የገናን ዛፍ የት መጣውን /ምንጩን/ ስናጤነው ቅዱሳት መጻሕፍት እንዲህ ይነግሩናል። በዞራስተርን የሁለት አማልክት ዕምነት የሚያምኑት ምዕራባውያን አዲሱን ዓመታቸውን /2014/ ከተቀበሉ ዛሬ ሦስተኛ ቀናቸውን ይዘዋል። በዞራስተርን የሁለት አማልክት ዕምነት መሠረት ክፉውና ደጉ የተባሉ ሁለት አማልክቶች አሉ። እንደ ዕምነቱ አስተሳሰብ ከሆነ እዚህ ምድር ላይ የሆነው እየሆነው ያለውና የሚሆነውም ማንኛውም ነገር በሙሉ የሚከናወነው በእነዚህ በሁለቱ አማልክቶች ፉክክር ነው። ክፉው አምላክ ከሰለጠነ /የበላይ ከሆነ/ በምድር ላይ ክፉ የሆኑ ብዙ ነገሮች ይከሰታሉ። በተቃራኒው ደግሞ ደጉ አምላክ ከሰለጠነ በጎ ነገሮች ይከሰታሉ ማለት ነው። ምዕራባውያኑ ታዲያ ደጉን አምላካቸውን ማለትም ጣዖታቸውን ሳተርን ብለው ይጠሩታል።
በምዕራቡ ዓለም የክረምቱ ወቅት በጣም አስቸጋሪ ነው። ዛፎች ሁሉ ቅጠሎቻቸው ይረግፋሉ። ልምላሜ አይታይባቸውም። ፅድ ግን በተፈጥሮው ይህን አስቸጋሪ ወቅት ተቋቁሞ የማለፍ ኃይል አለው። በመሆኑም ፅድ ክፉውን ዘመን /ክረምቱን/ ተቋቁሞ መልካሙ ዘመናቸው እስኪመጣላቸው ድረስ በልምላሜ ይቆይላቸዋል። ይህም ሳተርን /ደጉ አምላካቸው/ ከክፉው አምላክ ለመሸሸግ በፅድ ውስጥ ተደብቆ ይኖራል ብለው ያመናሉ ምዕራባውያኑ። እናም ብራ ሲሆን /በእኛ መስከረም ጠባ እንደምንለው ነው/ የደጉን አምላክ ‹‹የእንኳን ደህና መጣህ›› በዓልን በድምቀት ያከብራሉ።