- ጥናቱን የማስቆም አልያም የማዘግየት ፍላጎት ያላቸው ሙሰኛ እና ጎጠኛ ‹ተቃዋሚዎች› የመናፍቃንን ዓላማ በውስጥ አርበኝነት የማስፈጸም ዓላማ ሊኖራቸው እንደሚችል በማስጠንቀቅ ሕጋዊና የሥነ ሥርዐት ርምጃዎች እንዲወሰዱባቸው አመልክተዋል
* * *
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ጥር 5 ቀን 2006 ዓ.ም
ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
አዲስ አበባ፤
ጉዳዩ፡- የቤተ ክርስቲያኒቱን አደረጃጀትና አሠራር ለማሻሻል የተጠናው ጥናት ተግባራዊ እንዲደረግ ስለ መጠየቅ
ቅዱስ አባታችን፡-
ከሁሉ አስቀድሞ እኛ ምእመናን የመንፈስ ቅዱስ ልጆችዎ በመጀመሪያው በዓለ ሢመትዎ ዋዜማ ላይ ኾነን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛው
ፓትርያርክ ኾነው በመመረጥዎ የተሰማንን ደስታ እየገለጽን መልካም የሥራ ጊዜ እንዲኾንልዎት እንመኛለን፡፡ እንዲሁም
ለ2006 ዓ.ም. የጌታችን የመድኃኔታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ የልደት በዓል እንኳን በሰላም አደረሰዎ ስንል
የቅዱስነትዎ ቡራኬ እንዲደርሰን ከእግረ መስቀልዎ ሥር ኾነን በመማፀን ነው፡፡
ቅዱስ አባታችን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፡-
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነቷ ሥርዓቷና ትውፊቷ እንከን የማይወጣለት በዓለም ዐደባባይ
ገናናነቷ ጥንታዊነቷና ድንቃድንቅ ቅርሶቿ ገዳማትና አደባራቷ ከሰው ልጆች ዓይነ ኅሊና የማይጠፋ ለሀገርና ለወገን
የሚጠቅም መንፈሳዊና ማኅበራዊ አስተዋፅኦ ያበረከተች እንደኾነች በእምነት ከማይመስሉን ወገኖች ጭምር ምስክርነት የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡
የኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ብቻ ሳትወሰን የመንግሥት መዋቅርና አደረጃጀት
እንደዛሬው ባልተስፋፋበትና ባልተጠናከረበት ወቅት የሕዝቡ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ኑሮ እንዲሻሻል፣ የአገሪቱ
ሉዓላዊነት እንዲከበር፤ ፍቅርና ሰላም እንዲሰፍን በሕዝቡ የዕለት ተዕለት አኗኗር ሁሉ የመቻቻል መንፈስ እንዲሰፍን
በማድረግ በአጠቃላይ ለሀገሪቱ ሥልጣኔና ዕድገት የተጫወተችውን የላቀ ሚና ታሪክ የማይረሳውና በገሓዱ ዓለምም
በግልጽ የሚታይ ነው፡፡
ቅዱስ አባታችን፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፡- ይህ በእንዲህ እንዳለ ኾኖ በአሁኑ ወቅት በሰፊው የሚስተዋለው
የሥነ ምግባር ግድፈቶች፣ ጎጣዊ/ዘረኛ አሠራሮችና የሙስና መንሰራፋት ለምእመናን ወደ መናፍቃን ጎራ መጉረፍ
ምክንያት ከመኾናቸውም ባሻገር ፤በቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የተጠናና የተደራጀ
በሚመስል ኹኔታ የሚፈጽሙትን የሥነ ምግባር ጉድለቶች በማየት አንዳንድ ምእመናን ከቤተ ክርስቲያን ይርቃሉ፤ በቤታቸው
ኾነው መጸለይን ይመርጣሉ፤ እነሱን አርኣያ በማድረግም ኃጢአት ለመሥራት ይደፋፈራሉ፤ ሃይማኖቱ በራሱ ሕጸጽ
እንዳለበት አድርገው የሚቆጥሩም አሉ፡፡
የሙሰኞችና
የጎጠኞች ዋነኛ ዓላማ ላይ ላዩን እንደሚታየውና እንደሚገመተው የራሳቸውን ጎጥ/ጎሳ አባላት መጥቀም ብቻ ሳይሆን
በጥልቀት ሲመረመር ራሳቸውን ለመጥቀም በሚያደርጉት እንቅስቃሴ አውቀውም ኾነ ሳያውቁ በተዘዋዋሪ መንገድ በውስጥ
