የሚታጠነውን፤ ሥጋ ወደሙን ይቀበሉ፤ ቃጭሉን ይስሙ፤ ደወሉ ሲደወል ይስሙ፤ ቄሳቸው ማን እንደ ኾነ፣ ቤተ ክርስቲያናቸው ምን እንደ ኾነች፣ በውስጥዋ ምን ምን እንደሚሠራ ያጥኑ፤ ይማሩ፤ ወደ ሰንበቴውም ስትገቡ ይዛችኋቸው ግቡ ወደ ሰንበቴው፤ ብርሌአችኹን ይዘው ይከተሉ፤ ወደ ማኅበርም ስትሔዱ ይዛችኋቸው ሒዱ፤ ቆሎውን ተሸክመው ይምጡ፤ ይማሩ፤ እነርሱም ነገ ይኼን እንዲወርሱ÷ የነገ ባለአደራዎች መኾናቸውን እንዲያውቁ፡፡ እንዲያው ዝም ብለን ብቻ ትምህርት ሲባል ሌላ ነገር እየመሰለን ነው እንጂ ትምህርቱን እኮ እናቶቻችን አባቶቻችን አስቀምጠውልናል፡፡ ያን መውረስ ነው ያቃተን እንጂ እነርሱ አዘጋጅተው አስቀምጠውልናል፡፡ ሰንበቴው፣ ዝክሩ፣ ማኅበሩ፣ በቅዱሳን ስም በበዓል መሰብሰቡ፣ ማስቀደሱ፣ መቁረቡ፣ ቅዳሴ ጠበል መጠጣቱ፣ መስቀል መሳለሙ፣ ሥዕል መሳለሙ ይኽን ኹሉ አስቀምጠውልናል፡፡ ሌላ ምንም አዲስ ትምህርት እኮ አያስፈልገንም ነበር፡፡
የትውልድ አደራ
መመካት የሚገባን ቢኾን ኖሮ መመካት የሚገባን ሰዎች ነን እኮ እኛ፡፡ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር መመካት እንጂ በራስ መመካት አይገባም፡፡ የሚገባ ቢኾን እኛ ከዓለም ኹሉ በበለጠ መመካት ይገባን ነበር፤ ምክንያቱም አባቶቻችን እናቶቻችን ሥርዐታችንን እምነታችንን ኹሉ ሰፍረው ቆጥረው ያስረከቡን ስለኾነ ነው፡፡
እና ይኽ ትውልድ ይህን እንዳያጣ ነው አደራ የምንለው፤ ይኽ ትውልድ ይህን ከቀበረ በኋላ ይህን ካጠፋ በኋላ እንደገና ወደ ቤተ መዘክር እንዳይሔድ ነው አደራ የምንለው÷ ሃይማኖቱን ፍለጋ ታሪኩን ፍለጋ፡፡
አምላከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ይጠብቃችኹ፤
አምላከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያበርክታችኹ፤
አምላከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያክብራችኹ፤
በአገልግሎቱ የተሳተፋችኹትን፣ ቁማችኹ ያስቀደሳችኹትን፣ ትምህርቱን የሰማችኹትን፣ ልቡናችኹን ለእግዚአብሔር የሰጣችኹትን ኹሉ እግዚአብሔር በበረከት ያትረፍርፋችኹ፡፡ አቡነ ዘበሰማያት፡፡