አርበኝነት የመናፍቃንን ዓላማ ማስፈጸም መኾኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
የውስጥ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ከውጭ ጠላቶች የበለጠ አደገኛ ናቸው፤ ከመለያቸውም መካከል፡-
· ሓላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት ዘመናዊ የፋይናንስ ሥርዐት ሥራ ላይ እንዳይውል በጥብቅ ይከላከላሉ፡፡
· ከአጥቢያ ጀምሮ እስከ ሀገረ ስብከትና እስከ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ድረስ በተዘረጋ የሙስና መረብ ከሕጋዊ መዋቅሩ በበለጠ እርስ በርስ በመደጋገፍ የተፈጸሙ ጥፋቶችን ይሸፋፈናሉ፤
· የሥራ ዕድገት በሞያና በትምህርት ብቃት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን በዘመድና በጉቦ እንዲፈጸም ያደርጋሉ፣
· ጥፋተኛነቱ በተረጋገጠ የደብር አለቃ ወይም ሓላፊ ላይ ተገቢውን የሥነ ሥርዐት ርምጃ በመውሰድ ፋንታ ወደ ሌላ የተሻለ ቦታ እንዲዘዋወሩ ይደረጋል፡፡
በወዳጅም
በጠላትም በአኩሪ ታሪክና ምግባር የምትታወቀው ቤተ ክርስቲያናችን የዘመናት ስሟንና ክብሯን የማይመጥን እኩይ
ተግባራት የሚፈጸምባት ቦታ፤ ከሃይማኖት ይልቅ ግላዊ ጥቅም በሚያስቀድሙ የውስጥ አርበኞች ብልሹ አሠራር ዘረኝነት፣
ሙስናና የሥነ ምግባር ጉድለት ጎልቶ የሚታይባትና ተከታዮቿን የሚያሸማቅቅ ነውር ተግባር የሚፈጽሙባት እየኾነች
መጥታለች፡፡
ቅዱስ አባታችን፡- ይህን ኹኔታ በሚገባ የተገነዘቡት ቅዱስነትዎ በግንቦት 12/2006 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር “ምእመናን
በተለያየ መልኩ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡትን ስጦታ ዘመኑ በሚፈቅደው የፋይናንስ አያያዝና ቁጥጥር ባለመያዛችን
ለቤተ ክርስቲያን ሥራ ከሚውል ይልቅ በየመንገዱ እየተንጠባጠበ ወፎች የሚለቃቅሙት እንደሚበዛ ፍጹም የማይካድ ሐቅ
ነው፡፡
በሌላ በኩል ከአድልዎና ከወገንተኝነት ሙሉ በሙሉ ያልተላቀቀው አስተዳደራችን የቤተ ክርስቲያናችን ታላቅነትና ተሰሚነትን ክፉኛ እየጎዳው መኾኑ አሌ ልንለው አይገባም”
የሚለውን አባታዊ ቃልዎን በብዙኃን መገናኛ ስንሰማ እግዚአብሔር የእውነተኛ አገልጋዮቹን እንባ ተቀብሎ የቤተ
ክርስቲያናችንን ችግር መፍትሔ የሚሰጥበት ጊዜ ደረሰ ብለን ደስ ብሎናል፤ በከፍተኛ አድናቆትም ተቀብለናል፡፡
የቅዱስ
አባታችንን መንደርደሪያ ሓሳብ መሠረት አድርጎ በሰፊው የተወያየው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤም በወርቅ ቀለም
የተጻፈውን የቤተ ክርስቲያናችንን መልካም ስምና ዝና ወደ ቀደመ የክብር ቦታው ለመመለስ የሚያስችል ጥናት የሚያጠና
ኮሚቴ ማቋቋሙዎን በተለይም የቅዱስነትዎ ልዩ ሀገረ ስብከት በኾነው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አሠራርና አደረጃጀት
የሚያጠና ኮሚቴ መዋቀሩን ስንሰማ፣ ‹‹እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰባት፤ የቤተ ክርስቲያናችንን ትንሣኤ ሊያሳየን
ነው፤›› ያላለ ምእመን አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግር ይፈታል ተብሎ የታመነበት ይህ ጥናት
ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ቀርቦ ተቀባይነት ማግኘቱን ሰምተን ደስታችን ወደር አልነበረውም፡፡ ስለአደረጃጀትና
የአሠራር ማሻሻያው ጥናት ግንዛቤ ለማስጨበጥ በተከታታይ በተካሔዱ ውይይቶች የተሳተፉ ማኅበረ ካህናትና ምእመናንም