ቅዳሜ 25 ኤፕሪል 2015

ቀጣይ ሥራዎች ምን ሊሆን እንደሚገባ ብንወያይ


   
30 ኢትዮጵያውያን በሊብያ  ሰማእትነትን  ተቀበሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አዘነ . አለቀሰ ዓለም በሙሉ የሃዘን መግለጫ ሰጠ በጣም ግሩም ነው ፡፡ ነገር ግን ቀጣዩ ሥራችን የሚሆነው ምንድነው ?
ቅዱስ  ሲኖዶስ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን  በሚፈቅደው  መልኩ የሚወሰነውን  ውሳኔ ለዓለም እንደሚያሳውቁ ቅዱስ ፓትርያርኩ ባለፈው ገልጠዋል  ይሁን እንጂ
v  .     የተሰውትን 30 ኢትዮጵያውያንን  ሙሉ መረጃ  አሰባስቦ  ለቅዱስ  ሲኖዶስ ማቅረብ  የሚችል ጊዜያዊ  ኮሚት  ቤተክርስቲያናችን ማቋቋም ብትችልና ኮሚቴው መረጃዎችን አጠናክሮ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤው  ቢያቀርብየሰማእታቱ  ፎቶ ሌሎችም መረጃዎች  በዚያ መቀመጥ ቢችል ደብሩ ወደፊትም በተመሳሳይ መልኩ ሰማእትነት ለተቀበሉት ኢትዮጵያን ብቻ ቢሆን /አውደ ሰማእታት ቢሆን/
v  አሁን በሊብያ በሕይወት ያሉትን በመርዳት ያሉበትን ሁኔታ በመከታተል የሚያስፈልገውን ሁሉ ከሚመለከተው ጋር ሆኖ የመርዳቱንም ነገር ቢታሰብበት
በአጠቃላይ ቤተክርስቲያቲ ለምትወስነው ቀጣይ ሥራዎች ግብአት ይሆን ዘንድ   ሀሳብ ቢሰጥ!!



















ዓርብ 24 ኤፕሪል 2015

ማኅበረ ቅዱሳን በሊቢያ የተሰዉ ሰማዕታት ቤተሰቦችን በማጽናናት ላይ ይገኛል


አትምኢሜይል
ሚያዝያ 15 ቀን 2007 ዓ.ም.
002lekso001lekso003lekso004lekso
በሰሜን ሊቢያ ሜድትራንያን ባሕር ዳርቻ በእምነታቸው ምክንያት በግፍ ከተገደሉ ኢትዮጵያውያን መካከል ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ከሚገኙ የሰማዕታት ወላጆች ጋር የማኅበረ ቅዱሳን አመራርና አባላት ሐዘናቸውን እየተካፈሉ ነው፡፡
መርሐ ግብሩ በማኅበሩ መዘምራን ሰማዕታቱን የሚያስብ መዝሙር የቀረበ ሲሆን፤ መዝሙር 118፡ 129 ላይ €œምስክሮችህ ድንቆች ናቸው፣ ስለዚህ ነፍሴ ፈለገቻቸው€ በሚል ርእስ ሰባኬ ወንጌል ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ጸሎተ ምሕላ የተካሄደ ሲሆን ከሰማዕታቱ በረከት ለመሳተፍ የእራት ማብላት ሥነ ሥርዓት በማኅበሩ አስተባባሪነት በቦታው ተካሔዷል፡፡

ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው አይ ኤስ አሸባሪ ቡድን በአሰቃቂ ሁኔታ ከገደላቸው ኢትዮጵያውያን መካከል እስከ አሁን አምስቱ የቂርቆስ አካባቢ ክርስቲያኖች ሆነው ተገኘተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የተሰጠ መግለጫ