በጥናቱ ይዘት በእጅጉ ተደስተናል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የአደረጃጀትና የአሠራር ማሻሻያ ጥናቱ ተግባራዊ ኾኖ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሰንገው አላንቀሳቅስ ያሏት ሙስናና ጎጠኝነት
ተወግደው ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡት ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ለማዋል ያስችላል ተብሎ በጉጉት ሲጠበቅ
በጥናቱ ያልተደሰቱ የተወሰኑ ግለሰቦች ባቀረቡት ቅሬታ ጥናቱ ተግባራዊ ከመኾን ታግዶ እንደገና በዐዲስ መልክ
እንዲታይ መወሰኑን በከፍተኛ ድንጋጤ ነው የሰማነው፡፡
ይህ
ለቤተ ክርስቲያን ዓበይት የአስተዳደር ችግሮች ኹነኛ መድኅን ይኾናል ተብሎ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ
የታመነበት መመሪያ በተግባር ተፈትኖ በአፈጻጸም ያስከተለው ችግር ሳይመረመር ከወዲሁ በድጋሚ እንዲታይ ብሎ ማዘግየት
እስካሁን የጠፋው ጥፋት አልበቃ ብሎ በሙስናው ሥራ ለተሠማሩት ወገኖች ተጨማሪ ዕድልና ጊዜ መስጠት ወይም እነሱ
በሚፈልጉት ዓይነትና ሁኔታ ተቃኝቶ እንዲስተካከል ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ተንሠራፍቶ የቆየው ሙስናና ብልሹ አሠራር ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ለነገ ሊባል የማይችል ባስቸኳይ ርምጃ መወሰድ ያለበት ስለኾነ የቤተ
ክርስቲያቱን ሥር የሰደደና የተከማቸ ችግር ያስወግዳል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትና የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል
በኾነው በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቀው ጥናት ባስቸኳይ ተግባራዊ እንዲደረግ በአጽንኦት እንጠይቃለን፡፡
ቅዱስ አባታችን፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፡-የተቋማዊ ለውጡ ጥናት በቅዱስ ሲኖዶስ ተቀባይነት ማግኘቱ በራሱ ከፍተኛ ውጤት ቢኾንም አስፈላጊው
የአፈጻጸም ስልትና በቁርጠኝነት ሥራ ላይ ሊያውል የሚችል ቅን ታታሪ ታማኝ ተግዳሮቶችን በከፍተኛ ጽናት መቋቋም
የሚችል የሰው ኃይል ካልተመደበለት ብልጣብልጦቹ እጅ ወድቆ የታሰበውን ውጤት ሳያስገኝ ሊከሽፍ የሚችልበት አጋጣሚ
ሰፊ ነው፡፡
ስለዚህ ተቋማዊ ለውጡን በተሟላና በተሳካ ሁኔታ ሥራ ላይ ለማዋልና ዘለቄታማነቱን ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ፡
- በጥናቱ ላይ ጥያቄ ያለው ግለሰብ ወይም ቡድን ቢኖር ጥያቄውን በዝርዝር አቅርቦ በጥናት ቡድኑ ታይቶ በቅዱስ ሲኖዶስ የሚታመንበት ነገር ካለ አስፈላጊው ማሻሻያ ከሚደረግበት በስተቀር በጉጉት የምንጠብቀው የጥናት ውጤት ቢቻል ለማስቆም ካልተቻለም ለማዘግየት እንደገና በአዲስ መልክ እንዲታይ እየተደረገ ያለው አካሔድ ቆሞ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ልዕልና ተጠብቆ በውሳኔው መሠረት እንዲፈጸም እንዲደረግ፤
- የተጠናውን የአሠራርና የአደረጃጀት ጥናት የሚገመግም አዲስ ኮሚቴ በተመለከተም ጥናቱን ሊያዳብር በሚችል መልኩ በፍጥነት ሠርተው ያቀርባሉ ብሎ ለማሰብ ከኮሚቴው አባላት መካከል ከአሁን ቀደም በሀገረ ስብከቱም ኾነ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ውስጥ በተመሳሳይ ችግር ተጠቃሽ የሚኾኑ ሰዎች መካተታቸው ያሳሰበን በመኾኑ እንደገና እንዲታይልን እንዲደረግ
- ተቋማዊ ለውጡን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ያስተላለፈው ውሳኔ እንዳይፈጸም በሚያውኩና በሚቃወሙ ላይ ሌሎችን ሊያስተምር የሚችል ጥብቅ የሥነ ሥርዓት ርምጃ እንዲወሰድ እንደረግ፤
- ከቅን የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህናትና ሠራተኞች፣ ከሰንበት ት/ቤት እንዲሁም ከምእመናን የተውጣጣ ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ የሆነ የተቋማዊ ለውጥ አስፈጸሚ አካል እንዲቋቋም፤
- ከዚህ ቀደም በቤተክርስቲያን ሀብትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ምዝበራ የፈጸሙ ሁሉ ጉዳያቸው ተጣርቶ ተገቢው ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድልን፣
- ስለጎጠኝነትና ሙስና አስከፊነት የሥልጠናና ትምህርት መርሐ ግብር ቀርጾ ተግባራዊ እንዲደረግ፣
- ከሙስና የጸዱትንና የላቀ መልካም ተግባር የሚፈጸሙትን አገልጋዮች በመሸለም እንዲበረታቱ እንዲደረግ፣
- ቤተ ክርስቲያኒቱ ከወቅታዊ ሁኔታዎች አንጻር ራሷን እየፈተሸች፣ ችግሮቿን እየለየች መፍትሔ በማስቀመጥ ተግባራዊ ርምጃ ለመውሰድ የሚያስችላት የጥናትና ምርምር ማዕከል እንዲቋቋም እንዲደረግ፣
- ከመንግሥት አሠራር ልምድ በመቅሰም በስፋት የተንሰራፋውን የሙስና ተግባር መቋቋም ይቻል ዘንድ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና አካል ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እንዲቋቋም እንዲደረግ፤
ቅዱስ አባታችን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፡-ቤተ ክርስቲያናችን የደረሰባትን የበጎች/የተከታዮች ስርቆትና ብልሹ አሠራር ለማስወገድ ብቻ ሳሆን ለህልውናዋ ስትል ከችግሩ ለመላቀቅ ጨክና (በቁርጠኝነት) ይህን መሰል ድርጊት በሚፈጽሙ ስውር የቤተ ክርስቲያን ጠላቶችና የመናፍቃን ጉዳይ አስፈጻሚ ተላላኪዎች ላይ ዛሬ ነገ ሳትል በጥንቃቄ በተጠና መንገድ ጠንካራና ጠበቅ ያለ ርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀት ይኖርባታል፡፡
ሕገ
ቤተ ክርስቲያን ሲጣስ ቃለ ዓዋዲው በዘፈቀደ ሲሻር የደጋግ አባቶች አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ እንደዘበት
በቸልታ ማለፍ ከክፉ ሰዎች ክፉ ተግባር ባልተናነስ ደረጃ ቤተ ክርስቲያናችንን ጉዳት ላይ እየጣላት እንደኾነ
ልናስተውል ይገባል፡፡ ትላንት ርምጃ መውሰድ ሲቻል ባለመወሰዱ ዛሬ መመሪያውን ተግባራዊ ማድረግ እየተቻለ በጥቃቅን
ምክንያቶች ተግባራዊ ባለመደረጉ በዚች በዛሬዋ ዕለት እንኳ በቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት ይልቁንም በቅንና
እውነተኛ አባቶቻችን ላይ የሚደርሰውን ኢፍትሐዊ ውሳኔ ለማዳን እየቻልን ያለማዳናቸን በታሪክና በትውልድ ይልቁንም
በእግዚአብሔር ዘንድ ተወቃሽ ከመሆን ለመዳን አዲሱን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ እንረባረብ፡፡
ቅዱስ አባታችን፡- በመጨረሻም ያቀረብነው ጥያቄ በጥሞና ታይቶ ምላሽ የሚሰጥበት ቀነ ቀጠሮ እንዲያዝልን በታላቅ መንፈሳዊ ትሕትና እናሳስባለን፡፡
የቅዱስ አባታችንንና የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ረድኤትና በረከት ይደርብን!
ወስብሐት ለእግዚአብሔ