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን
‹‹ርትዕት ሃይማኖቶሙ ለቅዱሳን አበዊነ = የአባቶቻችን ሃይማኖት የቀናች ናት››
Addis Ababa sunday school students02
የአ/አ ገዳማትና አድባራት ሰንበት ት/ቤቶች በዛሬው የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የጸሎተ ፍትሐት ሥነ ሥርዐት
ራሱን እስላማዊ መንግሥት (አይ ኤስ አይ ኤስ) እያለ የሚጠራው የጨካኝ አረመኔዎች ስብስብ፣ በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ላይ ያካሔደው ዘግናኝ ግድያ ሳይበቃው ይህን እኩይ ድርጊቱን በልዩ ልዩ ምክንያት ከአገር ተሰድደው በሊቢያ በነበሩ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ላይ ፈጽሟል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ‹‹ሃይማኖቱን ገልጦ የማይናገር በክብር የተገለጠ አይኾንም››/ሃይ.አበ. 63÷41/ እንዳለው ‹‹ሃይማኖታችንን አንክድም፤ ማዕተባችንን አንበጥስም›› ባሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ላይ ኢሰብአዊነት በተሞላበት ግፍ አንገታቸውን በሰይፍ በመቅላት እና ጭንቅላታቸውን በጥይት በመበታተክ በጭካኔ አገዳደል ገድሏቸዋል፡፡
ይህ ቡድን ከጨካኝ እና አረመኔ የግድያ ድርጊቱ አንጻር የአባላቱን ሰብአዊ ፍጥረት አጠራጣሪ የሚያደርገው ነው፡፡ እጆቻቸው በደም የተሞሉ ናቸው፡፡ ቅዱስ ዳዊት፣ ‹‹የሰውን ደም ለማፍሰስ እግራቸው ፈጣን ነው፤ በመንገዳቸው ኃሣር መከራ አለ፤ የፍቅርን መንገድ አያውቋትም፤ በልቡናቸው እግዚአብሔርን መፍራት የለም፤›› እንዳለው ነው፡፡ መዝ. 13(14)÷1-4፡፡
Addis Ababa sunday school students
የአ/አ ገዳማትና አድባራት ሰንበት ት/ቤቶች በዛሬው የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የጸሎተ ፍትሐት ሥነ ሥርዐት
ስለኾነም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ሥር የምንገኝ ሰንበት ት/ቤቶች፡-
  • በየትኛውም ቦታ እና ጊዜ ክርስትናን በማስገደድ እና በመቀሰጥ ለመለወጥ የሚደረገውን ዘመቻ እና እንቅስቃሴ በጥብቅ እንቃወማለን፡፡
  • ራሱን አይ ኤስ አይ ኤስ ብሎ የሚጠራውን ቡድን ድርጊት በጥብቅ እናወግዛለን፡፡
  • በዚኹ ቡድን እና በቡድኑ የአሸባሪነት ድርጊት ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ያወጣቸውን የአቋም መግለጫዎች በሙሉ እንቀበላለን፤ በአፈጻጸሙም እንታዘዛለን፡፡
  • በደቡብ አፍሪቃ በዜጎች እና ሌሎችም ወገኖች ላይ የሚፈጸመውን ጥላቻ እና ዘረኝነት የወለደው ግድያ እና ዘረፋ በጥብቅ እናወግዛለን፡፡
  • በአዲስ አበባ ያሉ ሰንበት ት/ቤቶች ኹሉ መርሐ ግብር በማውጣት በየቤተሰቦቻቸው ቤት በመገኘት ሐዘንተኞችን የሚያጽናኑ ይኾናሉ፡፡
ወደፊትም ኹኔታውን እየተከታተልን የሚጠበቅብንን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መኾናችንን እየገለጽን ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን፣ በተጋድሎ ላለፉት ወንድሞቻችን ደግሞ ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን ልዑል እግዚአብሔር እንዲሰጥልን እንለምናለን፡፡
ልዑል እግዚአብሔር በሃይማኖታችን ያጽናን፤ ለዓለሙም ሰላም ይስጥልን፤ አሜን፡፡
የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት

ሐሙስ 23 ኤፕሪል 2015

ተዋሕዶ-በደም

ሚያዝያ 14ቀን 2007ዓ.ም
መምህር ሳሙኤል ተስፋዬ
0000000000በደም ተመሥርተሽ
በደም ተገንብተሸ
በደም ተዋሕደሽ
በደም ተሰራጭተሸ
ደሙ ብርሃን ሆነን ከጨለማም ወጣን ፡፡
ተዋሕዶ
በደም አጥምቀሽን
በደም አጽንተሸን
ከጌታችን ጋራ አንድ አካል አረግሽን፡:
ተዋሕዶ
በደሙ አክብረሽን
በደሙ አስታርቀሽን
ደሙን ከካሰልን
የደሙን ማኅተም ኃይሉን ተጎናጸፍን፡፡

ተዋሕዶ
በደም ተገዝቼ
በደሙም ነጽቼ
በደሙ ጸንቼ
ኖርኩኝ ረክቼ ደሙን ጠጥቼ ፡፡

ተዋሕዶ
ለዓለም በፈሰሰው ደሙ
ምልክት ዓርማዬ ሲሆን ማኅተሙ
ነብር ዝንጉርጉርነቱን መለወጥ እንዳይችል መልኩን
እንዴት በመከራ አላውቀውም ልበል?

ተዋሕዶ
ደሙ ይጠራኛል ጽና በርታ እያለ
ምልከት በልቤ ታትሞ ስላለ፡፡
እንዴት ልበጥሰው አላውቅም ልበለው?
መንፈሱ አጽንቶ መንፈሱ ካገዘኝ፡፡
የቀድሞ ማንነት በደሌን ሳያየው
በማተቤ አጸናኝ ለመንግሥቱ አበቃኝ፡፡

                                   በአውሮጳ   የካህናት አንድነት ማኅበር ሊቋቋም መሆኑ ታወቀ በ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመላዋ አውሮጳ   የተውጣጡ ካህናት፡” የ...